Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

መሳፍንት 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ምዕራፍ 7 ጌዴዎን ምድያማውያንን ድል ማድረጉ

1 በማግስቱም ማለዳ ይሩባዓል የተባለው ጌዴዎንና ተከታዮቹ በጧት ማልደው ተነሥተው በሐሮድ ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ። የምድያማውያን ሰፈርም ከእነርሱ በስተሰሜን በሞሬ ኮረብታ አጠገብ በሸለቆ ውስጥ ነበር።

2 እግዚአብሔርም ጌዴዎንን እንዲህ አለው፦ “በምድያማውያን ላይ ድልን አቀዳጃቸው ዘንድ ከአንተ ጋር ያሉ ሰዎች ለእኔ እጅግ ብዙ ሆነዋል፤ በራሳቸው ኀይል የሚያሸንፉ ስለሚመስላቸው ለእኔ ክብር ከመስጠት ይቈጠባሉ፤

3 ስለዚህ ለሕዝቡ ‘ከመካከላችሁ ፈሪና ድንጉጥ የሆነ ሰው ካለ ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ፤ እኛም በዚህ በገለዓድ ተራራ ላይ እንቈያለን’ ብለህ ንገራቸው።” በዚህ ምክንያት ኻያ ሁለቱ ሺህ ሲመለሱ ዐሥሩ ሺህ ቀሩ።

4 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፦ “አሁንም ገና ብዙ ሠራዊት አሉህ፤ እነርሱን ወደ ወንዝ ውሰዳቸውና በዚያ እኔ እፈትናቸዋለሁ፤ ከአንተ ጋር ይሂድ የምለው ሰው ይሂድ፤ ይቅር የምለው ሰው ደግሞ ይመለስ።”

5 ጌዴዎንም ሰዎቹን ወደ ወንዝ ውሃ አወረዳቸው፤ እግዚአብሔርም “በጒልበቱ ተንበርክኮ ውሃ ከሚጠጣው መካከል እንደ ውሻ በምላሱ እየጨለፈ የሚጠጣውን ሁሉ ለየው!” አለው።

6 በእጃቸው ውሃ እየዘገኑ የሚጠጡት ቊጥር ሦስት መቶ ሆነ፤ የቀሩት ሁሉ የጠጡት ግን በጒልበታቸው ተንበርክከው ነበር።

7 እግዚአብሔር ጌዴዎንን “በእጃቸው ውሃ እየዘገኑ በጠጡት በእነዚህ ሦስት መቶ ሰዎች አማካይነት አድናችኋለሁ፤ በምድያማውያን ላይ ድልን እንድትቀዳጅ አደርግሃለሁ፤ ለቀሩት ግን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ንገራቸው” አለው።

8 ስለዚህ ጌዴዎን የሕዝቡን ስንቅና እምቢልታዎቹን ከተረከቡት ከሦስት መቶዎቹ በቀር ሌሎቹን እስራኤላውያን ሁሉ ወደየቤታቸው እንዲመለሱ አሰናበታቸው፤ ይህም ሁሉ በሚሆንበት ጊዜ የምድያማውያን ሰፈር ከእነርሱ በታች በሸለቆው ውስጥ ነበር።

9 በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፥ “በእነርሱ ላይ ድልን እንድትቀዳጅ የማደርግህ ስለ ሆነ ተነሥተህ የእነርሱን ሰፈር አጥቃ።

10 አንተ በሰፈሩ ላይ አደጋ ለመጣል ከፈራህ ግን ፑራ ተብሎ ከሚጠራው አገልጋይህ ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ፤

11 እነርሱም የሚሉትን ትሰማለህ፤ ከዚያም በኋላ በእነርሱ ላይ አደጋ ለመጣል ድፍረት ታገኛለህ፤”። ስለዚህ ጌዴዎንና አገልጋዩ ፑራ ወደ ጠላት ሰፈር ዳርቻ ወረዱ፤

12 ብዛታቸው እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ምድያማውያን፥ ዐማሌቃውያንና የምሥራቅ ሰዎች በሸለቆው ውስጥ ሰፍረው ነበር፤ ግመሎቻቸውም ከብዛታቸው የተነሣ እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ሊቈጠር የማይቻል ነበር።

13 ጌዴዎን እዚያ በደረሰ ጊዜ አንድ ሰው ያየውን ሕልም ለጓደኛው ሲነግረው ሰማ፤ ሕልሙም እንዲህ የሚል ነበር፦ “አንዲት የገብስ ቂጣ ከላይ ተንከባልላ ወርዳ ወደ ምድያም ሰፈር ደርሳ በዚያ ያለውን ድንኳን መታችው፤ ድንኳኑም ተገልብጦ በምድር ላይ ተዘረጋ።”

