ዘካርያስ 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየኢየሩሳሌም የመዳን ተስፋ 1 ሰማይን የዘረጋ፥ ምድርን የመሠረተ፥ ለሰውም የሕይወትን እስትንፋስ የሰጠ እግዚአብሔር ስለ እስራኤል እንዲህ ይላል፦ 2 “ኢየሩሳሌምን በዙሪያዋ ላሉ ሕዝቦች ጠጥተውት እንደሚያንገዳግድ የወይን ጠጅ ዋንጫ አደርጋታለሁ፤ እነርሱ ኢየሩሳሌምን በሚይዙ ጊዜ የቀሩትም የይሁዳ ከተሞች ይከበባሉ። 3 በዚያን ቀን ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ እንደ ከባድ ድንጋይ አደርጋታለሁ፤ እርስዋን ለማንሣት የሚሞክር ሁሉ ራሱን ይጐዳል፤ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ እርስዋን ለማጥቃት ተባብረው ይመጣሉ፤ 4 በዚያን ጊዜ ፈረሶቻቸውን በፍርሃት አስጨንቃለሁ፤ ፈረሰኞችንም አሳብዳለሁ፤ የጠላቶቻቸውን ፈረሶች አሳውራለሁ፤ የይሁዳን ሕዝብ ግን በዐይኔ እየተመለከትኩ እጠብቃቸዋለሁ። 5 በዚያን ጊዜ የይሁዳ አለቆች በልባቸው ‘የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር አምላካቸው ስለ ሆነ በኢየሩሳሌም የሚኖሩት ሕዝቡ በእርሱ ኀይልን ያገኛሉ’ ይላሉ። 6 “በዚያን ጊዜ የይሁዳን ሕዝብ አለቆች በእሳት ማንደጃ ላይ ተከምሮ እንደሚነድ እንጨት፥ በእህል ነዶዎች መካከል እንደ ተቀጣጠለ ችቦ አደርጋቸዋለሁ፤ በአካባቢው ያሉትን ሕዝቦች ሁሉ ያወድማሉ፤ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ግን ምንም ሳይደርስባቸው በከተማይቱ ውስጥ ይኖራሉ። 7 “እኔ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ለይሁዳ ነገድ ድልን አጐናጽፋለሁ፤ ይህንንም የማደርገው የዳዊት ልጆች ክብርና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ክብር ከሌሎቹ የይሁዳ ነገድ ተወላጆች ከፍ ከፍ እንዳይል ነው። 8 በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንደ ጋሻ መከታ እሆንላቸዋለሁ፤ ከእነርሱ እጅግ ደካማ የተባለው እንኳ የዳዊትን ያኽል ብርቱ ይሆናል፤ የዳዊት ልጆች እንደ እኔ እንደ እግዚአብሔር ወይም እንደ መላእክት ሆነው ሕዝቡን ይመራሉ። 9 በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ላይ በጠላትነት የሚነሡትን የአሕዛብ መንግሥታት ሁሉ ለመደምሰስ እነሣለሁ። 10 “በዚያን ጊዜ በዳዊት ዘሮችና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የርኅራኄና የጸሎት መንፈስ እሞላለሁ፤ ይህንንም የማደርገው እነርሱ ለአንድያ ልጅና ለበኲር ልጅ እንደሚለቀስ ለወጉት ምርር ብለው እንዲያለቅሱለት ነው። 11 በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም የሚሰማው ለቅሶ በመጊዶ ሜዳ ለሀዳድሪሞን እንደ ተለቀሰለት ለቅሶ ይሆናል። 12 በምድሪቱ ላይ የእያንዳንዱ ወገን ቤተሰብ ለየራሱ ያለቅሳል፤ ሚስቶቻቸውም ለየራሳቸው ያለቅሳሉ፤ በዚህ ዐይነት የዳዊት ቤተሰብ ከነሚስቶቻቸው፥ የናታን ቤተሰብ ከነሚስቶቻቸው፥ 13 የሌዊ ቤተሰብ ከነሚስቶቻቸው፥ የሺምዒ ቤተሰብ ከነሚስቶቻቸው፥ በየወገናቸው ሆነው ያለቅሳሉ፤ 14 የቀሩትም በቤተሰቦች ተከፋፍለው ያለቅሳሉ፤ ሚስቶቻቸውም ለብቻ ተለይተው በማዘን ያለቅሳሉ።” |