Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘካርያስ 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የእምቢተኞች አወዳደቅ

1 ሊባኖስ ሆይ! እሳት ዛፎችሽን ያቃጥል ዘንድ በሮችሽን ክፈቺ!

2 የሊባኖስ ዛፎች ስለ ወደቁ፥ እናንተ የዝግባ ዛፎች “ዋይ!” እያላችሁ አልቅሱ፤ ግርማ የነበራቸው ዛፎች ሁሉ ጠፍተዋል፤ ጥቅጥቅ ያለው ደን ስለ ተቈረጠ የባሳን ወርካዎች “ዋይ!” እያላችሁ አልቅሱ።

3 እረኞች ለምለም የሆነ መሰማሪያቸው ስለ ወደመ “ዋይ!” እያሉ ሲያለቅሱ ስሙ፤ የዮርዳኖስን ወንዝ ተከትሎ ያለው የደን መኖሪያቸው ስለ ተደመሰሰ፥ አንበሶች በሐዘን ሲያገሡ ስሙ።


ሁለቱ እረኞች

4 እግዚአብሔር አምላኬ እንዲህ ብሎኛል፦ “እስቲ ለዕርድ የተዘጋጁትን የበግ መንጋ አሰማራ።

5 የገዙአቸው ሰዎች በጎቹን በማረዳቸው አይቀጡበትም፤ የሸጡአቸውም ሰዎች ‘እግዚአብሔር ይመስገን በልጽገናል’ ይላሉ፤ እረኞቻቸው እንኳ ለእነርሱ አይራሩላቸውም።”

6 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔም ከእንግዲህ ወዲህ በምድር ላይ ለሚኖር ለማንም ሰው ርኅራኄ አላደርግም፤ እኔ ራሴ እያንዳንዱን ሰው ለጐረቤቱና ለንጉሡ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እነርሱ ምድሪቱን ያጠፋሉ፤ እኔም ከእነርሱ እጅ አልታደጋቸውም።”

7 በጎቹን ይገዙና ይሸጡ ለነበሩት ሰዎች ተቀጥሬ እንዲታረዱ ለተፈረደባቸው የበጎች መንጋ እረኛ ሆንኩ፤ መንጋውንም በማሰማራበት ጊዜ ሁለት በትሮችን ወሰድኩ፤ አንደኛውን በትር “ተወዳጅ” ብዬ ጠራሁት፤ ሌላውን በትር “አንድነት” ብዬ ጠራሁት።

8 ሦስቱ እረኞች እኔን ስላስቈጡኝና ስለ ጠሉኝ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አስወገድኳቸው።

9 ከዚህ በኋላ መንጋውን እንዲህ አልኩ፦ “እኔ ከእንግዲህ ወዲህ እረኛችሁ አልሆንም፤ የሚሞቱት ይሙቱ፤ የሚጠፉትም ይጥፉ፤ የተረፉትም እርስ በርሳቸው ተባልተው ይለቁ፤”

10 ቀጥሎም “ተወዳጅ” የተባለውን በትሬን አንሥቼ ሰበርኩት፤ ይህን ማድረጌም ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ቃል ኪዳን መቋረጡን ለማመልከት ነው።

11 በዚህ ዐይነት ቃል ኪዳኑ በዚያኑ ዕለት ፈረሰ፤ ይህንንም ሳደርግ ይመለከቱኝ የነበሩት የበግ ነጋዴዎች የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ዐወቁ።

12 እኔም “ብትፈቅዱ ደመወዜን ስጡኝ፤ ባትፈቅዱ ተዉት” አልኳቸው፤ እነርሱም የአገልግሎቴን ዋጋ ሠላሳ ብር ሰጡኝ።

13 እግዚአብሔርም “በቤተ መቅደስ የገንዘብ መቀበያ ሣጥን ውስጥ ጣለው” አለኝ። ስለዚህም ለእኔ “በቂ ደመወዝ ነው” ብለው የሰጡኝን ሠላሳ ብር ወስጄ በሸክላ ሠሪው ገንቦ ውስጥ ጣልኩት።

14 ከዚህ በኋላ “አንድነት” የተባለውን ሁለተኛውን በትር ሰበርኩት፤ ይህንንም ማድረጌ በይሁዳና በእስራኤል መካከል የነበረው ወንድማማችነት መጥፋቱን ለማመልከት ነበር።

15 ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “አሁንም እንደገና ራስህን እንደ ዋጋቢስ እረኛ አድርግ፤

16 እነሆ በምድሪቱ መንጋዬን የሚጠብቅ አንድ እረኛ አስነሣለሁ፤ ይህን በማድረግ ፈንታ እርሱ ስለ ጠፉት አያስብም፤ የባዘኑትን አይፈልግም፤ ያነከሱትን አይፈውስም፤ ጤናማዎችንም አይመግብም፤ ይህን በማድረግ ፈንታ የወፈረውን እያረደ ይበላል፤ ሰኮናቸውንም ይቈራርጣል።

17 መንጋውን ለከዳ ለእንዲህ ዐይነቱ ዋጋቢስ እረኛ ወዮለት! ክንዱና ቀኝ ዐይኑ በሰይፍ ይመታ፤ ክንዱ በፍጹም ይድረቅ፤ ቀኝ ዐይኑም ጨርሶ ይጥፋ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告