ራእይ 15 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየመጨረሻዎቹን መቅሠፍቶች የያዙ መላእክት 1 ሌላም ታላቅና ድንቅ ምልክት በሰማይ አየሁ፤ የእግዚአብሔር ቊጣ የሚፈጸምባቸውን የመጨረሻ የሆኑትን ሰባት መቅሠፍቶች የያዙትን ሰባት መላእክት አየሁ። 2 ከዚህ በኋላ እሳት የተቀላቀለበት የመስተዋት ባሕር የሚመስል ነገር አየሁ፤ እንዲሁም አውሬውንና የአውሬውን ምስል፥ የስሙንም ቊጥር ምልክት ድል የነሡትን አየሁ፤ እግዚአብሔር የሰጣቸውን በገና ይዘው በመስተዋቱ ባሕር አጠገብ ቁመው ነበር። 3 የእግዚአብሔርን አገልጋይ የሙሴን መዝሙርና የበጉን መዝሙር እንዲህ እያሉ ይዘምሩ ነበር፥ “ሁሉን የምትችል ጌታ አምላክ ሆይ! ሥራህ ታላቅና አስደናቂ ነው፤ የሕዝቦች ንጉሥ ሆይ! መንገድህ ትክክልና እውነት ነው፤ 4 ጌታ ሆይ! አንተን የማይፈራና ስምህንም የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህ፤ የእውነት ፍርድህ ስለ ተገለጠ፥ ሕዝቦች ሁሉ መጥተው በፊትህ ይሰግዳሉ።” 5 ከዚህም በኋላ ተመለከትኩ፤ እነሆ፥ የምስክር ድንኳን የሆነው ቤተ መቅደስ በሰማይ ተከፈተ፤ 6 ሰባቱን መቅሠፍቶች የያዙት ሰባቱ መላእክት ከቤተ መቅደሱ ወጡ፤ ንጹሕ የሚያንጸባርቅ ነጭ በፍታ ለብሰው ነበር፤ ደረታቸውንም በወርቅ መታጠቂያ ታጥቀው ነበር። 7 ከአራቱ እንስሶች አንዱ ለሰባቱ መላእክት ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የሚኖረው የእግዚአብሔር ቊጣ የመላባቸውን ሰባት የወርቅ ጽዋዎች ሰጣቸው። 8 ቤተ መቅደሱም ከእግዚአብሔር ክብርና ኀይል የተነሣ በጢስ ተሞላ፤ ሰባቱ መላእክት የያዙአቸው ሰባት መቅሠፍቶች እስከ ተፈጸሙ ድረስ ማንም ወደ ቤተ መቅደሱ መግባት አልቻለም። |