Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

መሳፍንት 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


አቤሜሌክ

1 የጌዴዎን ልጅ አቤሜሌክ የእናቱ ዘመዶች ወደሚኖሩበት ወደ ሴኬም ከተማ ሄዶ ለእናቱ ወገኖች ሁሉ እንዲህ አላቸው፦

2 “ለሴኬም ሰዎች ሁሉ እንዲህ ብላችሁ ንገሩአቸው፦ ‘የጌዴዎን ሰባ ልጆች፥ ወይስ አንድ ሰው ብቻ ቢገዛችሁ ይሻላል? እኔ ደግሞ ለእናንተ የአጥንታችሁ ፍላጭ የሥጋችሁ ቊራጭ መሆኔን አስታውሱ።’ ”

3 የእናቱም ዘመዶች እርሱን ወክለው ይህንኑ ለሴኬም ሰዎች ነገሩአቸው፤ የሴኬም ሰዎችም እርሱ ወንድማችን ነው ብለው አቤሜሌክን የመከተል ፍላጎት አደረባቸው።

4 ከባዓልበሪት ቤት ሰባ ጥሬ ብር ወስደው ሰጡት፤ አቤሜሌክም በዚያ በሰባ ጥሬ ብር ዋልጌዎችንና ወሮበሎችን ቀጥሮ እንዲከተሉት አደረገ።

5 ወደ አባቱ ቤት ወደ ዖፍራም ሄዶ የጌዴዎን ልጆች የሆኑትን ሰባውን ወንድሞቹን በአንድ ድንጋይ ላይ ዐረዳቸው፤ የጌዴዎን መጨረሻ ልጅ ኢዮአታም ግን ተደብቆ ስለ ነበር ከሞት ተረፈ፤

6 ከዚያን በኋላ የሴኬምና የቤትሚሎ ሕዝብ በአንድነት ተሰብስበው፥ በሴኬም ወደሚገኘው ወደተቀደሰው ወርካ ዛፍ ሄዱ፤ በዚያም አቤሜሌክን አነገሡ።

7 ኢዮአታም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ወደ ገሪዛን ተራራ ጫፍ ላይ ወጥቶ እንዲህ በማለት ወደ እነርሱ ጮኸ፤ “እናንተ የሴኬም ሰዎች! እኔን ብታዳምጡኝ እግዚአብሔርም እናንተን ያዳምጣችኋል።

8 ከዕለታት አንድ ቀን ዛፎች ተሰብስበው በላያቸው ንጉሥ ሊያነግሡ ሄዱ፤ የወይራንም ዛፍ ‘በእኛ ላይ ንገሥ’ አሉት።

9 የወይራ ዛፍም ‘ለአማልክትና ለሰዎች ጠቃሚ የሆነውን ዘይቴን መስጠት ትቼ በዛፎች ላይ ልንገሥን?’ አላቸው።

10 ከዚህ በኋላ ዛፎቹ የበለስን ዛፍ ‘መጥተህ በእኛ ላይ ንገሥ’ አሉት።

11 የበለስ ዛፍ ግን ‘ጣፋጭና መልካም ፍሬዬን መስጠት ትቼ በዛፎች ላይ ለመንገሥ ልሂድን?’ አላቸው።

12 ስለዚህ ዛፎቹ የወይን ተክልን ‘መጥተህ በእኛ ላይ ንገሥ’ አሉት።

13 የወይን ተክሉ ግን ‘አማልክትንና ሰዎችን የሚያስደስተውን የወይን ጠጄን መስጠቴን አቁሜ በዛፎች ላይ ለመንገሥ ልሂድን?’ ሲል መለሰላቸው።

14 ስለዚህ ዛፎች ሁሉ የእሾኽ ቊጥቋጦን ‘መጥተህ በእኛ ላይ ንገሥ’ አሉት።

15 የእሾኽ ቊጥቋጦም ‘በእርግጥ ንጉሥ ልታደርጉኝ ከፈለጋችሁ፥ ኑና በጥላዬ ሥር ተጠለሉ፤ ይህን ባታደርጉ ከእሾኻማዎቹ ቅርንጫፎቼ እሳት ወጥቶ የሊባኖስ ዛፍን ያቃጥላል’ ሲል መለሰላቸው።”

16 ኢዮአታምም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አላቸው፤ “አቤሜሌክን ስታነግሡ በቅንነትና ተገቢ በሆነ መንገድ ነውን? ጌዴዎን ያደረገውን በማስታወስ ቤተሰቡን እንደሚገባ ረዳችሁለትን?

