ራእይ 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሁለቱ አውሬዎች 1 ከዚህ በኋላ አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ ዐሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፤ በቀንዶቹም ላይ ዐሥር ዘውዶች ነበሩ፤ በራሶቹም ላይ የስድብ ስሞች ነበሩ። 2 ያየሁት አውሬ ነብር ይመስል ነበር፤ እግሮቹ የድብ እግሮች፥ አፉ የአንበሳ አፍ ይመስል ነበር። ዘንዶው የራሱን ኀይልና የራሱን ዙፋን ትልቅም ሥልጣን ለአውሬው ሰጠው። 3 ከአውሬው ራሶች አንዱ ለሞት የሚያደርስ ቊስል እንደ ነበረው ሆኖ አየሁት፤ ነገር ግን ለሞት የሚያደርሰው ቊስሉ ድኖአል፤ ዓለም በሙሉ በመደነቅ አውሬውን ተከተለ። 4 ለአውሬው ሥልጣን በመስጠቱ ሰዎች ሁሉ ለዘንዶው ሰገዱለት፤ “አውሬውን የሚመስል ማን ነው? ከእርሱስ ጋር ማን ሊዋጋ ይችላል?” እያሉ ለእርሱም ሰገዱለት። 5 የትዕቢትና የስድብ ቃል የሚናገርበት አፍ ለአውሬው ተሰጠው፤ አርባ ሁለት ወር በሥልጣን እንዲሠራም ተፈቀደለት። 6 እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን ስም፥ መኖሪያውንና በሰማይ የሚኖሩትን መሳደብ ጀመረ። 7 ቅዱሳንን እንዲዋጋና ድል እንዲነሣቸው ሥልጣን ተሰጠው፤ በነገድና በወገን፥ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች በሚናገሩና በሕዝብ ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። 8 ዓለም ሲፈጠር ጀምሮ ስሞቻቸው በታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፈ በዓለም ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ለአውሬው ይሰግዳሉ። 9 ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ! 10 “ለመማረክ የተመደበ ይማረካል፤ በሰይፍ ለመገደል የተመደበ በሰይፍ ይገደላል፤” እንግዲህ የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት የሚያስፈልገው በዚህ ጊዜ ነው። 11 ሌላ አውሬ ደግሞ ከምድር ሲወጣ አየሁ፤ እንደ በግ ሁለት ቀንዶች ነበሩት፤ አነጋገሩም እንደ ዘንዶው ነበር፤ 12 የመጀመሪያውን አውሬ ተክቶ በእርሱ ሥልጣን ይሠራ ነበር፤ ምድርና በእርስዋ ላይ የሚኖሩት ሁሉ ለመጀመሪያው አውሬው እንዲሰግዱ አደረገ፤ ይህም አውሬ ያ ለሞት የሚያደርስ ቊስል የዳነለት የመጀመሪያው አውሬ ነው። 13 ይህ ሁለተኛው አውሬ ግን በሰዎች ፊት እሳትን ከሰማይ እስከማውረድ ድረስ ታላላቅ ተአምራትን ያደርግ ነበር። 14 በመጀመሪያው አውሬ ፊት እንዲያደርግ በተፈቀደለት ተአምራት ምክንያት በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ያስት ነበር፤ በሰይፍ ቈስሎ ለዳነው ለአውሬው ክብር ምስል እንዲሠሩም በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ያዛቸዋል። 15 ሁለተኛው አውሬ ለመጀመሪያው አውሬ ምስል የሕይወት እስትንፋስ ለመስጠት ሥልጣን ተሰጠው፤ የሕይወት እስትንፋስ ለመስጠት ሥልጣን የተሰጠውም ምስሉ ለመናገር እንዲችልና ለእርሱ የማይሰግዱት ሁሉ እንዲገደሉ ያደርግ ዘንድ ነው። 16 ሁለተኛው አውሬ ታናናሾችም ሆኑ ታላላቆች፥ ሀብታሞችም ሆኑ ድኾች፥ ጌቶችም ሆኑ አገልጋዮች፥ ሁሉም በቀኝ እጃቸው ወይም በግንባራቸው ላይ ምልክት እንዲያደርጉ አስገደዳቸው። 17 በዚህ ዐይነት የአውሬውን ስም የሚያሳይ ምልክት ወይም የስሙ ቊጥር የሌለው ማንም ሰው መግዛትም ሆነ መሸጥ አይችልም። 18 ጥበብ የሚፈለገው እንግዲህ እዚህ ላይ ነው፤ አእምሮ ያለው የአውሬውን ቊጥር ያስላው፤ ቊጥሩ የሚያመለክተው ሰውን ነው፤ ቊጥሩም ስድስት መቶ ሥልሳ ስድስት ነው። |