ማሕልየ መሓልይ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሙሽራው 1 ፍቅሬ ሆይ! እንዴት ውብ ነሽ! እንዴት ያማርሽ ነሽ! ዐይኖችሽ በፊትሽ መሸፈኛ ዐይነ ርግብ ውስጥ ሲታዩ እንደ ርግብ ያማሩ ናቸው፤ ጠጒርሽ ከገለዓድ ተራራ ላይ እንደሚወርድ የፍየል መንጋ ነው። 2 ጥርሶችሽ፥ በመካከላቸው ምንም መኻን ሳይኖርባቸው መንታ መንታ እንደሚወልዱ፥ ተሸልተው በውሃ እንደ ታጠቡ፥ ነጫጭ የበጎች መንጋ ደስ ያሰኛሉ። 3 ከንፈሮችሽ እንደ ቀይ ሐር ፈትል ያማሩ ናቸው፤ ስትነጋገሪም እጅግ ደስ ያሰኛሉ፤ ሁለቱ ጒንጮችሽ በፊትሽ መሸፈኛ ዐይነ ርግብ ውስጥ ሲታዩ ለሁለት የተከፈለ የሮማን ፍንካች ይመስላሉ። 4 አንገትሽ በሺህ የሚቈጠሩ የኀያላን ጋሻዎችና የጦር ዕቃዎች ተሰቅለው የሚታዩበትን፥ የጦር ምሽግ ይሆን ዘንድ የተሠራውን የዳዊትን ግንብ ይመስላል። 5 ሁለቱ ጡቶችሽ መንታ ሆነው የተወለዱና በሱፍ አበባዎች መካከል የተሰማሩ የዋልያ ግልገሎችን ይመስላሉ። አራተኛ መዝሙር የጋብቻ ኅብረት 6 ሌሊቱ እስከሚነጋና ጨለማውም እስከሚያልፍ ድረስ ወደ ከርቤ ተራራና ወደ ዕጣን ኮረብታ ሄጄ ዐርፋለሁ። 7 ፍቅሬ ሆይ! ሁለንተናሽ ውብ ነው፤ ምንም እንከን የለብሽም። 8 ሙሽራዬ ሆይ! ከሊባኖስ ወደ እኔ ነይ፤ ከሊባኖስ ወደ እኔ ነይ፤ ከአማና ተራራ ጫፍ ውረጂ፤ የአንበሳና የነብር መኖሪያ ከሆኑት ከሠኒርና ከሔርሞን ተራራዎች ወርደሽ ነይ 9 ውድ እኅቴ የሆንሽ ሙሽራዬ ሆይ፥ የዐይኖችሽ አመለካከትና የአንገትሽ ድሪ ልቤን ማርኮታል፤ 10 ውድ እኅቴ የሆንሽ ሙሽራዬ ሆይ፥ ፍቅርሽ እንዴት ያስደስታል! ፍቅርሽ ከወይን ጠጅ ይልቅ ደስ ያሰኛል፤ የሽቶሽ መዓዛ ከማንኛውም ሽቶ ይበልጣል። 11 ሙሽራዬ ሆይ! ከከንፈሮችሽ የማር ወለላ ይፈስሳል፤ ከአንደበትሽም ማርና ወተት ይፈልቃል፤ የልብስሽም መዓዛ እንደ ሊባኖስ ሽቱ ነው። 12 አንቺ የእኔ ሙሽራ፥ እንደ አትክልት ቦታና ለሌሎች እንደ ተዘጋ ምንጭ ነሽ። 13 የአንቺ መተላለፊያ በጣፋጭ ፍሬዎች እንደ ተሞላ እንደ ሮማን የአትክልት ቦታ ነው። 14 ናርዶስ፥ ቀጋ፥ ጠጅ ሣርና ቀረፋ፥ እንዲሁም ሽታቸው እንደ ዕጣን መዓዛ ያላቸው ልዩ ልዩ ተክሎች ይገኙባታል፤ እንዲሁም ከርቤ፥ የሬት አበባና ልዩ ልዩ የቅመማቅመም ተክሎች ይበቅሉባታል። 15 አንቺ የአትክልት ቦታን እንደምታጠጣ ምንጭ ነሽ፤ የሕይወት ውሃም እንደሚገኝባት ጒድጓድ ነሽ፤ ከሊባኖስ ተራራ ሥር እንደሚፈልቅ ወንዝ ነሽ። ሙሽራይቱ 16 የሰሜን ነፋስ ሆይ! ንቃ! አንተም የደቡብ ነፋስ ሆይ! ወደዚህ ና! በአትክልት ቦታዬም ላይ ንፈስ፤ ዐየሩም በመልካም ሽታ የተሞላ ይሁን፤ ውዴም ወደ አትክልት ቦታው ይምጣ፤ ምርጥ የሆኑትንም ፍሬዎች ይመገብ። |