ማሕልየ መሓልይ 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሙሽራው 1 ልዕልት ሆይ! እግሮችሽ በነጠላ ጫማ ውስጥ ሲታዩ እንዴት ያምራሉ! ዳሌዎችሽ በብልኅ አንጥረኛ እጅ የተሠራ የዕንቊ ጌጥ ይመስላሉ፤ 2 እንብርትሽ በወይን ጠጅ የተሞላ ብርሌ ይመስላል፤ ወገብሽ ዙሪያውን በውብ አበባ የታሰረ የስንዴ ነዶ ይመስላል። 3 ሁለቱ ጡቶችሽ መንታ የዋልያ ግልገሎችን ይመስላሉ። 4 አንገትሽ በዝሆን ጥርስ እንዳጌጠ ግንብ ነው፤ ዐይኖችሽ በታላቅዋ ከተማ በሐሴቦን የቅጽር በር አጠገብ የሚገኙ የውሃ ኲሬዎችን ይመስላሉ። አፍንጫሽ ወደ ደማስቆ አቅጣጫ ለመመልከት የተሠራውን የሊባኖስ ግንብ ይመስላል። 5 የራስሽ ቅርጽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ ነው፤ ዞማው ጠጒርሽም የሐር ጒንጒን የመሰለ ነው። ንጉሡም በሹሩባሽ ውበት ተማርኮአል። 6 ውዴ ሆይ! እንዴት ያማርሽ ነሽ? እንዴትስ ውብ ነሽ? ፍቅርሽ እንዴት ያስደስታል? የጋራ ፍቅራችን 7 ቁመናሽ የዘንባባ ዛፍ ይመስላል፤ ጡቶችሽም ዘለላውን ይመስላሉ። 8 በዘንባባው ዛፍ ላይ ወጥቼ ፍሬውን መልቀም እወዳለሁ፤ ጡቶችሽ እንደ ወይን ዘለላ ዕቅፍ ይሁኑ፤ የእስትንፋስሽ መዓዛ እንደ ፖም ፍሬ ሽታ ነው። 9 የአፍሽም መዓዛ እንደ መልካም ወይን ጠጅ ነው። እንግዲያውስ መልካሙ የወይን ጠጅ በውዴ ከንፈሮችና ጥርሶች መካከል እየተንቆረቆረ በዝግታ ይውረድ። ሙሽራይቱ 10 እኔ የውዴ ነኝ፤ የእርሱም ምኞት ወደ እኔ ነው። 11 ውዴ ሆይ! ና፤ ከከተማ ወጥተን ወደ ገጠር እንሂድ፤ ሌሊቱን በዚያ እናሳልፍ። 12 ማልደንም ወደ ወይኑ ተክል ቦታ እንሂድ፤ የወይኑ አበባ ፈክቶ እንደ ሆነ፥ ሮማኑም አብቦ እንደ ሆነ እንይ፤ በዚያም ፍቅሬን እገልጥልሃለሁ። 13 የእንኰይ ፍሬ መዓዛና እንዲሁም ደስ የሚያሰኙ ልዩ ልዩ ፍራፍሬዎች ደጃችንን ሞልተውታል። ውዴ ሆይ! ከነዚህም ፍሬዎች የበሰሉትንና አዲስ የተቀጠፉትን ለአንተ አኑሬልሃለሁ። |