መሳፍንት 18 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሚካና የዳን ነገድ 1 በዚያም ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ በእስራኤል ነገዶች መካከል የራሳቸው የሆነ የርስት ድርሻ ገና ያላገኙ ስለ ነበሩ የዳን ነገድ ተወላጆች የሚሰፍሩበትን ርስት ለማግኘት በመፈለግ ላይ ነበሩ። 2 ስለዚህ የዳን ሕዝብ ከነገዱ ቤተሰቦች መካከል ብርታት ያላቸውን አምስት ሰዎች መረጡ፤ ምድሪቱንም አጥንተው እንዲመለሱ መመሪያ በመስጠት ከጾርዓና ከኤሽታኦል ከተሞች ላኩአቸው፤ እነርሱም ኮረብታማ ወደ ሆነው ወደ ኤፍሬም አገር በደረሱ ጊዜ በሚካ ቤት አደሩ፤ 3 እዚያም በነበሩበት ጊዜ ወጣቱን ሌዋዊ በአነጋገሩ ሁኔታ ከየት እንደ ሆነ ለይተው ዐወቁት፤ ወደ እርሱም ቀርበው “እዚህ ምን ትሠራለህ፤ ወደዚህ ያመጣህስ ማነው?” ሲሉ ጠየቁት። 4 እርሱም “ደሞዝ እየከፈለኝ ካህን ሆኜ ላገለግለው ከሚካ ጋር ተስማምቻለሁ” ሲል መለሰላቸው። 5 እነርሱም “ጒዞአችን ይሳካልን እንደ ሆነ እባክህ እግዚአብሔርን ጠይቅልን” አሉት። 6 ካህኑም፦ “ሂዱ በጒዞአችሁ ምንም ችግር አይገጥማችሁም፥ እግዚአብሔር ይጠብቃችኋል” ሲል መለሰላቸው። 7 ከዚህ በኋላ አምስቱ ሰዎች ከዚያ ሄደው ወደ ላዪሽ ደረሱ፤ በዚያም የነበሩት ኗሪዎች ልክ እንደ ሲዶናውያን በሰላም የሚኖሩ መሆናቸውን ተመለከቱ፤ ሕዝቡም ከማንም ጋር ሳይጋጩ ጸጥ ባለ መንፈስ የሚኖሩ ሰላም ወዳዶች ነበሩ፤ ከዚህም ጋር ከሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ምንም የሚጐድላቸው አልነበረም፤ ከዚህም የተነሣ ከማንኛውም ሕዝብ ጋር ግንኙነት ሳይኖራቸው ከሲዶናውያን በመራቅ ተገልለው ይኖሩ ነበር። 8 አምስቱም ሰዎች ወደ ጾርዓና ወደ ኤሽታኦል በተመለሱ ጊዜ ወገኖቻቸው፦ “ምን ወሬ አላችሁ?” ብለው ጠየቁአቸው። 9 እነርሱም እንዲህ አሉአቸው፦ “እንግዲህ ኑ! በላዪሽ ላይ አደጋ እንጣል! ምድሪቱ በጣም ጥሩ መሆንዋን አይተናል፤ እዚህ ያለ ሥራ ቦዝናችሁ አትቀመጡ፤ ይልቅስ በፍጥነት ሄዳችሁ ያዙአት! 10 ወደዚያም በምትሄዱበት ጊዜ ምንም የማይጠራጠሩ ሰላም ወዳዶች ሆነው ታገኙአቸዋላችሁ፤ አገሪቱ ታላቅ ናት፤ ለሰው የሚያስፈልገው ማናቸውም ነገር በውስጥዋ ይገኛል፤ እግዚአብሔር ይህችን አገር ለእናንተ ሰጥቶአችኋል።” 11 ስለዚህ ከዳን ነገድ የጦር መሣሪያ የታጠቁ ስድስት መቶ ሰዎች ከጾርዓና ከኤሽታኦል ተነሡ፤ 12 እነርሱም ወጥተው በይሁዳ በምትገኘው ከቂርያትይዓሪም በስተ ምዕራብ ሰፈሩ፤ ያ ስፍራ እስከ አሁን የዳን ሰፈር ተብሎ የሚጠራውም ስለዚህ ነው። 13 ከዚያም ጒዞአቸውን በመቀጠል በኮረብታማው በኤፍሬም አገር ወደሚገኘው ወደ ሚካ ቤት መጡ። 14 በላዪሽ ዙሪያ ያለውን አገር ሊያጠኑ ተልከው የነበሩት አምስት ሰዎች ለጓደኞቻቸው “በዚህ ስፍራ ከነዚህ ቤቶች በአንዱ ውስጥ በብር የተለበጠ የእንጨት ጣዖት እንዳለ ታውቃላችሁን? ሌሎች ጣዖቶች አንድ ኤፉድም በተጨማሪ አለ፤ ታዲያ ምን ማድረግ የሚገባን ይመስላችኋል?” አሉአቸው። 