መሳፍንት 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየሶምሶን መወለድ 1 የእስራኤል ሕዝብ እንደገና እግዚአብሔርን በደሉ፤ ስለዚህም አርባ ዓመት ሙሉ እንዲገዙአቸው እግዚአብሔር ለፍልስጥኤማውያን አሳልፎ ሰጣቸው። 2 በዚያን ዘመን ጾርዓ በምትባል ከተማ የሚኖር ማኑሄ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ትውልዱ ከዳን ነገድ ነበር፤ ሚስቱ መኻን ስለ ነበረች ልጆች አልወለደችም፤ 3 ለእርስዋም የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ እንዲህ አላት፤ “አንቺ መኻን ነሽ፤ ልጆችም የሉሽም፤ ነገር ግን ትፀንሺአለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ 4 የወይን ጠጅም ሆነ ማንኛውንም የሚያሰክር መጠጥ ከመጠጣትና ማንኛውንም ርኩስ ምግብ ከመብላት ተጠንቀቂ። 5 በእርግጥ ትፀንሺአለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ልጁም ከተወለደበት ቀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ስለሚሆን የራስ ጠጒሩን ፈጽሞ አይላጭ፤ እርሱም እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ማዳን ይጀምራል።” 6 ከዚህ በኋላ ሴቲቱ መጥታ ለባልዋ እንዲህ አለችው፤ “አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጥቶ ነበር፤ መልኩም እንደ እግዚአብሔር መልአክ እጅግ የሚያስፈራ ነበር፤ እኔ ከወዴት እንደ መጣ አልጠየቅሁትም፤ እርሱም ስሙን አልነገረኝም፤ 7 ነገር ግን እርሱ ‘እነሆ ትፀንሺአለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ’ ብሎ ነገረኝ፤ እንዲሁም የሚወለደው ልጅ ከተወለደበት ቀን ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ በናዝራዊነት ለእግዚአብሔር የተለየ ስለሚሆን፥ የወይን ጠጅም ሆነ ማንኛውንም የሚያሰክር መጠጥ ከመጠጣትና ማንኛውንም ርኩስ ምግብ ከመብላት እንድጠነቀቅ ነግሮኛል።” 8 ከዚህ በኋላ ማኑሄ “እግዚአብሔር ሆይ! ሕፃኑ ሲወለድ ምን ማድረግ እንደሚገባን ይነግረን ዘንድ ያ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው እንደገና ተመልሶ ወደ እኛ እንዲመጣ አድርግልን” ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። 9 እግዚአብሔርም የማኑሄን ጸሎት ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ እንደገና ወጥቶ ሴቲቱ በእርሻ ውስጥ እንደ ተቀመጠች ተገለጠላት፤ ባልዋ ማኑሄ ከእርስዋ ጋር አልነበረም፤ 10 ስለዚህ በፍጥነት ወደ እርሱ ሮጣ በመሄድ “እነሆ! ያ ከዚህ በፊት ወደ እኔ መጥቶ የነበረው ሰው ዛሬም እንደገና ተገለጠልኝ” አለችው። 11 ማኑሄም ከተቀመጠበት ተነሥቶ ሚስቱን ተከትሎ ሄደ፤ ወደ ሰውየውም ቀርቦ “ከሚስቴ ጋር ተነጋግረህ የነበርከው አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው። ሰውየውም “አዎ! እኔ ነኝ” ሲል መለሰ። 12 ቀጥሎም ማኑሄ “የተናገርከው ቃል ሲፈጸም ለሚወለደው ልጅ ምን መደረግ አለበት?” ሲል ጠየቀው። 13 መልአኩም እንዲህ ሲል መለሰ፥ “ሚስትህ የነገርኳትን ሁሉ ነገር ለማድረግ ትኲረት መስጠት አለባት። 14 ከወይን ተክል የሚገኝ ምንም ነገር መመገብ አይኖርባትም፤ የወይን ጠጅም ሆነ ማንኛውንም የሚያሰክር መጠጥ አትጠጣ፤ ማንኛውንም ርኩስ ምግብ አትበላም፤ በአጠቃላይ እኔ ያዘዝኳትን ሁሉ መፈጸም አለባት።” 15 ማኑሄም የእግዚአብሔርን መልአክ “አንድ የፍየል ጠቦት ዐርደን እስክናዘጋጅልህ ድረስ እባክህ ቈይልን!” አለው። 16 የእግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን “ምንም አንተ ብታቈየኝ ምግብህን አልበላም፤ የሚቃጠል መሥዋዕት ማዘጋጀት ብትፈልግ ግን ለእግዚአብሔር አቅርበው” አለው። ማኑሄ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር። 17 ማኑሄም “የተናገርከው ቃል ሲፈጸም ምስጋና እናቀርብልህ ዘንድ ስምህ ማን ነው?” አለው። 18 መልአኩም “ስሜን ለማወቅ የፈለግኸው ለምንድን ነው? ስሜ ድንቅ ነው” ሲል መለሰለት። 19 ከዚህ በኋላ ማኑሄ አንድ የፍየል ጠቦትና የእህል ቊርባን ወስዶ በአለቱ መሠዊያ ላይ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ ማኑሄና ሚስቱም እየተመለከቱ ሳለ እግዚአብሔር አስደናቂ ነገር አደረገ። 20 ነበልባሉ ከመሠዊያው ወደ ሰማይ ሲወጣ ማኑሄና ሚስቱ እየተመለከቱ ሳለ የእግዚአብሔር መልአክ በነበልባሉ ውስጥ ሆኖ ወደ ላይ ወጣ፤ እነርሱም በግንባራቸው በመሬት ላይ ተደፉ። 21 የእግዚአብሔር መልአክ ለማኑሄና ለሚስቱ ዳግመኛ አልተገለጠም ከዚያ በኋላ ማኑሄ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ዐወቀ። 22 ማኑሄ ሚስቱን “እግዚአብሔርን ስላየን በእርግጥ እንሞታለን!” አላት። 23 ሚስቱ ግን “እግዚአብሔር ሊገድለን ቢፈልግ ኖሮ የሚቃጠል መሥዋዕታችንንና የእህል ቊርባናችንን ባልተቀበለም ነበር፤ ይህን ሁሉ አሁን ባላሳየንና እንዲህ ያለውን ነገር ሁሉ ባልነገረንም ነበር” ስትል መለሰችለት። 24 ሴቲቱም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሶምሶን ብላ ጠራችው፤ ልጁም አደገ፤ እግዚአብሔርም ባረከው፤ 25 በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በዳን ሰፈር ውስጥ በነበረበት ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ ያበረታው ጀመር። |