Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

መሳፍንት 19 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


አንድ ሌዋዊና የእርሱ ቊባት

1 በእስራኤል ገና ንጉሥ ባልነበረበት ጊዜ በኮረብታማው በኤፍሬም አገር ራቅ ብሎ በሚገኝ ስፍራ የሚኖር አንድ ሌዋዊ ነበረ፤ ይህ ሰው በይሁዳ ግዛት ከምትገኘው ከቤተልሔም አንዲት ልጃገረድ ቊባት ወስዶ ነበር፤

2 ነገር ግን ልጅቱ ከእርሱ ጋር ተጣልታ በቤተልሔም ወደሚገኘው ወደ አባቷ ቤት ኮብልላ ሄደች፤ በዚያም አራት ወር ቈየች።

3 ዘግየት ብሎም ሰውየው ወደ ልጅቱ ለመሄድና በማግባባት መልሶ ሊያመጣት ቊርጥ ውሳኔ አደረገ፤ ሲሄድም አገልጋዩንና ሁለት አህዮች ይዞ ነበር፤ እዚያም በደረሰ ጊዜ ልጅቱ ተቀብላ ወደ ቤት አስገባችው፤ የልጅቱም አባት ሰውየውን ባየው ጊዜ በደስታ ተቀበለው፤

4 እዚያ እንዲቈይ አደረገው፤ እርሱም ሦስት ቀን በዚያ ቈየ፤ እዚያም እየበሉና እየጠጡ ቈዩ።

5 በአራተኛው ቀን ጧት በማለዳ ተነሡና ለመሄድ ተዘጋጁ፤ የልጅቱ አባት ግን የልጁን ባል “ብርታት እንድታገኝ መጀመሪያ እህል ቅመስ፤ ከዚያም በኋላ ትሄዳለህ” አለው።

6 ስለዚህ ሁለቱ ሰዎች ተቀምጠው አብረው ተመገቡ፤ የሴቲቱም አባት ሌዋዊውን “እባክህ ዛሬ ደስ ብሎህ እዚሁ ዕደር” አለው።

7 ሌዋዊው ለመሄድ ተነሣ፤ የልጅቱ አባት ግን እንዲቈይ አግባባውና ያንን ሌሊት በዚያው አሳለፈ፤

8 በአምስተኛው ቀን ጧት በማለዳ ተነሥቶ ጒዞ ጀመረ፤ የልጅቱ አባት ግን “እባክህ እህል ቅመስ፤ ቈየት ብለህ ትሄዳለህ” አለው፤ ስለዚህም ሁለቱ ሰዎች አብረው በሉ።

9 ሌዋዊውና ቊባቱ እንዲሁም አገልጋዩ ሆነው እንደገና ጒዞ ሲጀምሩ የልጅቱ አባት እንዲህ አለ፤ “ተመልከቱ! እነሆ ጊዜው መሽቶአል፤ ሌሊቱን እዚሁ ብታሳልፉ ይሻላል፤ አሁን ፈጥኖ ይጨልማል፤ እዚሁ ደስ ብሎአችሁ ዕደሩ፤ ነገ በማለዳ ተነሥታችሁ ጒዞ በመጀመር ወደ ቤታችሁ ትሄዳላችሁ።”

10 ሌዋዊው ግን ያንን ሌሊት እዚያ ለማሳለፍ አልፈለገም፤ ስለዚህ እርሱ፥ ቊባቱና አገልጋዩ ተነሥተው ጒዞ ጀመሩ፤ ኮርቻ የተጫኑ ሁለት አህዮችም ነበሩአቸው፤ ቀኑም በመሸ ጊዜ የቡስ ተብላ ትጠራ ወደነበረችው ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ አጠገብ ደረሱ፤

11 ወደ ኢያቡስ በደረሱ ጊዜ መሸባቸው፤ አሽከሩም ጌታውን “ና እባክህ ወደ እዚህ ወደ ኢያቡሳውያን ከተማ እንመለስና እዚያ እንደር” አለው።

12 ጌታው ግን “እስራኤላውያን በማይኖሩባት ከተማ አንቆምም፤ ይህን ስፍራ አልፈን ሄደን በጊብዓ እንደር” ብሎ መለሰለት፤

13 አሽከሩንም “ና ከእነዚህ ቦታዎች ወደ አንዱ እንቅረብ፤ በጊብዓ ወይም በራማ እንደር” አለው።

14 ስለዚህ ኢየሩሳሌምን አልፈው ጒዞአቸውን ወደፊት ቀጠሉ፤ በብንያም ግዛት በምትገኘው በጊብዓ ሲደርሱ ፀሐይ ጠለቀች፤

15 የሚያድሩበትንም ስፍራ ፈልገው ለማግኘት ከመንገድ ወጣ አሉ፤ ወደ ከተማይቱም ገብተው በአደባባዩ አጠገብ ተቀመጡ፤ ነገር ግን ወደ ቤት ወስዶ የሚያሳድራቸው ማንንም አላገኙም።

