Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

መሳፍንት 14 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የሶምሶን ጋብቻ

1 አንድ ቀን ሶምሶን ወደ ቲምና ወረደ፤ በዚያም አንዲት ፍልስጥኤማዊት ሴት አየ፤

2 ወደ ቤቱም ተመልሶ ለአባቱና ለእናቱ “በቲምና ከፍልስጥኤማውያን ሴቶች ልጆች አንድዋን አይቼ ወድጃታለሁ፤ ስለዚህ እርስዋን አጭታችሁ አጋቡኝ” አላቸው።

3 አባቱና እናቱ ግን “ሚስት ለማግኘት ወደ አልተገረዙ ፍልስጥኤማውያን ዘንድ ሄደህ ሚስት የምትፈልገው ከወገንህ ወይም በሕዝባችን መካከል ሴት ልጅ የሌለች ሆኖ ነውን?” ሲሉ ጠየቁት። ሶምሶን ግን አባቱን “እኔ እርስዋን በጣም ስለ ወደድኳት ከእርስዋ ጋር አጋባኝ” አለው።

4 ሶምሶን ይህን እንዲያደርግ የሚመራው እግዚአብሔር እንደ ሆነ ወላጆቹ አላወቁም፤ በዚያም ጊዜ ፍልስጥኤማውያን እስራኤላውያንን ይገዙ ስለ ነበር፥ እግዚአብሔር ፍልስጥኤማውያንን ለመቃወም ምክንያት ይፈልግ ነበር።

5 ከዚህ በኋላ ሶምሶን ከአባቱና ከእናቱ ጋር ወደ ቲምና ወረደ፤ እዚያም በወይን ተክል ውስጥ አልፈው ሲሄዱ አንድ ደቦል አንበሳ እያገሣ መጣበት፤

6 በድንገትም የእግዚአብሔር መንፈስ ሶምሶንን አበረታው፤ ስለዚህም አንበሳውን እንደ አንድ የፍየል ጠቦት ያኽል በመቊጠር ያለ ምንም መሣሪያ በባዶ እጁ ገነጣጥሎ ጣለው፤ ያደረገውንም ነገር ለወላጆቹ አልነገራቸውም።

7 ከዚህ በኋላ ወደ ሴቲቱ ሄዶ አነጋገራት፤ ወደዳትም፤

8 ከጥቂት ቀኖች በኋላ እርስዋን ለማግባት ወደዚያ ተመልሶ ሄደ፤ በጒዞም ላይ ሳሉ ያንን የገደለውን አንበሳ ሁኔታ ለማየት ከመንገድ ዞር አለ፤ በድኑን ንቦች ሰፍረውበት በውስጡም ማር. መኖሩን በተመለከተ ጊዜ እጅግ ተደነቀ፤

9 ከማሩም ጥቂት በእጁ ቈርጦ እየበላ መንገዱን ቀጠለ፤ ወደ አባቱና ወደ እናቱ ቀርቦ ከያዘው ማር. ሰጥቶአቸው በሉ፤ ነገር ግን ሶምሶን ያንን ማር. ያገኘው ከሞተው አንበሳ በድን ውስጥ መሆኑን አልነገራቸውም።

10 አባቱ ወደ ሴቲቱ ቤት በሄደ ጊዜ፥ ሶምሶን በዚያ ትልቅ ግብዣ አደረገ፤ ይህም ዐይነቱ ግብዣ በወጣቶች ዘንድ የተለመደ ነበር፤

11 ፍልስጥኤማውያን እርሱን ባዩት ጊዜ ከእርሱ ጋር እንዲቈዩ ሠላሳ ወንዶች ወጣቶችን መርጠው ላኩለት።

12 ሶምሶንም እንዲህ አላቸው፤ “እስቲ ታውቁ እንደ ሆነ አንድ እንቆቅልሽ ልንገራችሁ፤ በሰባቱ የሠርጉ በዓል ቀኖች ውስጥ ይህን እንቆቅልሽ ፈትታችሁ ብትነግሩኝ፥ ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ቅያሬ ልብስ እሰጣችኋለሁ፤

13 ፍቹን መንገር ባትችሉ ግን ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ቅያሬ ልብስ ትሰጡኛላችሁ።” እነርሱም “እንቆቅልሽህን ንገረን፤ እስቲ እንስማው” አሉት።

14 እርሱም “ከበላተኛው መብል ተገኘ፤ ከብርቱውም ጣፋጭ ነገር ወጣ” አላቸው። እስከ ሦስት ቀን ድረስ እንቆቅልሹን መፍታት አልቻሉም።

15 በአራተኛው ቀን የሶምሶንን ሚስት እንዲህ አሉአት፤ “ባልሽን አግባብተሽ የእንቆቅልሹን ፍች እንዲነግረን አድርጊ፤ ይህን ካላደረግሽ ግን የአባትሽን ቤት በእሳት አያይዘን አንቺንም በውስጡ በመጨመር እናቃጥልሻለን፤ ለካስ እናንተ ሁለታችሁም ወደ ግብዣችሁ የጠራችሁን ልትዘርፉን ኖሮአልን?”

16 ስለዚህ የሶምሶን ሚስት እያለቀሰች ወደ እርሱ ቀርባ “ለካስ አንተ እኔን አትወደኝም! እንዲያውም በጣም ትጠላኛለህ! የአገሬን ልጆች እንቆቅልሽ ጠይቀህ ለእኔ እስከ አሁን ፍቺውን አልነገርከኝም!” አለችው። እርሱም “እነሆ! እኔ ይህን ለአባቴና ለእናቴ እንኳ አልነገርኳቸውም፤ ታዲያ ለአንቺ የምነግርበት ምክንያት ምንድን ነው?” አላት።

17 ከዚህም የተነሣ እርስዋ በሠርጉ በዓል ሰባት ቀን ሙሉ አለቀሰች፤ አጥብቃም ስለ ነዘነዘችው የእንቆቅልሹን ፍች በሰባተኛው ቀን ነገራት፤ እርስዋም ሄዳ ለፍልስጥኤማውያኑ ነገረቻቸው።

18 ስለዚህ በሰባተኛው ቀን ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት፥ የከተማይቱ ሰዎች “ከማር የጣፈጠ፥ ከአንበሳስ የበረታ ምን አለ?” ሲሉ የእንቆቅልሹን ፍች ነገሩት። ሶምሶንም “በእኔ ጊደር ባታርሱ ኖሮ፥ መልሱን ማግኘት ባልቻላችሁም ነበር” አላቸው።

19 የእግዚአብሔርም መንፈስ ለእርሱ ብርታትን ሰጠው፤ ወደ አስቀሎናም ወርዶ ሠላሳ ሰዎችን ገደለ፤ ውብ የሆነውንም ልብሳቸውን ሁሉ በመግፈፍ አምጥቶ የእንቆቅልሹን ፍች ላወቁት ሰዎች ሰጣቸው። በሆነውም ነገር ሁሉ እጅግ ተቈጥቶ ወደ ቤተሰቦቹ ተመለሰ፤

20 ሚስቱም በሠርጉ ሚዜ ለነበረው ጓደኛው ተዳረች።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告