መሳፍንት 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምዲቦራና ባራቅ 1 ኤሁድ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ እንደገና በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠሩ፤ 2 ስለዚህም እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በሐጾር ከተማ ይኖር ለነበረው ለከነዓናዊው ንጉሥ ለያቢን አሳልፎ ሰጣቸው፤ የሠራዊቱም አለቃ የአሕዛብ ይዞታ በሆነችው በሐሮሼት ከተማ ይኖር የነበረው ሲሣራ ነበር። 3 ያቢን ዘጠኝ መቶ የብረት ሠረገሎች ነበሩት፤ የእስራኤል ሕዝብ በጭካኔና በዐመፅ ለኻያ ዓመት ገዛቸው፤ ከዚያም በኋላ የእስራኤል ሕዝብ እንዲረዳቸው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። 4 በዚያን ጊዜ የላፒዶት ሚስት የሆነች “ዲቦራ” የምትባል ነቢይት ነበረች፤ እርስዋም በዚያን ጊዜ የእስራኤል መሪ ነበረች። 5 ይህችም ነቢይት በተራራማው በኤፍሬም አገር በራማና በቤትኤል መካከል በሚገኘው የዲቦራ የተምር ዛፍ ሥር ተቀምጣ ትፈርድ ስለ ነበር የእስራኤል ሕዝብ ፍርድ ለማግኘት ወደ እርስዋ ይሄዱ ነበር። 6 የአቢኒዓምን ልጅ ባራቅን የንፍታሌም ድርሻ ከሆነችው ከቃዴስ ከተማ አስጠርታ እንዲህ አለችው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይህን ትእዛዝ ሰጥቶሃል፦ ‘ከንፍታሌምና ከዛብሎን ነገዶች ዐሥር ሺህ ሰዎች መርጠህ ወደ ታቦር ተራራ ውሰዳቸው፤ 7 የያቢን ሠራዊት አዛዥ የሆነው ሲሣራ በቂሾን ወንዝ አንተን ለመውጋት እንዲመጣ አደርጋለሁ፤ እርሱም ሠረገሎቹንና ወታደሮቹን አሰልፎ ይመጣል፤ እኔም በእርሱ ላይ ድልን እንድትቀዳጅ አደርግሃለሁ።’ ” 8 ከዚህ በኋላ ባራቅ “አንቺ ከእኔ ጋር ከሄድሽ እሄዳለሁ፤ አብረሽኝ ካልሄድሽ ግን እኔም አልሄድም” አላት። 9 እርስዋም “እሺ፥ እኔም ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሲሣራን ለሴት አሳልፎ ስለሚሰጥ ድሉ ለአንተ ክብር አይሆንም” አለችው፤ ስለዚህ ዲቦራ ከባራቅ ጋር ወደ ቃዴስ ዘመተች። 10 ባራቅም የንፍታሌምንና የዛብሎንን ነገዶች ወደ ቃዴስ አስጠራ፤ ከእነርሱም ዐሥር ሺህ ሰዎች ተከተሉት፤ ዲቦራም አብራው ዘመተች። 11 ቀኔናዊው ሔቤር የሙሴ ዐማት ከነበረው ከሆባብ ልጆች ከቄናውያን ተለየ፤ ወደ ቃዴስ ቀረብ ብሎ በጸእናይም በሚገኘው በታላቁ ዛፍ አጠገብ ድንኳኑን ተከለ። 12 የአቢኒዓም ልጅ ባራቅ ወደ ታቦር ተራራ መሄዱ ለሲሣራ ተነገረው። 13 ሲሣራም ዘጠኝ መቶ የብረት ሠረገሎችንና ከእርሱ ጋር የነበረውን ሠራዊት ሁሉ የአሕዛብ ይዞታ ከነበረችው ከሐሮሼት ወደ ቂሶን ወንዝ ሰበሰበ። 14 ዲቦራም ባራቅን “እግዚአብሔር አንተን በሲሣራ ላይ ድልን እንድትቀዳጅ የሚያደርግበት ቀን ዛሬ ስለ ሆነ ተነሥ! እነሆ! እግዚአብሔር ይመራሃል” አለችው፤ ባራቅም ዐሥር ሺህ ወታደሮች ተከትለውት ከታቦር ተራራ ወረደ። 15 ባራቅ ከሠራዊቱ ጋር አደጋ በጣለ ጊዜ እግዚአብሔር ሲሣራን ከሠረገሎቹና ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር በአደናጋሪ ሁከት ላይ እንዲወድቅ አደረገው፤ ሲሣራም ከሠረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ። 16 ባራቅም ሠረገሎቹንና ሠራዊቱን የአሕዛብ ይዞታ እስከ ሆነችው እስከ ሐሮሼት ድረስ አሳደዳቸው፤ የሲሣራም ሠራዊት በሙሉ በሰይፍ ተገደሉ፤ አንድ ሰው እንኳ አልተረፈም። 17 የሐጾር ንጉሥ ያቢን ከሔቤር ቤተሰብ ጋር ሰላም መሥርቶ ይኖር ስለ ነበር ሲሣራ ሸሽቶ የቄናዊው የሔቤር ሚስት ወደሆነችው ወደ ያዔል ድንኳን ገባ። 18 ያዔልም ሲሣራን ልትቀበለው ወጥታ “ጌታዬ ና፥ ወደ ድንኳኔ ግባ፤ ከቶ አትፍራ” አለችው፤ እርሱም ወደ ውስጥ በገባ ጊዜ በልብስ ሸፈነችው፤ 19 ሲሣራም “እባክሽ የምጠጣው ውሃ ስጪኝ፤ በጣም ጠምቶኛል” አላት፤ እርስዋም ከቈዳ የተሠራውን የወተት ዕቃ ከፍታ አጠጣችውና እንደገና ሸፍና ደበቀችው። 20 ከዚህ በኋላ እርሱ “በድንኳኑ በር ላይ ቁሚ፤ አንድ ሰው መጥቶ ከዚህ ሌላ ሰው እንዳለ ቢጠይቅሽ ማንም የለም በይው” አላት። 21 ሲሣራ በጣም ደክሞት ስለ ነበር ከባድ እንቅልፍ ወሰደው፤ ከዚህ በኋላ የሔቤር ሚስት ያዔል መዶሻና የድንኳን ካስማ ወስዳ በቀስታ ወደ እርሱ ቀረበች፤ ካስማውንም በጆሮ ግንዱ ጠልቆ መሬት እስኪነካ ድረስ ቸነከረችው፤ እርሱም ሞተ። 22 ባራቅ ሲሣራን እያሳደደ ሲመጣ ያዔል ልትቀበለው ወጥታ “ወደዚህ ና! አንተ የምትፈልገውን ሰው አሳይሃለሁ” አለችው። ስለዚህም ከእርስዋ ጋር ወደ ውስጥ በገባ ጊዜ የድንኳኑ ካስማ በሲሣራ ጆሮ ግንድ ላይ እንደ ተቸነከረ ሬሳውን በመሬት ላይ ተጋድሞ አየ። 23 እግዚአብሔርም በዚያን ቀን እስራኤላውያን በከነዓናዊው ንጉሥ በያቢን ላይ ድልን እንዲቀዳጁ አደረገ። 24 እነርሱም እርሱን ፈጽመው እስከሚያጠፉ ድረስ የእስራኤል ሕዝብ በያቢን ላይ እየበረቱ ሄዱ። |