15 ወጣቱ ሌዋዊ ወደሚኖርበትም ወደ ሚካ ቤት ገቡ፤ ሌዋዊውንም እንዴት እንደሚኖር ጠየቁት፤ 16 የጦር መሣሪያ የታጠቁት ከዳን የመጡት ስድስት መቶ ሰዎች በዚያን ጊዜ በቅጽሩ በር አጠገብ ቆመው ነበር። 17 አምስቱም ሰላዮች በቀጥታ ወደ ሚካ ቤት ገብተው ያንን በብር የተለበጠ የእንጨት ጣዖትና ሌሎቹንም ጣዖቶች ኤፉዱንም ጭምር ወሰዱ፤ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ካህኑ የጦር መሣሪያ ከታጠቁት ስድስት መቶ ሰዎች ጋር በቅጽር በሩ አጠገብ ቆሞ ነበር። 18 እርሱም ሰዎቹ ወደ ሚካ ቤት ሄደው ምስሎቹንና ኤፉዱን በሚወስዱበት ጊዜ “ምን ማድረጋችሁ ነው?” ሲል ጠየቃቸው። 19 እነርሱም “ዝም በል! አፍህን ዝጋ፤ ይልቅስ መጥተህ ካህናችንና አማካሪያችን ሁን፤ የአንድ ሰው ቤተሰብ ካህን ከምትሆን የአንድ እስራኤላዊ ነገድ ካህን መሆን አይሻልህምን?” አሉት። 20 ይህም አባባል ካህኑን እጅግ ስላስደሰተው ጣዖቶቹንና ኤፉዱን ይዞ ከእነርሱ ጋር ሄደ። 21 እነርሱም ልጆቻቸውን ከብቶቻቸውንና ዕቃቸውን ሁሉ ከፊት አስቀድመው ወደ ኋላ በመመለስ ጒዞአቸውን ቀጠሉ። 22 ከቤቱ ራቅ ብለው ከሄዱ በኋላ ሚካ ጐረቤቶቹን ሰብስቦ በመከተል ከዳን የመጡትን ሰዎች ደረሰባቸውና፤ 23 ደነፋባቸው፤ ከዳን የመጡትም ሰዎች ወደ ኋላ መለስ ብለው ሚካን “ምን ሆነሃል? ይህን ሁሉ ሰውስ የሰበሰብከው ለምንድነው?” ሲሉ ጠየቁት። 24 ሚካም “እንዴት ‘ምን ሆነሃል’ ትሉኛላችሁ? የሚያገለግለኝን ካህንና እኔ የሠራኋቸውን ጣዖቶች ዘርፋችሁ ሄዳችሁ፤ ታዲያ እኔ ምን ተረፈኝ?” አላቸው። 25 ከዳን የመጡትም ሰዎች “የተቈጡ ሰዎች አደጋ እንዳይጥሉብህና የአንተንና የቤተሰብህን ሕይወት እንዳታጣ በመካከላችን ምንም ድምፅ ባታሰማ ይሻልሃል” አሉት። 26 ከዚህም በኋላ ጒዞአቸውን ቀጠሉ፤ ሚካም ሊቋቋማቸው እንደማይችል ባየ ጊዜ ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ። 27 ከዳን የመጡትም ሰዎች ሚካ የሠራውን ጣዖትና ያገለግለው የነበረውን ካህን ይዘው ጸጥ ብሎ ተዝናንቶ ወደ ተቀመጠው ሕዝብ ወደ ላዪሽ መጡ፤ ሕዝቡንም በሰይፍ ፈጁ፤ ከተማይቱንም በእሳት አቃጠሉ። 28 የላይሽ ሕዝብ ከማንም ጋር ግንኙነት ስላልነበራቸውና ከሲዶንም ርቀው ይኖሩ ስለ ነበረ የሚያድናቸው አልተገኘም። ከተማዋ በቤትረሖብ አጠገብ በሚገኝ ሸለቆ ውስጥ ነበረች፤ የዳን ሰዎችም ከተማዋን እንደገና ሠርተው ኖሩባት። 29 የቀድሞ ስምዋንም ላይሽን ለውጠው የቀድሞው አባታቸው በነበረው በያዕቆብ ልጅ ስም ዳን ብለው ጠሩአት፤ 30 የዳን ሰዎችም ያመልኩት ዘንድ ያን ጣዖት በዚያ አኖሩ፤ ከሙሴ ልጅ ከጌርሾም የተወለደው ዮናታንም ለዳን ነገድ ካህን ሆኖ ማገልገል ጀመረ። የእርሱም ዘሮች ሕዝቡ ተማርከው እስከ ተሰደዱበት ጊዜ ድረስ ማገልገላቸውን ቀጠሉ። 31 በዚህም ዐይነት የሚካ ጣዖት እግዚአብሔር የሚመለክበት ድንኳን በሴሎ እስከ ነበረበት ዘመን በዚያው ቈየ። |