መሳፍንት 20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእስራኤል ሕዝብ ለጦርነት መዘጋጀት 1 ከሰሜን እስከ ደቡብ፥ ማለትም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ እንዲሁም በስተምሥራቅ በገለዓድ ምድር ያሉት የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ለጦርነት ተዘጋጁ፤ በአንድነትም ሆነው በምጽጳ በእግዚአብሔር ፊት ተሰበሰቡ፤ 2 የእስራኤል ሕዝብና ነገድ አለቆች ሁሉ፥ እንዲሁም አራት መቶ ሺህ መሣሪያ የታጠቁ የእግረኛ ጦር ወታደሮች በስብሰባው ተገኝተው ነበር። 3 በዚያን ጊዜ የብንያም ነገድ እስራኤላውያን በሙሉ በምጽጳ መሰብሰባቸውን ሰሙ። እስራኤላውያንም “ይህ ክፉ ሥራ የተፈጸመው እንዴት እንደ ሆነ ንገሩን!” አሉ፤ 4 ቊባቱ የተገደለችበት ያ ሌዋዊ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔና ቊባቴ ሌሊቱን ለማሳለፍ በብንያም ግዛት ወደምትገኘው ወደ ጊብዓ ሄድን፤ 5 የጊብዓ ሰዎች በእኔ ላይ አደጋ ለመጣል መጥተው በሌሊት ቤቱን ከበቡት፤ በመጀመሪያ እኔን ለመግደል አስበው ነበር፤ በኋላ ግን በቊባቴ ላይ ተረባርበው ስላመነዘሩባት ሞተች፤ 6 ከዚህ በኋላ የቁባቴን አስከሬን ወስጄ ቈራረጥሁት፤ እነርሱ ይህን የመሰለ ክፉ በደል ስለ ሠሩ የቈራረጥኋቸውን ቊርጥራጮች ወደ እስራኤል አገር ሁሉ ላክሁ። 7 እዚህ ያላችሁት እስራኤላውያን ሁሉ ምክራችሁንና ፍርዳችሁን ስጡ።” 8 ሕዝቡም ሁሉ በአንድነት ቆመው እንዲህ አሉ፤ “ከእኛ መካከል በድንኳንም ሆነ በቤት ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ሰው ወደ ቤቱ አይመለስም፤ 9 የምናደርገውም ይህ ነው፤ ዕጣ በመጣል በጊብዓ ላይ አደጋ የሚጥሉ ሰዎችን እንመርጣለን፤ 10 በእስራኤል ላይ በፈጸሙት አሳፋሪ ተግባር በብንያም ግዛት የምትገኘውን የጊብዓን ሕዝብ ለመበቀል ለሚዘምተው ሠራዊት ስንቅ ያቀብሉ ዘንድ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል ከመቶ ዐሥር፥ ከሺህ መቶ፥ ከዐሥር ሺህ አንድ ሺህ ሰው እንመድባለን።” 11 ስለዚህም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ በከተማይቱ ላይ አደጋ ለመጣል በአንድነት ተሰበሰቡ። 12 የእስራኤል ነገዶች በመላው በብንያም ግዛት ተዘዋውረው እንዲህ የሚል ቃል የሚናገሩትን መልእክተኞች ላኩ፥ “ይህ የፈጸማችሁት ክፉ ነገር ምንድን ነው? 13 እነርሱን ገድለን ይህን ክፉ ነገር ከእስራኤል እናስወግድ ዘንድ እነዚያን በጊብዓ ያሉትን ነውረኞች አሳልፋችሁ ስጡን።” የብንያም ሕዝብ ግን የቀሩት እስራኤላውያን የነገሩአቸውን ነገር አልተቀበሉም፤ 14 እንዲያውም እነርሱን ለመውጋት ከብንያም ከተሞች ሁሉ ተሰባስበው ወደ ጊብዓ መጡ፤ 15 በዚያን ቀን ብንያማውያን፥ ከየከተሞቻቸው ኻያ ስድስት ሺህ መሣሪያ የታጠቁ ሰዎችን አሰባሰቡ፤ ይህም ከጊብዓ ኗሪዎች ከተመረጡት ከሰባት መቶ ሰዎች ሌላ ነው። 