አብድዩ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበኤዶም ላይ የሚደርስ ቅጣት 1 አብድዩ ያየው ራእይ፦ እግዚአብሔር አምላክ ኤዶምን በተመለከተ አብድዩን ልኮአል፤ የሰማነውም የእግዚአብሔር መልእክት፦ “እኔ እግዚአብሔር በኤዶም ላይ አደጋ እንዲጥሉ በማዘዝ ወደ ሕዝቦች መልእክተኛ ልኬአለሁ!” የሚል ነው። 2 እግዚአብሔር ኤዶምን እንዲህ ይላል፦ “እነሆ በአሕዛብ መካከል ደካማ አደርግሃለሁ፤ እጅግም የተናቅህ ትሆናለህ። 3 የልብህ ትዕቢት አታሎሃል፤ በጠንካራ አለት በተመሸገ ከተማ ውስጥ ትኖራለህ፤ የምታድርበትም ቤት በከፍተኞች ተራራዎች ላይ የተሠራ ነው፤ ‘ካለሁበት ስፍራ ማን ሊያወርደኝ ይችላል?’ በማለት ትመካለህ። 4 ነገር ግን እንደ ንስር ወደ ላይ ብትበር፥ መኖሪያህንም በከዋክብት መካከል ብታደርግ፥ ከዚያ አወርድሃለሁ። ይህን እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።” 5 “ሌቦች ወይም ቀማኞች በሌሊት ቢመጡ፥ የሚበቃቸውን ያኽል ብቻ ይወስዳሉ፤ የወይን ምርትንም የሚሰበስቡ ቃርሚያ ይተዋሉ፤ የአንተ ጠላቶች ግን ፈጽሞ ያጠፉሃል። 6 እናንተ የዔሳው ዘሮች ቤታችሁ ተበርብሯል፤ እነሆ ሀብታችሁ በሙሉ ተዘርፎአል። 7 የቃል ኪዳን ጓደኞችህ ሁሉ አታለሉህ፤ ከሀገርህም አስወጥተው አሳደዱህ፤ ወዳጆችህ በአንተ ላይ በጠላትነት ተነሡብህ፤ ያንተን እንጀራ የበሉ ወጥመድ ዘረጉብህ፤ ይህን ሁሉ ሲያደርጉብህ ግን አንተ አልደረስክበትም። 8 “በዚያን ጊዜ ከኤዶም ጥበበኞችን፥ ከዔሳው ተራራ ዕውቀትን አጠፋለሁ። 9 በኤዶም የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይገደላሉ፤ የቴማንም ጀገኖች በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ።” ኤዶም የሚቀጣበት ምክንያት 10 “የወንድምህን የያዕቆብን ዘሮች በግፍ ስለ ገደልክ፥ ትዋረዳለህ፤ ለዘለዓለምም ትጠፋለህ። 11 ጠላቶቻቸው በሮቻቸውን ሰባብረው፥ ሀብታቸውን ሁሉ በዘረፉበት ቀን፥ አንተ በዳር ቆመህ ትመለከት ነበር፤ አንተ እኮ ኢየሩሳሌምን በዕጣ ከተከፋፈሉአት ሰዎች በምንም አትሻልም። 12 በይሁዳ አገር በሚኖሩ ወንድሞችህ ላይ በደረሰው መከራ፥ ልትደሰት ባልተገባህም ነበር፤ በጥፋታቸው ቀን ሐሤት ልታደርግና በጭንቀታቸውም ቀን በእነርሱ ላይ ልትታበይ ባልተገባህም ነበር። 13 በችግራቸው ቀን ወደ ሕዝቤ በር ልትገባ ባልተገባህ ነበር፤ በመከራቸውም ቀን በይሁዳ ሕዝብ ጥፋት ለመደሰት መተባበር አይገባህም ነበር፤ በመጥፊያቸው ቀን የእነርሱን ንብረት መዝረፍ ባልተገባህም ነበር። 14 የሚሸሹትን ለመግደል በመስቀልኛ መንገድ ላይ ባላደባህባቸውም ነበር፤ የተረፉትንም በመከራቸው ቀን ለጠላት አሳልፈህ መስጠት ባልተገባህም ነበር።” የእግዚአብሔር ፍርድ በአሕዛብ ላይ 15 “እኔ እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ላይ የምፈርድበት ቀን ደርሶአል፤ ኤዶም ሆይ! እንደ ሥራህ ዋጋህን ታገኛለህ፤ የምትፈጽመው ክፉ ሥራ በራስህ ላይ ይመለሳል። 16 ሕዝቤ በተቀደሰው ተራራዬ ላይ የመከራ ጽዋ ጠጥተዋል፤ በዙሪያው ያሉት አሕዛብ ሁሉ ከዚህ የከፋ የመከራ ጽዋ ይጠጣሉ፤ የጠጡትም ሁሉ እንዳልነበሩ ይሆናሉ።” የእስራኤል ድል 17 “በጽዮን ተራራ ከጥፋት የሚያመልጡ ይገኛሉ፤ የጽዮን ተራራም የተቀደሰች ትሆናለች፤ የያዕቆብም ሕዝብ ተወስዶባቸው የነበረውን ንብረት መልሰው ይወስዳሉ። 18 የያዕቆብ ልጆች እንደ እሳት፥ የዮሴፍ ልጆች እንደ ነበልባል፥ የዔሳውም ልጆች እንደ ገለባ ይሆናሉ፤ እሳት ገለባን እንደሚያቃጥል የያዕቆብና የዮሴፍ ልጆች የዔሳውን ልጆች ያጠፋሉ። ይህንንም የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 19 “ከይሁዳ በስተደቡብ ያሉ ሕዝቦች የኤዶምን ምድር ይወርሳሉ፤ በምዕራብ ተራራዎች ግርጌ በሚገኘው ቆላማ ስፍራ የሚኖሩ ሕዝቦች የፍልስጥኤምን ምድር ይይዛሉ፤ የኤፍሬምንና የሰማርያንም ግዛት ይወስዳሉ፤ የብንያም ሰዎችም የገለዓድን ምድር ይወርሳሉ። 20 በስደት ላይ የነበሩት የሰሜን እስራኤል ሕዝብ ሖላ ከሚባል አገር ተመልሰው የከነዓንን ምድር እስከ ሰራጵታ ድረስ ይወርሳሉ፤ በሰፋራድም የሚኖሩ የኢየሩሳሌም ስደተኞች በስተ ደቡብ ያሉትን ከተሞች ይይዛሉ። 21 የዳኑት የኢየሩሳሌም ሰዎች በጽዮን ተራራ ላይ ሆነው ኤዶምን ይገዛሉ፤ መንግሥቱም የእግዚአብሔር ይሆናል።” |