17 አባቴ ለእናንተ እንደ ተዋጋና እናንተንም ከምድያማውያን እጅ ለማዳን ሲል ሕይወቱን በአደጋ ላይ ጥሎ እንደ ነበረ አስታውሱ፤

18 ዛሬ ግን እናንተ በአባቴ ቤተሰብ ላይ በጠላትነት ተነሣችሁ፤ ልጆቹን ገደላችሁ፤ ሰባውንም በአንድ ድንጋይ ላይ ዐረዳችሁ፤ ይህንንም ያደረጋችኹት ጌዴዎን ከገረዱ የወለደው አቤሜሌክ የእናንተ ዘመድ ስለ ሆነ ነው፤ እርሱንም የሴኬም ንጉሥ አደረጋችሁት።

19 እንግዲህ ዛሬ ለጌዴዎንና ለቤተሰቡ ያደረጋችኹት በቅንነትና ተገቢ በሆነ መንገድ ከሆነ ከአቤሜሌክ ጋር ደስ ይበላችሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ደስ ይበለው፤

20 ይህ ካልሆነ ግን ከአቤሜሌክ እሳት ወጥቶ የሴኬምንና የቤትሚሎንን ሰዎች ይብላ፤ እንዲሁም ከሴኬምና ከቤትሚሎ እሳት ወጥቶ አቤሜሌክን ይብላ።”

21 ኢዮአታም ይህን ከተናገረ በኋላ ወንድሙን አቤሜሌክን ስለ ፈራ ሸሽቶ ወደ በኤር ሄዶ እዚያ ተቀመጠ።


አቤሜሌክና የሴኬም ሰዎች

22 አቤሜሌክም በእስራኤል ላይ ሦስት ዓመት ነገሠ፤

23 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በአቤሜሌክና በሴኬም ሰዎች መካከል ርኩስ መንፈስን ላከ፤ ስለዚህም የሴኬም ሰዎች በእርሱ ላይ ዐመፁበት።

24 ይህም የሆነው ወንድማቸው አቤሜሌክ የገደላቸውን የጌዴዎንን ሰባ ልጆች ደምና እነርሱንም እንዲገድል ያበረታቱትን የሴኬምን ሰዎች ለመበቀል ነው።

25 የሴኬም ኗሪዎች በአቤሜሌክ ላይ በጠላትነት ተነሥተው ጥቂት ሰዎችን መርጠው በተራሮች ጫፍ ላይ ሸመቁ፤ በመንገዳቸው የሚያልፈውን ሰው ሁሉ ዘረፉ፤ አቤሜሌክም ይህን ሁሉ ሰማ።

26 ከዚህ በኋላ የዔቤድ ልጅ ጋዓል ከወንድሞቹ ጋር ወደ ሴኬም መጣ፤ የሴኬምም ሰዎች እምነታቸውን በእርሱ ላይ ጣሉ።

27 ሁሉም ወደ ወይን ተክሎቻቸው ወጥተው የወይን ፍሬ ለቀሙ፤ የወይን ጠጅ ጠምቀው ትልቅ በዓል አደረጉ፤ ወደ አምላካቸውም መቅደስ ገብተው በዚያ እየበሉና እየጠጡ ስለ አቤሜሌክ በማፌዝ ተናገሩ።

28 የዓቤድ ልጅ ጋዓልም እንዲህ አለ፦ “አቤሜሌክ ማን ነው? እኛ የሴኬም ሰዎች ለእርሱ የምንገዛው ለምንድነው? የጌዴዎን ልጅና የእርሱ የጦር መሪ ዜቡር የሐሞርን አባት ሴኬምን ያገለገሉ አይደሉምን? ለምን ለእርሱ እንታዘዛለን? ይልቅስ የጐሣችሁ መሥራች ለሆነው ለሴኬም አባት ለሐሞር ታማኞች ሁኑ።

