ማሕልየ መሓልይ 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምአምስተኛ መዝሙር ፍቅር ከሁሉ ይመረጣል የሙሽራይቱ ጓደኞች 1 አንቺ ከሴቶች ሁሉ የተዋብሽ! ወዳጅሽ ወዴት ሄደ? እኛም አብረንሽ እንድንፈልገው የሄደበትን አቅጣጫ ንገሪን። ሙሽራይቱ 2 ውዴ የበጎቹን መንጋ ለማሰማራትና ውብ አበባን ለመቅጠፍ፥ የሽቶ ዕፀዋት ወደሚገኙበት የአትክልት ቦታው ወርዶአል። 3 ውዴ የእኔ ነው፤ እኔም የእርሱ ነኝ፤ በሱፍ አበባዎች መካከል መንጋውን ያሰማራል። ሙሽራው 4 ፍቅሬ ሆይ! እንደ ቲርጻ ከተማ የተዋብሽ ነሽ፤ እንደ ኢየሩሳሌምም እጅግ ያማርሽ ነሽ፤ የጦር ዓርማ ይዞ እንደሚጓዝ ሠራዊት የሚያስፈራ ግርማ አለሽ። 5 እባክሽ ዐይኖችሽን ከእኔ ላይ አንሺ፤ እነርሱ እኔን ማርከው እስረኛ አድርገውኛል። ጠጒርሽ ከገለዓድ ተራራ ላይ እንደሚወርድ የፍየል መንጋ ነው። 6 ጥርሶችሽ በመካከላቸው ምንም መኻን ሳይኖርባቸው መንታ መንታ እንደሚወልዱና በውሃ እንደ ታጠቡ ነጫጭ የበጎች መንጋ ደስ ያሰኛሉ። 7 ሁለቱ ጒንጮችሽ በፊትሽ ዐይነ ርግብ ውስጥ ሲታዩ ለሁለት የተከፈሉ የሮማን ፍሬ ፍንካች ይመስላሉ። 8 ሥልሳ ንግሥቶች፥ ሰማኒያ ቊባቶችና ከቊጥር በላይ የሆኑ ቈነጃጅት አሉ፤ 9 እኔ ግን የምወደው አንዲትዋን ብቻ ነው፤ እርስዋም ምንም እንከን የሌለባት እንደ ርግብ የተዋበች ናት፤ እርስዋ ለእናትዋ አንድ ናት፤ የወለደቻት እናትዋም ከሁሉ አብልጣ ታፈቅራታለች፤ ቈነጃጅትም እርስዋን እየተመለከቱ ያወድሱአታል፤ ነገሥታትና የንጉሥ ቊባቶች ያሞግሡአታል። 10 ይህች እንደ ብርሃን የምትፈልቅ፥ እንደ ጨረቃ የምትደምቅ፥ እንደ ፀሐይ የምታበራ፥ የጦር ዓርማ ይዞ እንደሚጓዝ ሠራዊት ግርማዋ የሚያስፈራ፥ እርስዋ ማን ናት? 11 በሸለቆ የተተከሉትን ተክሎች ልምላሜ አይ ዘንድ ወይኑ አቈጥቊጦ፥ ሮማኑም አብቦ እንደ ሆነ ልመለከት ወደ ለውዝ ተክል ቦታ ወረድኩ፤ 12 ሳላስበው፥ ምኞቴ በሠረገላ ላይ እንደ ልዑል አስቀመጠኝ። የሙሽራው ጓደኞች 13 አንቺ ሱላማዊት ሆይ! ነዪ ተመለሺ፤ በደንብ አድርገን እንድንመለከትሽ ነዪ ተመለሺ። ሱላማጢስን በሁለት ሠራዊት መካከል እንደሚደረግ ጭፈራ የምትመለከቱአት ለምንድን ነው? |