ራእይ 19 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ከዚህ በኋላ እንዲህ የሚል የብዙ ሰዎችን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ በሰማይ ሰማሁ “ሃሌ ሉያ! ማዳንና ክብር ኀይልም የአምላካችን ነው! 2 ፍርዱ እውነትና ትክክል ነው፤ ምድርን በአመንዝራነትዋ ያረከሰችውን ታላቂቱን አመንዝራ በፍርድ ቀጥቶአታል፤ እርስዋን በመቅጣትም የአገልጋዮቹን ደም ተበቅሎአል።” 3 እንደገናም፥ “ሃሌ ሉያ! ከእርስዋ የሚነሣው ጢስ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ወደ ላይ ይወጣል!” እያሉ ጮኹ። 4 ኻያ አራቱ ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶች በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው አምላክ በግንባራቸው ተደፍተው “አሜን፥ ሃሌ ሉያ!” እያሉ ሰገዱ። የበጉ ሠርግ ግብዣ 5 ከዚህ በኋላ “እርሱን የምትፈሩ አገልጋዮቹ ሁሉ፥ ታናናሾችም ታላላቆችም አምላካችንን አመስግኑ!” የሚል ድምፅ ከዙፋኑ ወጣ። 6 የብዙ ሰዎችን ድምፅ የወራጅ ውሃን ድምፅ፥ የብርቱ ነጐድጓድንም ድምፅ፥ የሚመስል ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ሃሌ ሉያ! ሁሉን የሚችል ጌታ አምላካችን ይነግሣል! 7 የበጉ ሠርግ ስለ ደረሰና የእርሱም ሙሽራ ስለ ተዘጋጀች ኑ ደስ ይበለን! ደስታም እናድርግ! እናክብረውም! 8 የሚያንጸባርቅና ንጹሕ የሆነ ውብ ልብስ እንድትለብስ ተሰጣት፤ ቀጭኑ ልብስ የቅዱሳን የጽድቅ ሥራ ነው።” 9 ከዚህ በኋላ መልአኩ “ወደ በጉ ሠርግ ግብዣ የተጠሩ የተባረኩ ናቸው” ብለህ ጻፍ አለኝ፤ ቀጥሎም “ይህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃል ነው” አለ። 10 እኔም ለመልአኩ ልሰግድለት በእግሩ ሥር በግንባሬ ተደፋሁ፤ እርሱ ግን “ተው! ይህን አታድርግ! እኔም ከአንተና የኢየሱስን ምስክርነት ከያዙት ወንድሞችህ ጋር አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ! የኢየሱስ ምስክርነት የትንቢት መንፈስ ነው” አለኝ። በነጩ ፈረስ ላይ የተቀመጠ ፈረሰኛ 11 ከዚህ በኋላ ሰማይ ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆ፥ ነጭ ፈረስም አየሁ፤ በፈረሱ ላይ የተቀመጠው ታማኝና እውነተኛ የሚባል ነው፤ እርሱ በትክክል ይፈርዳል፤ ይዋጋልም፤ 12 ዐይኖቹ የእሳት ነበልባል ይመስላሉ፤ በራሱም ላይ ብዙ ዘውዶች አሉ፤ ከእርሱ በቀር ሌላ ማንም የማያውቀው በእርሱ ላይ የተጻፈ ስም ነበረ፤ 13 እርሱ በደም የተነከረ ልብስ ለብሶ ነበር፤ ስሙም “የእግዚአብሔር ቃል” የሚባል ነው። 14 በነጫጭ ፈረሶች ላይ የተቀመጡ፥ ነጭና ንጹሕ የሆነ ውብ ልብስ የለበሱ የሰማይ ሠራዊት ተከትለውታል፤ 15 ሕዝቦችን የሚመታበት ስለታም ሰይፍ ከአፉ ይወጣል፤ በብረት በትርም ይገዛቸዋል፤ እርሱ ሁሉን የሚችለውን የእግዚአብሔር አስፈሪ ቊጣ መግለጫ የሆነውን የወይን ጠጅ መጭመቂያ ይረግጣል፤ 16 በልብሱና በጭኑ ላይ “የነገሥታት ንጉሥ፥ የጌቶች ጌታ” የሚል ስም ተጽፎአል። 17 ከዚህ በኋላ በፀሐይ ላይ የቆመ አንድ መልአክ አየሁ፤ እርሱ በሰማይ ለሚበርሩ ወፎች እንዲህ ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ “ወደ ታላቁ የእግዚአብሔር ግብዣ ኑ! ተሰብሰቡ! 18 የነገሥታትን ሥጋ፥ የጦር አዛዦችን ሥጋ፥ የብርቱ ጦረኞችን ሥጋ፥ የፈረሶችንና የፈረሰኞችን ሥጋ፥ የጌቶችንና የአገልጋዮችን ሥጋ፥ የታናናሾችንና የታላላቆችን ሥጋ፥ የማንኛውንም ሰው ሁሉ ሥጋ ኑ ብሉ!” 19 እንዲሁም አውሬውና የምድር ነገሥታት፥ ወታደሮቻቸውም በነጩ ፈረስ ላይ ከተቀመጠውና ከሠራዊቱ ጋር ለመዋጋት ተሰብስበው አየሁ፤ 20 ነገር ግን አውሬው ተያዘ፤ ከእርሱም ጋር በፊቱ ብዙ ተአምራት ያደርግ የነበረው ሐሰተኛው ነቢይ ተያዘ፤ እርሱ የአውሬው ምልክት የነበረባቸውንና ለአውሬውም ምስል ይሰግዱ የነበሩትን ተአምራት እያደረገ ያስታቸው ነበር፤ እነዚህ ሁለቱ በዲን ወደሚቃጠለው የእሳት ባሕር ከነሕይወታቸው ተጣሉ። 21 የቀሩት ደግሞ በነጩ ፈረስ ላይ ከተቀመጠው አፍ በሚወጣው ሰይፍ ተገደሉ፤ ወፎችም ሁሉ ሥጋቸውን በመብላት ጠገቡ። |