29 ይህን ሕዝብ የምመራው እኔ በሆንኩ ኖሮ! አቤሜሌክን ወዲያ አስወግደው ነበር፤ ደግሞም ‘ሠራዊትህን በማጠንከር ወጥተህ ተዋጋ!’ ብዬ እነግረው ነበር።”

30 የከተማይቱ ገዢ ዘቡል የዔቤድ ልጅ ጋዓል የተናገረውን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤

31 በአሩማ ወዳለውም ወደ አቤሜሌክ መልእክተኞችን ልኮ እንዲህ ብለው እንዲነግሩት አሳሰባቸው፥ “የዔቤድ ልጅ ጋዓል ከወንድሞቹ ጋር ወደ ሴኬም መጥቶአል፤ በአንተም ላይ የከተማውን ሕዝብ አነሣሥቶአል።

32 እንግዲህ አንተና ተከታዮችህ በሌሊት ከዚያ ተነሥታችሁ በመስክ ውስጥ ደፈጣ አድርጉ፤

33 ነገ ጧትም ፀሐይ ስትወጣ ተነሥታችሁ በከተማይቱ ላይ በድንገት አደጋ ጣሉ፤ ጋዓልና ተከታዮቹ እናንተን ለመውጋት ሲወጡም በተቻላችሁ መጠን በብርቱ ምቱአቸው።”

34 ስለዚህ አቤሜሌክና ተከታዮቹ ሁሉ በሌሊት ተነሥተው ከሴኬም ውጪ በአራት ወገን ተከፍለው ደፈጣ አደረጉ፤

35 አቤሜሌክና ተከታዮቹ የዔቤድ ልጅ ጋዓል ወጥቶ በከተማይቱ ቅጽር በር መቆሙን ባዩ ጊዜ ከሸመቁባቸው ስፍራዎች ወጡ፤

36 ጋዓልም እነርሱን አይቶ ዘቡልን “ተመልከት! ሰዎች ከተራራው ጫፍ ላይ እየወረዱ ነው!” አለው። ዘቡልም “እነርሱ በተራሮች ላይ የሚታዩ ጥላዎች እንጂ ሰዎች አይደሉም” ሲል መለሰለት።

37 ቀጥሎም ጋዓል “ተመልከት! ከከፍተኛ ቦታ መካከል ሰዎች ቊልቊል በመውረድ ላይ ናቸው፤ አንዱ ቡድን የአስማተኞች የወርካ ዛፍ በሚባለው መንገድ እየመጣ ነው!” አለ።

38 ከዚህ በኋላ ዘቡል እንዲህ አለው፤ “ያ ሁሉ ፉከራህ አሁን የት ደረሰ? ‘አቤሜሌክ የተባለውን ሰው የምናገለግለው ለምንድን ነው?’ ብለህ የጠየቅህ አንተ አልነበርክምን? በማፌዝ ስታላግጥባቸው የነበርከው ሰዎች እነሆ፥ እነዚህ ናቸው፤ በል ወጥተህ ጦርነት ግጠማቸው፤”

39 ጋዓል የሴኬምን ሰዎች እየመራ ወጥቶ አቤሜሌክን ጦርነት ገጠመው፤

40 ጋዓል ሸሸ፤ አቤሜሌክም አሳደደው፤ በከተማይቱ ቅጽር በር ላይ ሳይቀር ብዙዎች ቈሰሉ፤

41 አቤሜሌክም መኖሪያውን በአሩማ አደረገ፤ ዘቡል ግን ጋዓልንና ወንድሞቹን ከሴኬም እያባረረ አስወጣቸው፤ ከዚያም በኋላ እዚያ ለመኖር አልቻሉም።

42 በማግስቱ የሴኬም ሕዝብ ወደየእርሻቸው መሄዳቸውን አቤሜሌክ ሰማ፤

43 የእርሱ ተከታዮች የሆኑትን ሰዎች ወስዶ በሦስት ወገን በመክፈል በየመስኩ ሸምቀው እንዲጠባበቁ አደረገ፤ ሴኬማውያንንም ከከተማ ሲወጡ ባየ ጊዜ እነርሱን ከሸመቀበት ቦታ ወጥቶ ገደላቸው፤

