ማሕልየ መሓልይ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 እኔ እንደ ሳሮን ጽጌረዳና በሸለቆ ውስጥ እንደሚበቅል የሱፍ አበባ ነኝ። ሙሽራው 2 ውዴ በሴቶች መካከል ስትታይ በእሾኽ መካከል እንደሚታይ የሱፍ አበባ ናት። ሙሽራይቱ 3 ውዴ ከሌሎች ጐልማሶች ጋር ሲነጻጸር በዱር ዛፎች መካከል አምሮ እንደሚታይ የፖም ዛፍ ነው፤ እኔም እጅግ ደስ ብሎኝ በጥላው ሥር ዐረፍኩ፤ ጣፋጭ ፍሬውንም በመመገብ ተደሰትኩ። 4 ወደ ምግብ አዳራሹ አስገባኝ፤ ፍቅሩንም እንደ ሰንደቅ ዓላማ በእኔ ላይ ከፍ ከፍ አደረገ። 5 እኔ በፍቅሩ ተይዤ ስለ ታመምኩ ዘቢብ እየመገባችሁ አበረታቱኝ፤ በፖም ፍሬም አስደስቱኝ። 6 ግራ እጁን ያንተርሰኛል፤ በቀኝ እጁም ያቅፈኛል። 7 እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ! ፍቅር ራሱ ፈቅዶ እስኪነሣ ድረስ ቀስቅሳችሁ እንዳታስነሡት፤ በፈጣን አጋዘንና በምድረ በዳ ዋልያ ስም ዐደራ እላችኋለሁ። ሁለተኛ መዝሙር ፍቅር ሁሉንም ነገር ውብ ያደርጋል ሙሽራይቱ 8 ውዴ በተራሮችና በኮረብቶች ላይ እየዘለለና እየተወረወረ ሲመጣ ድምፁ ይሰማል። 9 ውዴ፥ ዋልያ ወይም የአጋዘን ግልገል ይመስላል፤ እነሆም ከቤታችን ቅጽር አጠገብ ቆሞአል፤ በመስኮትም ወደ ውስጥ ይመለከታል፤ በዐይነ ርግቡ ቀዳዳ በኩል አሾልኮ ይቃኛል። 10 ውዴ እንዲህ ይለኛል፥ ውዴ ሆይ! ተነሺ፤ የእኔ ውብ ሆይ! ነይ አብረን እንሂድ፤ ሙሽራው 11 እነሆ፥ ክረምቱ አልፎአል፤ ዝናቡም ቆሞአል፤ 12 በየመስኩ አበባዎች መታየት ጀምረዋል፤ የዜማ ወራት ደርሶአል፤ የርግቦችም ዜማ በምድራችን ይሰማል። 13 በለስ ማፍራት ጀምሮአል፤ የወይን ተክልም አብቦአል፤ የአበባውም ሽታ ምድርን ሞልቶታል፤ ስለዚህ ውዴ ሆይ! ተነሺ፤ የእኔ ውብ ሆይ! ነይ አብረን እንሂድ። 14 አንቺ በገደል አለት ንቃቃት ውስጥ እንደ ተደበቀች ርግብ ነሽ፤ እስቲ አንድ ጊዜ ፊትሽን ልየው፤ ድምፅሽንም ልስማው፤ ድምፅሽ አስደሳች ነው፤ ፊትሽም እጅግ የተዋበ ነው። የሙሽራይቱ ወንድሞች 15 ወይናችን አብቦአል፤ ስለዚህ የወይን ተክላችንን እንዳያጠፉብን ቀበሮዎችን፥ እነኛን ትናንሽ ቀበሮዎችን አጥምዳችሁ ያዙልን። ሙሽራይቱ 16 ውዴ የእኔ ነው፤ እኔም የእርሱ ነኝ፤ በአሸንድዬ አበባዎች መካከል መንጋውን ያሰማራል። 17 የሌሊቱ ጨለማ እስከሚወገድ፤ የማለዳው ነፋስ እስከሚነፍስ፤ ውዴ ሆይ! እንደ ዋልያ ወይም እንደ አጋዘን ግልገል በገደላማ ተራራዎች ላይ እየሮጥክ ተመለስ። |