ማሕልየ መሓልይ 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ምነው አንተ የእናቴን ጡት እንደ ጠባ እንደ ወንድሜ በሆንክልኝ፤ በመንገድ ላይ አግኝቼ ብስምህ ማንም ሰው አይንቀኝም ነበር፤ 2 ወደ ወላጅ እናቴ ቤት ባስገባሁህ ነበር፤ በዚያም ስለ ፍቅር ባስተማርከኝ ነበር፤ በሮማን ፍሬዬ ጭማቂ የጣፈጠውን መልካሙን የወይን ጠጅ ባጠጣሁህ ነበር። 3 ግራ እጁን ያንተርሰኛል፤ በቀኝ እጁ ያቅፈኛል። 4 እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅ ሆይ! ፍቅር ራሱ ወዶ እስኪነሣ ድረስ ቀስቅሳችሁ እንዳታስነሡት ዐደራ እላችኋለሁ። ሰባተኛ መዝሙር የፍቅር ውዳሴ የሙሽራይቱ ጓደኞች 5 በወዳጅዋ ትከሻ ላይ ደገፍ ብላ ከበረሓ የምትመጣ ይህች ማን ናት? ዱሮ እናትህ አንተን አምጣ በወለደችበት በፖም ዛፍ ሥር ቀስቅሼ አስነሣሁህ። ሙሽራይቱ 6 በዘለዓለማዊ ፍቅር በልብህ ውስጥ እንደ ማኅተም አትመኝ፤ በክንድህም እንደ ማኅተም እኔን ብቻ ያዘኝ፤ ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናት፤ ቅናትም እንደ መቃብር የከፋች ናት፤ የእሳትዋ ወላፈን እንደ እግዚአብሔር ወላፈን ነው። 7 የውሃ ብዛት የፍቅርን እሳት ሊያጠፋ አይችልም፤ ጐርፍም ጠራርጎ ሊወስዳት አይችልም፤ ሰው ባለው ሀብት ሁሉ ፍቅርን ለመግዛት ቢሞክር ፍቅር በገንዘብ ስለማትገኝ ሰዎች ይዘባበቱበታል። የሙሽራይቱ ወንድሞች 8 ገና ጡት ያላወጣች ትንሽ እኅት አለችን፤ ለጋብቻ ብትጠየቅ ለዚህች ለእኅታችን የምናደርግላት ምንድን ነው? 9 እርስዋ ቅጽር ብትሆን ኖሮ የብር ማማ እንሠራላት ነበር፤ እርስዋ የቅጽር በር ብትሆን ኖሮ ከሊባኖስ ዛፍ ሳንቃ የታነጸ መዝጊያ እንሠራላት ነበር። ሙሽራይቱ 10 እነሆ፥ እኔ ቅጽር ነኝ፤ ጡቶቼም እንደ ቅጽር ማማዎች ናቸው፤ ከውዴ ጋር ስሆን እርሱ ደስታንና ሰላምን ያገኛል። የሙሽራይቱ ጓደኞች 11 ሰሎሞን በባዓልሃሞን የወይን ተክል ቦታ ነበረው፤ የወይኑንም ተክል ቦታ ለአትክልተኞች አከራየው፤ እያንዳንዳቸውም አንድ ሺህ ብር ያመጡለት ነበር፤ ሙሽራይቱ 12 እኔ የግሌ የሆነ የወይን ተክል ቦታ አለኝ፤ ሰሎሞን ሆይ! አንተ አንድ ሺህ ብር፥ አትክልተኞቹ ሁለት መቶ ብር ልትወስዱ ትችላላችሁ። ሙሽራው 13 አንቺ የእኔ ሙሽራ ሆይ! በአትክልት ቦታ ሆነሽ ጓደኞቼ ድምፅሽን ለመስማት ይፈልጋሉ፤ እስቲ ለእኔ ድምፅሽን አሰሚኝ። ሙሽራይቱ 14 ውዴ ሆይ! ፈጥነህ ወደ እኔ ና፤ የቅመም ተክሎች በሚበቅሉባቸው ተራራዎች ላይ የሚዘል አጋዘን ወይም የዋልያ ግልገል ምሰል። |