Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

መሳፍንት 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የዲቦራና የባራቅ መዝሙር

1 በዚያን ቀን ዲቦራና የአቢኒዓም ልጅ ባራቅ ይህን መዝሙር ዘመሩ፦

2 መሪዎች እስራኤልን ስለ መሩ፥ ሕዝቡም በፈቃደኛነት ራሱን ስላቀረበ፤ እግዚአብሔርን አመስግኑ!

3 እናንተ ነገሥታት ስሙ! እናንተም አለቆች አድምጡ! እኔ ለእግዚአብሔር፥ እዘምራለሁ፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር አዜማለሁ።

4 እግዚአብሔር ሆይ! ከኤዶም ተራራ በተነሣህ ጊዜ፥ በኤዶምም ምድር ላይ በተራመድህ ጊዜ ምድር ተንቀጠቀጠች፤ ሰማያት ዝናብን አዘነቡ፤ አዎ! ውሃ ከደመናዎች ወደታች ጐረፈ።

5 በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ፊት፥ በሲናው አምላክ ፊት፥ ተራራዎች ተናወጡ።

6 በዐናት ልጅ በሻምጋርና በያዔል ዘመን፥ የሲራራ ነጋዴዎች በምድሪቱ አያልፉም ነበር፤ መንገደኞችም ተደብቀው በዘወርዋራ መንገድ ይሄዱ ነበር፤

7 አንቺ ዲቦራ ነሽ፥ በእስራኤል መካከል እንደ እናት ሆነሽ እስከ ተነሣሽ ድረስ በእስራኤል ዘንድ የተረፉ ኀያላን አልነበሩም።

8 እስራኤላውያን ቀድሞ የማያውቁአቸውን ባዕዳን አማልክትን በመረጡ ጊዜ፥ በምድሪቱ ላይ ጦርነት ሆነ፤ ከአርባ ሺህ እስራኤላውያን ጋሻና ጦር የያዘ አንድ ሰው እንኳ አልነበረም!

9 ልቤ ከእስራኤል የጦር አዛዦች ጋር ነው፤ እንዲሁም ደስ ብሎአቸው በበጎ ፈቃድ ከተነሣሡት ጋር ነው፤ እግዚአብሔር ይመስገን!

10 እናንተ ኮርቻ በተጫኑ በነጫጭ አህዮች ላይ ተቀምጣችሁ የምትጓዙ፥ እናንተ በምቹና በአማረ ግላስ ላይ የምትንደላቀቁ፥ እናንተ በእግር የምትንሸራሸሩ፥ ስለዚህ ነገር ተናገሩ።

11 እነሆ አድምጡ! ውሃ በሚቀዳባቸው ጒድጓዶች ዙሪያ የሚሰማው የብዙ ሰዎች ድምፅ፥ የእግዚአብሔርን ድል ያበሥራል፤ የእስራኤልንም ሕዝብ ድል አድራጊነት ይናገራል። ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ሕዝብ፥ ከከተሞቻቸው ተሰልፈው ወረዱ።

12 ዲቦራ ሆይ! ንቂ! ንቂ! ንቂ! መዝሙርም ዘምሪ! የአቢኒዔም ልጅ ባራቅ ሆይ! ተነሣ! ምርኮህንም እየመራህ ወደ ፊት ገሥግሥ!

13 ከዚህ በኋላ ቀሪዎቹ ወደ መኳንንቱ ወረዱ፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ ስለ እኔ ኀያላኑን ለመውጋት ወረዱ።

14 ቀድሞ ዐማሌቃውያን ይኖሩበት ከነበረው ከኤፍሬም ወታደሮች መጡ፤ ሌሎችም ከብንያም መጡ። ከማኪር መሪዎች፥ ከዛብሎንም በትረ መንግሥትን የሚይዙ መጡ።

15 የይሳኮር መሪዎች ከዲቦራ ጋር መጡ፤ አዎ፥ ይሳኮርም ባራቅም መጡ፤ ወደ ሸለቆው ተከተሉት፤ ነገር ግን የሮቤል ነገድ ለሁለት ተከፈለ፤ ለመምጣት ወይም ላለመምጣት አመነታ።

