መሳፍንት 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምለብንያም ነገድ ተወላጆች የተመደቡ ሚስቶች 1 እስራኤላውያን በምጽጳ በተሰበሰቡ ጊዜ “ከእኛ መካከል ማንም ሰው ሴት ልጁን ለብንያማዊ መዳር የለበትም” በማለት ተማምለው ነበር። 2 እስራኤላውያን ወደ ቤትኤል መጥተው በእግዚአብሔር ፊት እስከ ማታ ተቀምጠው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ። 3 እነርሱም፦ አቤቱ፥ የእስራኤል አምላክ ሆይ! ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ መታጣቱ፥ ስለምን ይህ በእስራኤል ላይ ሆነ? አሉ። 4 በማግስቱም ጧት በማለዳ ሕዝቡ በዚያ መሠዊያ ሠሩ፤ የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕትም አቀረቡ። 5 “በምጽጳ በእግዚአብሔር ፊት ስንሰበሰብ ወደዚያ ያልመጣ ከእስራኤል ነገዶች መካከል አንድ ወገን እንኳ ይገኛልን?” ብለውም ጠየቁ፤ ይህንንም ያሉበት ምክንያት ወደ ምጽጳ ያልሄደ ማንም ሰው ቢገኝ በሞት ለመቅጣት ተማምለው ስለ ነበር ነው። 6 የእስራኤል ሕዝብ ወንድሞቻቸው ለሆኑት ለብንያማውያን አዝነው ስለ ነበር “ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ ጠፍቷል፤ 7 ከሴቶች ልጆቻችን ማንኛይቱንም ለእነርሱ እንዳንድር በመሐላ ቃል ስለ ገባን ከሞት የተረፉት ብንያማውያን ሚስት ያገኙ ዘንድ ምን እናድርግ?” አሉ። 8 እነርሱ እንዲህ አሉ፦ “ከእስራኤል ነገዶች መካከል ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ ያልመጣ አለን?” እነሆ ከያቤሽ ገለዓድ ወደ ስብሰባው ማንም አልመጣም ነበር። 9 ሠራዊቱን ለመቊጠር በያንዳንዱ ስም በሚጠራበት ጊዜ ከያቤሽ ወገን አንድም ሰው አልነበረም፤ 10 ስለዚህ ጉባኤው “ወደ ያቤሽ ሄዳችሁ ሴቶችና ሕፃናት ሳይቀሩ የገለዓድ ኗሪዎችን በሰይፍ ስለት ግደሉ!” ብለው ዐሥራ ሁለት ሺህ ኀያላንን ላኩ። 11 ወንዶችን ሁሉና ከወንድ ጋር የተገናኙትን ሴቶች ሁሉ ግደሉ ብለው አዘዙአቸው። 12 በዚህም ዐይነት በያቤሽ ገለዓድ ካሉት ኗሪዎች መካከል አራት መቶ ወንድ ያላወቁ ቆነጃጅት አገኙ፤ ስለዚህም እነርሱን በከነዓን ምድር በሴሎ ወደሚገኘው ሰፈር ይዘው መጡ። 13 ከዚህ በኋላ መላው ጉባኤ የሪሞን አለት ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ወደነበሩት ብንያማውያን መልእክት ልከው ጦርነቱ እንዲቆም ተስማሙ፤ 14 ብንያማውያንም ተመልሰው መጡ፤ ሌሎቹም እስራኤላውያን ከሞት በመትረፍ ከያቤሽ ተማርከው የመጡትን ልጃገረዶች ሰጡአቸው፤ ነገር ግን ቊጥራቸው ተመጣጣኝ ሆኖ አልተገኘም። 15 እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ነገዶች መካከል ያለው አንድነት እንዲቋረጥ አድርጎ ስለ ነበር ሕዝቡ ስለ ብንያማውያን እጅግ አዘኑ። 16 ስለዚህም የጉባኤው መሪዎች እንዲህ አሉ፥ “በብንያም ነገድ ከእንግዲህ ሴቶች አልተገኙም፤ ታዲያ ከሞት የተረፉት ወንዶች ሚስት ማግኘት ይችሉ ዘንድ ምን እናድርግ? 17 ከእስራኤል ነገድ አንዱ ጠፍቶ እንዳይቀር ብንያማውያን ወራሽ ሊኖራቸው ይገባል። 18 ይሁን እንጂ ከእኛ መካከል ማንም ሰው ሴት ልጁን ለብንያማዊ ቢድር የተረገመ እንደሚሆን በመሐላ ቃል የገባን ስለ ሆነ ሴቶች ልጆቻችንን ያገቡ ዘንድ ልንፈቅድላቸው አንችልም።” 19 ከዚህ በኋላ “በየዓመቱ በሴሎ ለእግዚአብሔር የሚዘጋጀው በዓል እነሆ ቀርቦአል” በማለትም አሰቡ፤ ሴሎ ከቤትኤል በስተ ሰሜን፥ ከለቦና በስተ ደቡብ፥ በቤትኤልና በሴኬም መካከል ካለው መንገድ በስተ ምሥራቅ ነበረች። 20 ስለዚህ ብንያማውያንን እንዲህ አሉአቸው፥ “ሂዱና በወይን ተክል ውስጥ ሸምቁ፤ 21 ተጠባበቁ፤ በበዓሉ ዕለት የሴሎ ልጃገረዶች ለመጨፈር ሲመጡ እናንተም ከወይኑ ተክል ውስጥ ውጡ፤ እያንዳንዳችሁ ከእነዚያ ልጃገረዶች መካከል እየጠለፋችሁ ሚስት አድርጋችሁ ውሰዱ፤ ወደ ብንያም ግዛትም ይዛችኋቸው ሂዱ። 22 አባቶቻቸውም ሆኑ ወንድሞቻቸው ወደ እናንተ መጥተው ሊቃወሙአችሁ ቢፈልጉ ‘ሚስቶች ለማድረግ የወሰድናቸው በጦርነት አስገድደን ስላልሆነ እባካችሁ ምሕረት አድርጉልን፤ እናንተም በፈቃዳችሁ ስላልሰጣችሁን መሐላችሁን በማፍረስ በደለኞች አትሆኑም’ ብላችሁ መልስ መስጠት ትችላላችሁ።” 23 ብንያማውያንም እንደዚሁ አደረጉ፤ በብዛታቸው ልክ እያንዳንዱ በሴሎ ከሚጨፍሩት ልጃገረዶች መካከል እየጠለፈ በሚስትነት ይዞ ሄደ፤ ወደ ግዛታቸውም ተመልሰው ከተሞቻቸውን በማደስ በዚያ ኖሩ። 24 በዚያኑ ጊዜ ሌሎቹም እስራኤላውያን በሙሉ ለመሄድ ተነሡ፤ እያንዳንዱም ወደ ራሱ ነገድና ቤተሰብ እንዲሁም ወደራሱ ቤት ንብረት ተመለሰ። 25 በዚያም ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ እያንዳንዱም ሰው ለራሱ ደስ ያለውን ነገር ሁሉ እንደ ፈለገ ያደርግ ነበር። |