መሳፍንት 17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሚካ ያሠራቸው ጣዖቶች 1 ሚካ ተብሎ የሚጠራ አንድ ሰው በኮረብታማው በኤፍሬም አገር ይኖር ነበር፤ 2 እርሱም አንድ ቀን እናቱን እንዲህ አላት፤ “አንድ ሰው አንድ ሺህ አንድ መቶ ጥሬ ብር በሰረቀሽ ጊዜ ያን የሰረቀሽን ሰው ስትረግሚው ሰምቼሽ ነበር፤ እነሆ ያ ብር በእኔ እጅ ነው፤ እርሱንም የወሰድኩ እኔ ነበርኩ።” እናቱም “ልጄ! እግዚአብሔር ይባርክህ!” አለችው። 3 ልጁም ገንዘቡን መልሶ ለእናቱ ሰጣት፤ እርስዋም “እኔ ራሴ ብሩን ለእግዚአብሔር ስለ ልጄ የተለየ አደርገዋለሁ፤ ከእንጨት ተሠርቶ በብር የተለበጠ ጣዖት ማሠሪያም ይሆናል፤ ስለዚህ ብሩን ለአንተ መልሼ እሰጥሃለሁ” አለችው። 4 ልጁም ብሩን ለእናቱ ሰጣት፤ እርስዋም ከላዩ ሁለት መቶ ብር አንሥታ እንጨት ጠርቦ በብሩ በመለበጥ ጣዖት ለሚሠራላት የብር አንጥረኛ ሰጠችው፤ ጣዖቱም በሚካ ቤት ተቀመጠ። 5 ይህ ሚካ የተባለ ሰው የራሱ የሆነ የአምልኮ ስፍራ ነበረው፤ በርከት ያሉ ጣዖቶች አንድ ኤፉድ ሠርቶ ከልጆቹ አንዱን ካህን ሆኖ እንዲያገለግለው ሾመው፤ 6 በዚያን ጊዜ በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ እያንዳንዱም ሰው ለራሱ ደስ ያለውን ነገር ሁሉ እንደ ፈለገ ያደርግ ነበር። 7 በዚያን ወቅት በይሁዳ ግዛት በቤተልሔም ከተማ የሚኖር አንድ ወጣት ሌዋዊ ነበር፤ 8 ይህም ሰው የሚኖርበትን ስፍራ ለማግኘት ከቤተልሔም ተነሥቶ ሄደ፤ በጒዞም ላይ ሳለ በኮረብታማው በኤፍሬም አገር ወደሚገኘው ወደ ሚካ ቤት መጣ፤ 9 ሚካም “ከወዴት መጣህ?” አለው። እርሱም “እኔ በይሁዳ ግዛት ከምትገኘው ከቤተልሔም የመጣሁ ሌዋዊ ነኝ፤ የምኖርበትን ስፍራ እየፈለግሁ ነው” ሲል መለሰለት። 10 ሚካም “እንግዲያውስ ከእኔ ጋር ኑር፤ የእኔ አማካሪና ካህን ሁንልኝ፤ በዓመት ዐሥር ብር እንዲሁም ልብስና ምግብ እሰጥሃለሁ” አለው። 11 ወጣቱ ሌዋዊም ከሚካ ጋር ለመኖር ተስማማ፤ ያም ወጣት ካህን ለሚካ እንደ ልጅ ሆነለት፤ 12 ሚካም እርሱን ካህን አድርጎ ሾመው፤ በቤቱም ተቀመጠ። 13 ሚካም “እንግዲህ ሌዋዊ ካህን ካገኘሁ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር እንደሚያሳካልኝ ዐውቃለሁ” አለ። |