ራእይ 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምአዲሱ ሰማይና አዲሲቱ ምድር 1 ከዚህ በኋላ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የመጀመሪያው ሰማይና የመጀመሪያይቱ ምድር አልፈው ነበር፤ ባሕርም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። 2 ቅድስቲቱ ከተማ፥ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንዳጌጠች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ፤ 3 እንዲህም የሚል ከፍተኛ ድምፅ ከዙፋኑ ሲወጣ ሰማሁ፤ “እነሆ! የእግዚአብሔር ማደሪያ ከሰዎች ጋር ነው፤ ከእነርሱም ጋር ይኖራል፤ እነርሱም የእርሱ ሕዝብ ይሆናሉ። እግዚአብሔር ራሱ ከእነርሱ ጋር ይሆናል፤ አምላካቸውም ይሆናል፤ 4 እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ላይ ይጠርጋል፤ የቀድሞው ሥርዓት ስላለፈ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ለቅሶ ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።” 5 በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም “እነሆ! እኔ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ!” አለ፤ ቀጥሎም “ይህ ቃል የታመነና እውነት ስለ ሆነ ጻፍ” አለኝ። 6 ከዚህም በኋላ እንዲህ አለኝ፤ “ተፈጸመ! አልፋና ዖሜጋ፥ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እኔ ነኝ፤ ለተጠማ ከሕይወት ውሃ ምንጭ ያለ ምንም ዋጋ በነጻ እሰጠዋለሁ፤ 7 ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል፤ እኔ አምላክ እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል፤ 8 ነገር ግን ፈሪዎች፥ እምነተ ቢሶች፥ ርኩሶች፥ ነፍሰ ገዳዮች፥ አመንዝሮች፥ አስማተኞች፥ ጣዖት አምላኪዎች፥ ውሸታሞች ሁሉ ዕጣ ክፍላቸው በዲን በሚቃጠለው በእሳት ባሕር ውስጥ ይሆናል፤ ይህም ሁለተኛው ሞት ነው።” አዲሲቱ ኢየሩሳሌም 9 የመጨረሻዎቹ ሰባት መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ “ና! የበጉ ሚስት የሆነችውን ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ” አለኝ። 10 በመንፈስም ወደ አንድ ትልቅ ረጅም ተራራ ወሰደኝና ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ ስትወርድ አሳየኝ፤ 11 በእግዚአብሔር ክብር ታበራ ነበር፤ የብርሃንዋም ድምቀት እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ፥ እንደ ብርሌ የጠራ የእያሰጲድ ዕንቊ ነበረ፤ 12 ዐሥራ ሁለት ደጃፎች ያሉት ታላቅና ረጅም የግንብ አጥር ነበራት፤ በዐሥራ ሁለቱም ደጃፎች ዐሥራ ሁለት መላእክት ቆመው ይጠብቁ ነበር፤ በደጃፎቹም ላይ የዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር። 13 በምሥራቅ ሦስት ደጃፎች በሰሜን ሦስት ደጃፎች፥ በደቡብ ሦስት ደጃፎች፥ በምዕራብ ሦስት ደጃፎች ነበሩ። 14 የከተማይቱ የግንብ አጥር ዐሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩት፤ በመሠረቶቹም ላይ የዐሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር፤ 15 የተናገረኝም መልአክ ከተማይቱንና ደጃፎችዋን፥ የግንቡንም አጥር የሚለካበት የወርቅ ዘንግ ነበረው፤ 16 ከተማይቱም ርዝመትዋና ስፋትዋ እኩል የሆነ የአራት ማእዘን ቅርጽ ነበራት፤ መልአኩ ከተማይቱን በመለኪያው ዘንግ ለካትና ርዝመትዋ ሁለት ሺህ አራት መቶ ኪሎ ሜትር ያኽል ሆነ፤ ስፋትዋና ከፍታዋም ያንኑ ያኽል ሆነ፤ 17 መልአኩ የግንቡን አጥር ለካ፤ መልአኩ በሚለካበት በታወቀው መለኪያ ልክ ሰባ ሁለት ሜትር ያኽል ሆነ፤ 18 ግንቡም የተሠራው ከኢያሰጲድ ነበረ፤ ከተማይቱም እንደ መስተዋት በጠራ በንጹሕ ወርቅ የተሠራች ነበረች፤ 19 የከተማይቱ ግንብ መሠረቶች በልዩ ልዩ የከበረ ድንጋይ ያጌጡ ነበሩ፤ የመጀመሪያው መሠረት ኢያሰጲድ ነበረ፤ ሁለተኛው ሰንፔር፥ ሦስተኛው ኬልቄዶን፥ አራተኛው መረግድ፥ 20 አምስተኛው ሰርዶንክስ፥ ስድስተኛው ሰርድዮን፥ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፥ ስምንተኛው ቢረሌ፥ ዘጠነኛው ወራውሬ፤ ዐሥረኛው ክርስጵራስስ፥ ዐሥራ አንደኛው ያክንት፥ ዐሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ። 21 ዐሥራ ሁለቱም ደጃፎች ዐሥራ ሁለት ዕንቆች ነበሩ፤ እያንዳንዱ ደጃፍ ከአንድ ዕንቊ የተሠራ ነበረ፤ የከተማይቱም መንገድ እንደ መስተዋት ብርሃን ከሚያስተላልፍ ከንጹሕ ወርቅ የተሠራ ነበረ። 22 ሁሉን የሚችል ጌታ አምላክና በጉ የእርስዋ መቅደስ ስለ ሆኑ በከተማይቱ ውስጥ መቅደስ አላየሁም፤ 23 የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላትና በጉ መብራትዋ ስለ ሆነ ከተማይቱ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጋትም። 24 ሕዝቦች በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፤ የምድር ነገሥታትም ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ፤ 25 በዚያች ከተማ ሌሊት ስለሌለ ደጃፎችዋ በማንኛውም ቀን አይዘጉም። 26 የመንግሥታት ገናናነትና ክብር ወደ እርስዋ ይገባሉ፤ 27 ጸያፍ የሆነ ነገር ከቶ ወደ እርስዋ አይገባም፤ ርኲሰትን የሚያደርግና ውሸት የሚናገር ከቶ ወደ እርስዋ አይገባም፤ ወደ እርስዋ የሚገቡ ስሞቻቸው በበጉ የሕይወት መጽሐፍ የተጻፉ ብቻ ናቸው። |