44 አቤሜሌክና ከእርሱ ጋር የተመደበው ቡድን የከተማይቱን ቅጽር በር ለመጠበቅ ተጣድፈው ወጥተው በከተማው መግቢያ በር ላይ ቆሙ፤ የቀሩት ሁለቱ ቡድኖች በመስኩ በተገኙት ላይ አደጋ ጥለው ፈጁአቸው።

45 ውጊያውም ቀኑን ሙሉ ቀጥሎ ዋለ፤ አቤሜሌክ ከተማይቱን ይዞ ሕዝብዋን ሁሉ ገደለ፤ ከተማይቱን አፈራረሰ፤ በምድሪቱም ላይ ጨው ዘራባት።

46 በሴኬም ግንብ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ይህን በሰሙ ጊዜ ባዓልበሪት በሚመለክበት ቤት በሚገኘው ምሽግ ውስጥ ገቡ።

47 አቤሜሌክም በሴኬም መሰብሰባቸውን ሰማ።

48 ስለዚህም ከተከታዮቹ ጋር ወደ ጻልሞን ተራራ ወጣ፤ ከዚያም መጥረቢያ ወስዶ ከዛፍ ላይ እንጨት በመቊረጥ በትከሻው ተሸከመ፤ ተከታዮቹም በፍጥነት እርሱ እንዳደረገው ያደርጉ ዘንድ ነገራቸው።

49 እያንዳንዱም ሰው ከዛፍ እንጨት ቈረጠ፤ አቤሜሌክንም ተከትለው ያን እንጨት ምሽጉን በማስደገፍ ከመሩት፤ ሰዎቹ በውስጡ እንዳሉም በእሳት አቃጠሉት፤ ስለዚህም በምሽጉ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ሁሉ ሞቱ፤ የወንዶቹና የሴቶቹ ቊጥር አንድ ሺህ ያኽል ነበር።

50 ከዚህ በኋላ አቤሜሌክ ወደ ቶቤጽ ሄደ፤ ከተማይቱንም ከቦ ያዛት፤

51 በከተማይቱ ውስጥ አንድ ትልቅ የከተማ መጠበቂያ ግንብ ስለ ነበረ፥ መሪዎቹ ሳይቀሩ እያንዳንዱ ወንድም ሆነ ሴት ሮጦ ወደ እርሱ ገባ፤ በሩንም ዘግተው ወደ ጣራው ወጡ፤

52 አቤሜሌክ እየተዋጋ ወደ ግንቡ በደረሰ ጊዜ በእሳት ለማያያዝ ወደ በሩ ቀረበ።

53 ነገር ግን አንዲት ሴት በራሱ ላይ የወፍጮ ድንጋይ ናዳ በመጣል አናቱን ፈጠፈጠችው።

54 እርሱም የጦር መሣሪያ አንጋቹን ወጣት በፍጥነት በመጥራት፥ “ሰይፍህን መዘህ ግደለኝ፤ ሴት ገደለችው እንድባል አልፈልግም” ሲል አዘዘው። ስለዚህ ወጣቱ በሰይፍ መትቶ ገደለው።

55 እስራኤላውያን አቤሜሌክ መሞቱን ባዩ ጊዜ ሁሉም ወደየቤታቸው ሄዱ።

56 በዚህ ዐይነት አቤሜሌክ ሰባ ወንድሞቹን በመግደል በአባቱ ላይ በፈጸመው በደል እግዚአብሔር ፍዳውን ከፈለው፤

57 እንዲሁም እግዚአብሔር የሴኬም ሰዎች ስለ ክፋታቸው ዋጋ የሆነውን መከራ እንዲቀበሉ አደረገ፤ በዚህ አኳኋን የጌዴዎን ልጅ ኢዮአታም በረገማቸው ጊዜ በእነርሱ ላይ እንደሚደርስባቸው የተናገረው ሁሉ ተፈጸመ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告