14 ጓደኛውም “ይህማ የእስራኤላዊው የኢዮአስ ልጅ የጌዴዎን ሰይፍ ነው! ከቶ ሌላ ትርጒም ሊሰጠው አይችልም፤ እግዚአብሔር ለጌዴዎን በምድያምና በመላው ሠራዊታችን ላይ ድልን ሰጥቶታል!” ሲል መለሰለት።

15 ጌዴዎን ስለ ሰውየው ሕልምና ስለ ፍቹም ምንነት በሰማ ጊዜ በጒልበቱ ተንበርክኮ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ ወደ እስራኤላውያንም ሰፈር ተመልሶ “እግዚአብሔር በምድያማውያንና በሠራዊቱ ላይ ድልን የሚያቀዳጃችሁ ስለ ሆነ ተነሡ!” አላቸው።

16 ሦስት መቶዎቹንም ሰዎች ከፍሎ በሦስት ቡድን መደባቸው፤ ለእያንዳንዱም ሰው አንድ እምቢልታና በውስጡ ችቦ ያለበት አንድ ማሰሮ ሰጠ።

17 እንዲህም አላቸው፤ “እኔ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ ስደርስ፥ የማደርገውን በጥንቃቄ ተመልክታችሁ ያንኑ አድርጉ።

18 እኔና ከእኔ ጋር የተመደቡት ሰዎች በቀንደ መለከቶቻችን ድምፅ ስናሰማ፥ እናንተም የራሳችሁን እምቢልታ ድምፅ በሰፈሩ ዙሪያ እያሰማችሁ ‘ለእግዚአብሔርና ለጌዴዎን ተዋጉ!’ ብላችሁ ጩኹ።”

19 ከእኩለሌሊት ጥቂት ቀደም ብሎ፥ ዘብ ጠባቂዎች ከተቀያየሩ በኋላ ጌዴዎንና ከእርሱ ጋር የተመደቡት መቶ ሰዎች ወደ ሰፈሩ ዳርቻ መጡ፤ እምቢልታዎቻቸውን ነፉ፤ የያዙትንም ማሰሮ ሁሉ ሰባበሩ።

20 በሌላም በኩል የነበሩት ሁለቱ ክፍሎች እንዲሁ አደረጉ፤ ሁሉም የተለኰሱትን ችቦዎቻቸውን በግራ እጃቸው፥ እምቢልታቸውን በቀኝ እጃቸው ይዘው “ለእግዚአብሔርና ለጌዴዎን እንዋጋለን!” እያሉ በመጮኽ ደነፉ።

21 እያንዳንዱ ሰው በሰፈሩ ዙሪያ በተመደበለት ቦታ ቆመ፤ መላው የጠላት ሠራዊትም የኡኡታ ድምፅ እያሰማ ሸሸ፤

22 ሦስት መቶው የጌዴዎን ሰዎች እምቢልታቸውን በሚነፉበት ጊዜ እግዚአብሔር እያንዳንዱን የጠላት ወታደር በጓደኛው ላይና በሠራዊቱ ላይ ሰይፉን እንዲያነሣ አደረገ፤ ሠራዊቱም ፊታቸውን ወደ ጽሬራ በመመለስ እስከ ቤትሺጣ፥ ከዚያም አልፎ በጣባት አጠገብ እስካለው አቤልመሖላ ድረስ ሸሽተው ሄዱ።

23 ከዚህ በኋላ የንፍታሌም፥ የአሴርና መላው የምናሴ ነገድ ተጠርተው ወጥተው ምድያማውያንን አሳደዱ፤

24 ጌዴዎንም በኮረብታማው በኤፍሬም አገር ወዳሉት ሁሉ መልእክተኞች ልኮ “ወርዳችሁ በምድያማውያን ላይ ዝመቱ፤ ምድያማውያን ተሻግረው እንዳያመልጡ የዮርዳኖስን ወንዝና ወደ እርሱ የሚገቡትንም መጋቢ ወንዞች እስከ ቤትባራ ድረስ በር በሩን ዘግታችሁ በተጠናከረ ሁኔታ ጠብቁ” አላቸው። ስለዚህ የኤፍሬም ሰዎች በአንድነት ተጠራርተው የዮርዳኖስን ወንዝና ወደዚያ የሚገቡትን መጋቢ ወንዞች እስከ ቤተባራ ድረስ ዘግተው ያዙ።

25 ዖሬብና ዘኤብ የተባሉ ሁለት የምድያማውያን መሪዎችንም ማረኩ፤ ዖሬብን “የዖሬብ አለት” ተብሎ ወደሚጠራው ስፍራ፥ ዘኤብንም “የዘኤብ የወይን መጭመቂያ” ተብሎ በሚጠራው ቦታ ገደሉአቸው፤ ከዚህም በኋላ የቀሩትን ምድያማውያን ማሳደድ ቀጠሉ፤ የዖሬብንና የዘኤብንም ራሶች ቈርጠው ወደ ጌዴዎን አመጡለት፤ በዚያን ጊዜ ጌዴዎን ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በኩል ነበረ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告