16 ከእነዚያም መካከል የተመረጡ ሰባት መቶ ግራኝ ሰዎች ነበሩ፤ እነዚህም ድንጋይ የሚወነጭፉና ሌላው ቀርቶ አንዲት ጠጒርን እንኳ የማይስቱ ነበሩ። 17 እስራኤላውያን የብንያምን ነገድ ሳይጨምሩ ብዛቱ አራት መቶ ሺህ መሣሪያ የታጠቀ ሠራዊት አሰለፉ። በብንያማውያን ላይ የተደረገ ጦርነት 18 እስራኤላውያን ወደ ቤትኤል ወጥተው “በብንያማውያን ላይ መጀመሪያ አደጋ መጣል የሚገባው የትኛው ነገድ ነው?” ሲሉ እግዚአብሔርን ጠየቁ። እግዚአብሔርም “የይሁዳ ነገድ አስቀድሞ ይዝመት” አላቸው። 19 ስለዚህ በማግስቱ ጧት ጒዞ ጀመሩ፤ በጊብዓ አጠገብም ሰፈሩ፤ 20 በብንያም ሠራዊት ላይ አደጋ ለመጣል ሄዱ፤ ወታደሮቻቸውንም በጊብዓ ትይዩ አሰለፉ፤ 21 የብንያም ሠራዊት ከከተማይቱ ወጥቶ ቀኑ ከመምሸቱ በፊት ኻያ ሁለት ሺህ የእስራኤላውያንን ወታደሮች ገደለ፤ 22 የእስራኤልም ሠራዊት ተበራቱ፤ በመጀመሪያው ቀን በተሰለፉበትም ስፍራ ደግመው ተሰለፉ፤ 23 እስራኤላውያንም ወጥተው በእግዚአብሔር ፊት እስከ ማታ ድረስ አለቀሱ፤ እግዚአብሔርንም “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን ለመውጋት እንደገና እንዝመትን?” ብለው ጠየቁት፤ እግዚአብሔርም፦ “አዎ፥ በእነርሱ ላይ ዝመቱ” አላቸው። 24 በሁለተኛውም ቀን በብንያም ሠራዊት ላይ ዘመቱ፤ 25 እንዲሁም ብንያማውያን በሁለተኛው ቀን ከጊብዓ ወጡ፤ በዚህም ጊዜ ዐሥራ ስምንት ሺህ የሠለጠኑ የእስራኤላውያንን ወታደሮች ገደሉ፤ 26 ከዚህም በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ወደ ቤትኤል ሄደው አለቀሱ፤ በዚያም ምንም ሳይበሉ እስከ ምሽት በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጠው ቈዩ፤ የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕት አቀረቡ፤ 27 በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት በቤቴል ስለ ነበረ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ጠየቁ። 28 በዚያን ዘመን የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ስለ ነበረ እግዚአብሔርን ጠየቀ፦ “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን ለመውጋት እንደገና እንውጣን ወይስ እንቅር” ብሎ ጠየቀ። እግዚአብሔርም፥ “ነገ በእነርሱ ላይ ድልን እንድትቀዳጁ አደርጋለሁና ሂዱና ውጉአቸው!” አለ። 29 ስለዚህ እስራኤላውያን ጥቂት ወታደሮችን በጊብዓ ዙሪያ እንዲሸምቁ አደረጉ፤ 30 ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሁሉ በሦስተኛው ቀን በብንያም ሠራዊት ላይ ዘመቱ፤ ወታደሮቻቸውንም በጊብዓ ትይዩ አሰለፉአቸው። 31 ብንያማውያን ሠራዊቱን እየተከተሉ በወጡ ጊዜ ከከተማው ርቀው ሄዱ፤ በዋናው መንገድ ላይ እንደበፊቱ በሠራዊቱ ላይ አደጋ መጣል ጀመሩ፤ ወደ ቤትኤልና ወደ ጊብዓ በሚወስዱት መንገዶችና በሜዳው ላይ ሠላሳ እስራኤላውያንን ገደሉ። 