መሳፍንት 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእግዚአብሔር መልአክ በቦኪም 1 የእግዚአብሔር መልአክ ከጌልጌላ ወደ ቦኪም ሄዶ እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ከግብጽ ምድር አውጥቼ ለቀድሞ አባቶቻችሁ ልሰጣቸው ቃል ወደገባሁላቸው ምድር አመጣኋችሁ፤ እንዲህም አልኩ፦ ‘ከእናንተ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ከቶ አላፈርስም፤ 2 እናንተ በዚች ምድር ከሚኖሩ ሕዝብ ጋር ምንም ዐይነት ቃል ኪዳን አታድርጉ፤ መሠዊያዎቻቸውንም አፍርሱ፤’ እናንተ ግን አልታዘዛችሁኝም፤ ይህንስ ያደረጋችኹት ለምንድን ነው? 3 ስለዚህ አሁን እነዚህን ሕዝቦች ከፊታችሁ እንደማላስወጣቸው እነግራችኋለሁ፤ እነርሱ ለእናንተ ጠላቶች ይሆናሉ፤ ባዕዳን አማልክታቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል።” 4 የእግዚአብሔርም መልአክ ይህን በተናገረ ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ 5 ያ ስፍራ “ቦኪም” ተብሎ የተጠራውም በዚህ ምክንያት ነው፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ። የኢያሱ መሞት 6 ኢያሱ ሕዝቡን ባሰናበተ ጊዜ እስራኤላውያን ሁሉ የየራሳቸውን ድርሻ ለመያዝ ወደየተመደበላቸው ርስት ሄዱ። 7 በኢያሱ ዘመንና በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ታላቅ ሥራ ባዩት ሽማግሌዎች የሕይወት ዘመን ሁሉ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አመለከ። 8 የእግዚአብሔር አገልጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሆነው ሞተ፤ 9 የራሱ ድርሻ በሆነውም ርስት ተቀበረ፤ ይህም እርሱ የተቀበረበት ምድር በኮረብታማው የኤፍሬም አገር ከጋዓሽ ተራራ በስተሰሜን የሚገኘውና “ቲምናት ሴራሕ” ተብሎ የሚጠራው ነው። 10 ያ ትውልድ በሙሉ ሞተ፤ ከዚያ ቀጥሎ እግዚአብሔርንና ለእስራኤል ያደረገውን መልካም ነገር የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሣ። የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን ማምለክ መተዋቸው 11 ከዚህ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ክፉ ሥራ በመሥራት እግዚአብሔርን በደሉ። በዓሊም ተብለው የሚጠሩትን ባዕዳን አማልክት አመለኩ፤ 12 ከግብጽ ያወጣቸውን የቀድሞ አባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ማገልገል ተዉ፤ በዚህም ፈንታ በዙሪያቸው ያሉ ሕዝቦች የሚያመልኩአቸውን የውሸት አማልክትን ማገልገል ጀመሩ፤ ለእነርሱም በመስገድ እግዚአብሔርን አስቈጡት። 13 እግዚአብሔርን ማምለክ ትተው “ባዓልና ዐስታሮት” ተብለው የሚጠሩትን ባዕዳን አማልክት አመለኩ፤ 14 ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ በጣም ተቈጣ፤ እንዲዘርፉአቸውም ለወራሪዎች አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዙሪያቸው ያሉ ጠላቶቻቸውም እንዲበረቱባቸው አደረገ። ከዚያም በኋላ እስራኤላውያን ከጠላቶቻቸው ወረራ ራሳቸውን መከላከል ተሳናቸው። 15 ወደ ጦርነት በሄዱም ቊጥር ቀደም ብሎ በመሐላ በተናገረው መሠረት እግዚአብሔር ራሱ ይቃወማቸው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ እነርሱ በብርቱ ጭንቀት ላይ ወደቁ። 16 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ከወራሪዎቻቸው እጅ የሚያድኑአቸውን መሳፍንት ተብለው የሚጠሩ መሪዎችን አስነሣላቸው። 17 ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ ለመሪዎቻቸው የማይታዘዙ ሆኑ፤ ለእግዚአብሔርም ያላቸውን ታማኝነት አጓድለው የሌሎች ባዕዳን አማልክት አገልጋዮች ሆኑ፤ አባቶቻቸው የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ያከብሩ ነበር፤ እነርሱ ግን የአባቶቻቸውን ምሳሌ አልተከተሉም። 18 እግዚአብሔር መስፍን ባስነሣላቸው ጊዜ ሁሉ እርሱ ከመስፍኑ ጋር ነበር፤ በሚያሳድዱአቸውና በሚጨቊኑአቸው ጠላቶች ምክንያት ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር በሚጮኹበት ጊዜ እግዚአብሔር ያዝንላቸው ስለ ነበረ በመስፍኑ ዘመን ሁሉ ከጠላቶቻቸው እጅ ያድናቸው ነበር። 19 ነገር ግን መሪ በሚሞትበት ጊዜ ሁሉ ተመልሰው ሌሎች አማልክትን በመከተል፥ ለእነርሱም በመስገድና እነርሱንም በማምለክ ከአባቶቻቸው የከፋ በደል ይፈጽሙ ነበር፤ መጥፎ ድርጊታቸውንና ልበ ደንዳና መሆናቸውን አልተዉም። 20 ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እጅግ ተቈጥቶ እንዲህ አለ፦ “ይህ ሕዝብ ከአባቶቹ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አፈረሰ፤ ትእዛዜን አልጠበቀም። 21 ስለዚህ ኢያሱ በሞተ ጊዜ በምድሪቱ የነበሩትን ሰዎች አንዳቸውንም አላስወጣላቸውም። 22 እንዲያውም እነዚህ የእስራኤል ሕዝብ እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው መንገዴን ይከተሉ ወይም አይከተሉ እንደሆን የማውቀው በእነዚህ ሕዝቦች መሣሪያነት በመፈተን ነው።” 23 ስለዚህ እግዚአብሔር ለኢያሱ አሳልፎ በመስጠት እነዚያን ሕዝቦች በአንድ ጊዜ አላስወጣቸውም። |