16 ለምን በበጎች መካከል ዘገየህ? ለበጎች የሚደረገውን ፉጨት ለመስማት ነውን? ለመምጣት ወይም ላለመምጣት አመነታ።

17 የጋድ ነገድ ከዮርዳኖስ ማዶ ቈየ፤ የዳን ነገድ ለምን በመርከብ ውስጥ ኖረ? የአሴር ነገድ በባሕር ጠረፍ ቀረ፤ በወደብ አጠገብም ኖረ።

18 የዛብሎን ሕዝቦች፥ ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው ሰጡ።

19 በመጊዶ ውሃ አጠገብ በታዕናክ፥ ነገሥታቱ መጥተው ተዋጉ፤ ከዚያም የከነዓንን ነገሥታት ተዋጉ፤ የብር ምርኮ አላገኙም።

20 በሰማይ ከዋክብት ተዋጉ፤ በሂደታቸው ሲሣራንም ጦርነት ገጠሙት።

21 የቂሶን ጐርፍ ጠራረጋቸው፤ የጥንቱ የቂሶን ወንዝ በጐርፉ ወሰዳቸው፤ ነፍሴ ሆይ! በርቺ! ገሥግሺ!

22 ፈረሰኞች እየጋለቡ ሲመጡ የፈረሶቹ ኮቴዎች የነጐድጓድ ድምፅ አሰሙ።

23 የእግዚአብሔር መልአክ እንዲህ አለ፤ “ሜሮዝን ርገሙ! እዚያ የሚኖሩትን ሁሉ ፈጽማችሁ ርገሙ! እነርሱ በእግዚአብሔር ጐን አልቆሙም፤ ስለ እርሱም ለመዋጋት አልተሰለፉም።”

24 የቄናዊው የሔቤር ሚስት ያዔል፥ ከሴቶች ሁሉ ይልቅ የተባረከች ትሁን፤ በድንኳን ከሚኖሩ ሴቶችም ሁሉ ይልቅ የተባረከች ትሁን፤

25 ሲሣራ “ውሃ አጠጪኝ” አላት፤ እርስዋ ግን ወተት አቀረበችለት፤ በተከበረ ጽዋ እርጎ አመጣችለት።

26 እንዲሁም በአንድ እጅዋ የድንኳን ካስማ፥ በቀኝ እጅዋ የሠራተኛ መዶሻ ያዘች፤ ሲሣራንም መታ የራስ ቅሉን አደቀቀችው፤ ጆሮ ግንዱንም ቸነከረችው።

27 በእግሮችዋ ሥር ተዝለፍልፎ ወደቀ፤ በእግሮችዋ ሥር ተደፋ፤ በወደቀበትም በዚያው ሞተ።

28 የሲሣራ እናት በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ በዐይነ ርግብ ቀዳዳም አተኲራ አየች፤ “የልጄ ሠረገላ ለምን ዘገየ? የሠረገላዎቹ ፈረሶች የኮቴ ድምፅስ ለምን ዘገየ?” ስትል ጠየቀች።

29 ጥበበኞች የሆኑ ወይዛዝሮችዋም መልስ ሰጡአት፤ በእርግጥ እርስዋ ለራስዋ መልስዋን አገኘች።

30 “ምርኮ አግኝተው በመካከላቸው እየተከፋፈሉ አይደለምን? አንድ ወይም ሁለት ቈነጃጅት ለያንዳንዱ ወንድ፥ ለሲሣራ በልዩ ልዩ ቀለማት ያጌጠ የልብስ ምርኮ፥ ለእኔም ለአንገቴ በአንገቴ ላይ በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጒርጒር ልብስ፥”

31 እግዚአብሔር ሆይ! ጠላቶችህን ሁሉ በዚህ ዐይነት አጥፋ፤ ወዳጆችህ ግን እንደ ንጋት ፀሐይ ይድመቁ። ከዚህ በኋላ በምድሪቱ ላይ አርባ ዓመት ሙሉ ሰላም ሆነ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告