16 በዚያም ተቀምጠው ሳሉ በእርሻ ቦታ የቀን ሥራውን ፈጽሞ ወደ ቤቱ የሚመለስ አንድ ሽማግሌ በአጠገባቸው አለፈ፤ ይህ ሰው አስቀድሞ ከኮረብታማው ከኤፍሬም አገር የመጣ ሲሆን፥ አሁን ግን የሚኖረው በጊብዓ ነበር፤ በዚያ የሚኖሩት ሌሎቹ ሰዎች ግን ከብንያም ነገድ የተወለዱ ናቸው፤

17 ሽማግሌውም በከተማይቱ አደባባይ የተቀመጠውን ሰው አይቶ “ከየት መጣህ? የምትሄደውስ ወዴት ነው?” ሲል ጠየቀው።

18 ሌዋዊውም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “በይሁዳ በምትገኘው በቤተልሔም ነበርን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤትና በኮረብታማው በኤፍሬም አገር ራቅ ብሎ ወደሚገኘው ቤታችን ለመድረስ በጒዞ ላይ ነን፤ ወደ ቤቱ ወስዶ የሚያሳድረን እስከ አሁን አላገኘንም፤

19 እኛ ግን ለአህዮቻችን ገፈራና ገለባ፥ ለቊባቴና ለእኔ እንዲሁም ለአገልጋዬ እንጀራና የወይን ጠጅ አለን፤ የሚያስፈልገንን ሁሉ ይዘናል፤ ምንም ያጣነው ነገር የለም” አለው።

20 ሽማግሌውም “ሰላም ለአንተ ይሁን! እነሆ ወደ ቤቴ ግባ! እኔ ማደሪያ አዘጋጅልሃለሁ፤ በዚህ አደባባይ ላይ ማደር አይገባህም” አለ።

21 ስለዚህ ወደ ቤት ወሰዳቸውና ለአህዮቹ ገፈራ መገበለት፤ እንግዶቹም እግራቸውን ታጥበው ራታቸው በሉም ጠጡ።

22 እየተደሰቱ ሳለም ከከተማይቱ የመጡ ጋጠወጦች በድንገት ቤቱን ከበው በሩን መደብደብ ጀመሩ፤ ሽማግሌውንም “ያንን ወደ ቤትህ የገባውን ሰው ግብረ ሰዶም እንድንፈጽምበት አውጣልን!” አሉት።

23 ሽማግሌው ግን ወደ ውጪ ወጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “አይሆንም ወዳጆቼ ሆይ! እባካችሁ ይህን የመሰለ አስከፊ ነገር አታድርጉ! ይህ ሰው የእኔ እንግዳ ነው፤

24 እነሆ የሰውዬው ቊባትና ድንግል የሆነችውን የእኔንም ሴት ልጅ! አውጥቼ ልስጣችሁ፤ ተጠቀሙባቸው፤ የምትፈልጉትንም ነገር አድርጉባቸው፤ በዚህ ሰው ላይ ግን ክፉ ነገር አታድርጉ!” አላቸው።

25 ሰዎቹ ግን አልሰሙትም፤ ስለዚህ ሰውዬው ቊባቱን ወደ ውጪ አውጥቶ ሰጣቸው፤ ሌሊቱንም ሙሉ በእርስዋ ላይ ተራ በተራ በማመንዘር መጫወቻ አድርገዋት ዐደሩ፤ ሲነጋጋ ግን እንድትሄድ ለቀቁአት።

26 ጧትም ጎሕ ሲቀድ ያቺ ሴት መጥታ ባልዋ ባደረበት በሽማግሌው ቤት በር አጠገብ ወደቀች፤ ፀሐይ እስክትወጣም ድረስ በዚያ ነበረች፤

27 በዚያም ጧት ባልየው ጒዞውን ለመቀጠል በሩን ሲከፍት ቊባቱ እጅዋን ወደ በሩ እንደ ዘረጋች በቤቱ ፊት ለፊት ወድቃ አገኛትና፥

28 “ተነሽ እንሂድ!” አላት፤ ነገር ግን ምንም መልስ አላገኘም፤ ከዚህ በኋላ ሬሳዋን በአህያ ላይ ጭኖ ወደ ቤቱ ጒዞውን ቀጠለ፤

29 እዚያም በደረሰ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ፤ ቢላዋም አንሥቶ የቊባቱን ሬሳ ዐሥራ ሁለት ቦታ ቈራረጠው፤ ወደ እስራኤል አገር ሁሉ ለዐሥራ ሁለቱ ነገዶች አንዳንድ ቊራጭ ላከ፤

30 ከዚያ በኋላ የላካቸውን ሰዎች እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “ለእስራኤላውያን ሁሉ እንዲህ በሉአቸው፦ ‘የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲህ ያለ ነገር ተደርጎ ያውቃልን? አስቡበት፤ ተመካከሩበት ተነጋገሩበትም።’ ” ያዩት ሁሉ “እስከዚህ ጊዜ ድረስ እንዲህ ያለ ነገር ታይቶም አይታወቅ!” አሉ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告