Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

መሳፍንት 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ዮፍታሔና ኤፍሬማውያን

1 የኤፍሬም ሰዎች ለጦርነት ተዘጋጅተው የዮርዳኖስን ወንዝ በመሻገር ወደ ጻፎን በደረሱ ጊዜ ዮፍታሔን “ዐሞናውያንን ለመውጋት ወሰን አልፈህ ስትሄድ እኛን ያልጠራኸን ለምንድን ነው? እንግዲህ እኛም ቤትህን በላይህ እናቃጥለዋለን!” አሉት።

2 ዮፍታሔም እንዲህ አላቸው፤ “እኔና ሕዝቤ ከዐሞናውያን ጋር በብርቱ ተጣልተን በነበረበት ጊዜ እናንተን ጠርቼአችሁ ነበር፤ ነገር ግን ከእነርሱ ጥቃት አላዳናችሁኝም፤

3 እናንተ እኔን ለመርዳት አለመፈለጋችሁን ባየሁ ጊዜ ለሕይወቴ ሳልሳሳ እነርሱን ለመውጋት ወሰኑን ተሻግሬ ሄድሁ፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ድልን አቀዳጀኝ። ታዲያ፥ አሁን እኔን ለመውጋት የተነሣችሁበት ምክንያት ምንድን ነው?”

4 ከዚህ በኋላ ዮፍታሔ የገለዓድን ሰዎች አሰባስቦ በኤፍሬም ሰዎች ላይ አደጋ በመጣል ድል አደረጋቸው፤ የኤፍሬም ሰዎች “እናንተ በኤፍሬምና በምናሴ ግዛት ውስጥ የምትኖሩ ገለዓዳውያን ኤፍሬምን ከድታችሁ የመጣችሁ ናችሁ!” ይሉአቸው ነበር።

5 የኤፍሬም ሰዎች እንዳያመልጡ ለማድረግ ገለዓዳውያን የዮርዳኖስን መሻገሪያ ቦታዎች ሁሉ ዘግተው ያዙ፤ ለማምለጥ የሚሞክር ማንኛውም የኤፍሬም ሰው ለመሻገር ፈቃድ ቢጠይቅ ገለዓዳውያን “አንተ የኤፍሬም ሰው ነህን?” ብለው ይጠይቁት ነበር፤ “አይደለሁም!” ካለ፥

6 “እስቲ ሺቦሌት” በል ይሉታል፤ እርሱ ግን “ሺ” የሚለውን ፊደል አስተካክሎ መናገር ስለማይችል “ሲቦሌት” ይላል፤ ከዚህ በኋላ እርሱን ይዘው የዮርዳኖስ መሸጋገሪያ ከሆኑት ስፍራዎች በአንዱ ይገድሉታል፤ ያንጊዜም በዚሁ ዐይነት አርባ ሁለት ሺህ የኤፍሬም ሰዎች ተገደሉ።

7 ዮፍታሔ ስድስት ዓመት ሙሉ የእስራኤል መሪ ከሆነ በኋላ ሞተ፤ በትውልድ አገሩ በገለዓድ በምትገኘው በአንዲት ከተማ ተቀበረ።


ኢብጻን፥ ኤሎን፥ ዓብዶን

8 ከዮፍታሔ ቀጥሎ የቤተልሔም ተወላጅ የሆነው ኢብጻን የእስራኤል መሪ ሆነ፤

9 ኢብጻን ሠላሳ ወንዶችና ሠላሳ ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ ሴቶች ልጆቹን ከጐሣው ውጪ ከሆኑ ወንዶች ጋር አጋባቸው፤ እንዲሁም ከጐሣው ውጪ የሆኑ ሴቶች ልጆችን አምጥቶ ከወንዶች ልጆቹ ጋር እንዲጋቡ አደረገ፤ ኢብጻን ሰባት ዓመት የእስራኤል መሪ ሆነ።

10 ኢብጻንም ሞቶ በቤተልሔም ተቀበረ።

11 ከኢብጻን ቀጥሎ የዛብሎን ወገን የሆነው ኤሎን እስራኤልን ዐሥር ዓመት መራ፤

12 ከዚያም በኋላ ሞተ፤ በዛብሎን ግዛት በምትገኘው በአያሎንም ምድር ተቀበረ።

13 ከኤሎን ቀጥሎ የፒርዓቶን ተወላጅ የሆነው የሂሌል ልጅ ዓብዶን የእስራኤል መሪ ሆነ፤

14 ዓብዶን በሰባ አህዮች ላይ ተቀምጠው የሚጋልቡ አርባ ወንዶች ልጆችና ሠላሳ የልጅ ልጆች ነበሩት፤ ዓብዶን ስምንት ዓመት የእስራኤል መሪ ሆነ።

15 ከዚያም በኋላ ዓብዶን ሞተ፤ ኮረብታማም በሆነው በዐማሌቃውያን አገር በኤፍሬም ግዛት በምትገኘውም በፒርዓቶን ተቀበረ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告