32 ብንያማውያንም “ልክ ከዚህ በፊት እንዳደረግነው ፈጀናቸው” አሉ። እስራኤላውያን ግን “ወደ ኋላ አፈግፍገን ከከተማው ወደ አውራ ጐዳናው እናስወጣቸው” አሉ። 33 ዋናው የእስራኤል ሠራዊት ወደ በዓልታማር አፈገፈጉ፤ በጊብዓ ሜዳ ሸምቀው የነበሩት እስራኤላውያንም ድንገት ብቅ አሉ። 34 ከእስራኤል በልዩ ሁኔታ የተመረጡት ዐሥር ሺህ ሰዎች በጊብዓ ላይ አደጋ ጣሉ፤ ውጊያውም ከባድ ሆነ፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ብንያማውያን በቅርብ ጊዜ ችግር እንደሚደርስባቸው አልተገነዘቡም ነበር። 35 እግዚአብሔርም እስራኤልን በብንያማውያን ላይ ድልን እንዲቀዳጁ አደረገ። በዚያን ቀን እስራኤላውያን ከብንያም ወገን ኻያ አምስት ሺህ አንድ መቶ የጦር መሣሪያ የታጠቁ ሠራዊትን ገደሉ። 36 በዚህም ጊዜ ብንያማውያን መሸነፋቸውን ተገነዘቡ። ይህም የሆነበት ምክንያት እስራኤላውያን በጊብዓ አካባቢ አስፍረዋቸው በነበሩ የሽምቅ ወታደሮች በመተማመን ወደ ኋላ አፈግፍገው ስለ ነበረ ነው። 37 ሸምቆም የነበረው ጦር መጥቶ በከተማው ውስጥ ያለውን ሰው ሁሉ በሰይፍ ገደሉ። 38 ሸምቀው የነበሩት ሰዎች በከተማው ብዙ የጢስ ደመና እንዲያስነሡ በዋናው የእስራኤል ሠራዊትና ሸምቀው በነበሩት ሰዎች መካከል የምልክት ስምምነት ተደርጎ ነበር። 39 በምልክቱም መሠረት በጦር ሜዳ የነበሩት እስራኤላውያን የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ይወስዳሉ፤ እስከ አሁን ብንያማውያን ሠላሳ እስራኤላውያንን በመግደላቸው “ከዚህ በፊት እንዳደረግነው አሁንም ፈጀናቸው!” እያሉ ይደነፉ ነበር። 40 ከዚህም በኋላ ምልክቱ ታየ፤ ይኸውም ጢሱ እንደ ደመና ሆኖ እየተትጐለጐለ ወደ ላይ ይወጣ ነበር፤ ብንያማውያንም ወደኋላቸው ሲመለከቱ ከተማይቱ በሙሉ በእሳት ተያይዛ ነበልባሉ ወደ ላይ ሲወጣ አዩ፤ 41 እስራኤላውያንም የመልሶ ማጥቃት እርምጃቸውን በወሰዱ ጊዜ፥ ጨርሰው መደምሰሳቸውን ስለ ተገነዘቡ ብንያማውያን በፍርሃት ተሸበሩ፤ 42 ከእስራኤላውያንም ፊት አፈግፍገው ወደ በረሓው ሸሹ፤ ነገር ግን ማምለጥ አልቻሉም፤ በዋናው ሠራዊትና አሁን ከከተማው ውስጥ በመውጣት ላይ ባሉት ወታደሮች መካከል ተይዘው ተደመሰሱ። 43 እስራኤላውያን ብንያማውያንን ከበው በጊብዓ በስተ ምሥራቅ እስከሚገኘው ስፍራ ድረስ አሳደው ፈጁአቸው። 44 ከብንያማውያን ምርጥ ወታደሮች ዐሥራ ስምንት ሺህ ተገደሉ፤ 45 የቀሩት ወደ ኋላቸው ተመልሰው ወደ በረሓው፥ ወደ ሪሞን አለት በሸሹ ጊዜ በአውራው ጐዳና ላይ አምስት ሺህ ተገደሉ፤ እስከ ጊድዖም ድረስ ተሳደው ሁለት ሺህ ተገደሉ። 46 በዚያን ቀን በአጠቃላይ የተገደሉት ብንያማውያን ኻያ አምስት ሺህ ሲሆኑ ሁሉም ምርጥ ጦረኞች ነበሩ። 47 ነገር ግን ወደ በረሓው፥ የሪሞን አለት ተብሎ ወደሚጠራው ስፍራ በመሸሽ ለማምለጥ የቻሉት ስድስት መቶ ሰዎች ብቻ ነበሩ። እነርሱም በዚያ አራት ወር ቈዩ። 48 እስራኤላውያን ወደ ኋላ ተመልሰው በቀሩት ብንያማውያን ላይ አደጋ በመጣል ወንዶችንም ሴቶችንም ልጆችንና እንዲሁም እንስሶችን ጭምር ያገኙትን በሙሉ ገደሉ፤ በዚያ አካባቢ ያሉትን ከተሞች ሁሉ በእሳት አቃጠሉ። |