Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘካርያስ 10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ሕዝቡን ለመታደግ እግዚአብሔር የሰጠው ተስፋ

1 እግዚአብሔር በበልግ ወራት ዝናብ እንዲሰጣችሁ ለምኑት፤ ዝናብ ያዘለ ደመናን የሚልክ እግዚአብሔር ነው፤ ዝናብንና የመስክ አትክልትን ለሁሉም የሚሰጥ እርሱ ነው።

2 ጣዖቶች ዋጋቢስ ነገርን ይናገራሉ፤ ጠንቋዮችም ሐሰተኛ ራእይን ያያሉ፤ የማጭበርበሪያ ሕልምንም ይናገራሉ፤ ስለዚህ ሕዝቡ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች ይባዝናሉ፤ ማጽናናታቸው ከንቱ ነው፤ ከንቱ የማጽናናት ቃል ይሰጣሉ።

3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ኀይለኛ ቊጣዬ በሕዝቤ መሪዎች ላይ ይወርዳል፤ እኔ የሠራዊት አምላክ ለመንጋዬ ለይሁዳ ሕዝብ ስለምጠነቀቅ መሪዎቻቸውን እቀጣለሁ፤ የይሁዳንም ሕዝብ እንደ ኲሩ የጦር ፈረሴ አደርጋቸዋለሁ።

4 ከይሁዳ ሕዝብ እንደ ማእዘን ድንጋይ፥ እንደ ድንኳን ካስማ፥ እንደ ጦርነት ቀስት ያሉ መሪዎችና የጦር አዛዦች ይወጣሉ።

5 የይሁዳ ሕዝብ ጠላቶቻቸውን ረግጠው ከመንገድ ጭቃ ጋር እንደሚለውሱ እንደ ብርቱ ጦረኞች ይሆናሉ፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ስለ ሆነ በርትተው በመዋጋት ፈረሰኞችን ሳይቀር ድል ይነሣሉ።

6 “እኔ የይሁዳን ሕዝብ ብርቱ አደርጋለሁ፤ የእስራኤልንም ሕዝብ እታደጋለሁ፤ ስለምራራላቸውም ሁሉንም ወደ አገራቸው እመልሳለሁ፤ ከዚህ በፊት ከቶ ጥዬአቸው እንደማላውቅ ይሆናሉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ስለ ሆንኩ ጸሎታቸውን እሰማለሁ።

7 የእስራኤል ሕዝብ እንደ ብርቱ ጦረኞች ይሆናሉ፤ የወይን ጠጅ እንደ ጠጣ ሰውም ደስተኞች ይሆናሉ፤ ልጆቻቸውም ይህን ድል በማስታወስ ደስ ይላቸዋል፤ በእግዚአብሔርም ሐሤት ያደርጋሉ።

8 “ሕዝቤን በጥቅሻ ጠርቼ በአንድነት እሰበስባቸዋለሁ፤ እታደጋቸዋለሁም፤ ከዚህ በፊት እንደ ነበሩትም ቊጥራቸውን አበዛዋለሁ።

9 በሕዝቦች መካከል ብበትናቸውም እንኳ፥ በሚኖሩባቸው ሩቅ አገሮች ሆነው ያስታውሱኛል፤ እነርሱና ልጆቻቸው ተርፈው ወደ አገራቸው ይመለሳሉ።

10 ከግብጽ ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ ከአሦር እሰበስባቸዋለሁ፤ ቦታ እስኪጠባቸው ድረስ በገለዓድና በሊባኖስም ጭምር አሰፍራቸዋለሁ።

11 በመከራ ባሕር ውስጥ ሲያልፉ እኔ እግዚአብሔር ማዕበሉን እመታለሁ፤ ጥልቅ የሆነውም የዓባይ ወንዝ ይደርቃል፤ ትዕቢተኛይቱ አሦር ትዋረዳለች፤ ግብጽም በትረ መንግሥትዋን ታጣለች።

12 እኔ አምላካቸው አበረታቸዋለሁ እነርሱም ለቃሌ ይታዘዛሉ።” እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告