Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

መሳፍንት 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የይሁዳና የስምዖን ነገዶች አዶኒቤዜቅን መማረካቸው

1 ኢያሱ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ “በከነዓናውያን ላይ አደጋ ለመጣል ከነገዶቻችን መካከል ተቀዳሚ ሆኖ ማን ይዝመት?” ሲሉ እግዚአብሔርን ጠየቁ።

2 እግዚአብሔርም “የይሁዳ ነገድ ተቀዳሚ ሆኖ ይዝመት፤ እኔ ምድሪቱን ለእነርሱ አሳልፌ እሰጣለሁ” አለ።

3 የይሁዳ ነገድ ሕዝቦች ወንድሞቻቸውን የስምዖንን ነገድ ሕዝቦች “ለእኛ ወደ ተደለደለው ርስት በከነዓናውያን ላይ ለመዝመት ከእኛ ጋር አብረን እንሂድ እኛም ለእናንተ ወደተደለደለው ርስት አብረን እንሄዳለን” አሉአቸው። የስምዖን ነገድ ሕዝቦች ከእነርሱ ጋር ሄዱ።

4 ከዚያ በኋላ የይሁዳ ሕዝብ አብሮ ዘመተ። እግዚአብሔርም በከነዓናውያንና በፈሪዛውያን ላይ ድልን አቀዳጃቸው፤ እነርሱም በቤዜቅ ዐሥር ሺህ ሠራዊትን መቱ።

5 በዚያም አዶኒቤዜቅን በቤዜቅ አግኝተው ከእርሱ ጋር ጦርነት ገጠሙ፤ ከነዓናውያንንና ፈሩዛውያንን ድል አደረጉአቸው።

6 አዶኒቤዜቅም ከፊታቸው ሸሸ፤ እነርሱ ግን አባረው ከያዙት በኋላ የእጆቹንና የእግሮቹን አውራ ጣቶች ቈረጡ፤

7 አዶኒቤዜቅም “የእጆቻቸውና የእግሮቻቸው አውራ ጣቶች የተቈረጡባቸው ሰባ ነገሥታት ከገበታዬ ሥር ፍርፋሪ እየለቀሙ ይበሉ ነበር፤ በእነርሱ ላይ የፈጸምኩትን ግፍ ዛሬ እግዚአብሔር በእኔ ላይ መልሶ አመጣብኝ” ሲል ተናገረ። ወደ ኢየሩሳሌምም ተወስዶ በዚያው ሞተ።


የይሁዳ ነገድ ኢየሩሳሌምንና ኬብሮንን እንደ ያዘ

8 የይሁዳ ሰዎች ኢየሩሳሌምን በጦርነት ያዙአት፤ ሕዝብዋንም በሰይፍ ፈጁ፤ ከተማይቱንም በእሳት አቃጠሉ።

9 ከዚህ በኋላ የይሁዳ ሰዎች በተራራማው አገር፥ በኔጌብና በቈላማው አገር የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ለመውጋት ዘመቱ።

10 የይሁዳ ሰዎች በኬብሮን በሚኖሩ ከነዓናውያን ላይ ዘመቱ፤ ኬብሮን ቀድሞ ኪርያት አርባዕ ትባል ነበር፤ እነርሱም የሼሻይን፥ የአሒማንንና የታልማይን ጐሣዎች አሸነፉ።


ዖትኒኤል የደቢርን ከተማ ማሸነፉ
( ኢያሱ 15፥13-19 )

11 ከዚያም የይሁዳ ሰዎች በደቢር ኗሪዎች ላይ ዘመቱ፤ በዚያን ጊዜ ከተማይቱ “ቂርያት ሴፌር” ተብላ ትጠራ ነበር።

12 ካሌብም “ቀድሞ ቂርያት ሴፌርን ለሚይዝ ሰው ሴት ልጄን ዓክሳን እድርለታለሁ” አለ።

13 የካሌብ ታናሽ ወንድም የቀናዝ ልጅ ዖትኒኤል ከተማይቱን ቀድሞ ያዘ፤ ስለዚህም ካሌብ ሴት ልጁን ዓክሳን ዳረለት።

14 በጋብቻቸውም ቀን ዖትኒኤል ዓክሳን “አባትሽ የእርሻ መሬት እንዲሰጥሽ ጠይቂ” አላት፤ እርስዋም ካሌብን ስታይ ከበቅሎዋ ላይ ወረደች፤ ካሌብም “ምን እንድሰጥሽ ትፈልጊአለሽ” ብሎ ጠየቃት።

15 እርስዋም “የሰጠኸኝ መሬት በረሓማ ላይ ስለ ሆነ ጥቂት የውሃ ምንጮች እንድትሰጠኝ እለምንሃለሁ፤” አለችው፤ ስለዚህ ካሌብ የላይኛውንና የታችኛውን ምንጮች ሰጣት።


የይሁዳና የብንያም ነገዶች የተቀዳጁት ድል

16 የሙሴ ዐማት የነበረው የቄናዊው ዘሮች ከይሁዳ ሕዝብ ጋር በመሆን የተምር ዛፎች ከሞሉባት ከኢያሪኮ ከተማ ተነሥተው፥ በይሁዳ ካለችው ከዐራድ በስተደቡብ ወዳለው ደረቅ ምድር ተጓዙ፤ እዚያም በዐማሌቃውያን መካከል ተቀመጡ።

17 የይሁዳ ሕዝብ ከስምዖን ሕዝብ ጋር በአንድነት ዘምተው በጸፋት ከተማ ይኖሩ የነበሩትን ከነዓናውያንን ድል አደረጉ፤ ከተማይቱንም ፈጽመው ካጠፉአት በኋላ “ሖርማ” ብለው ሰየሙአት፤

18 የይሁዳም ነገድ ጋዛንና አስቀሎናን፥ አቃሮንንና አካባቢዎቻቸውን ያዙ።

19 እግዚአብሔር ከይሁዳ ሕዝብ ጋር ስለ ነበረ የተራራማውን አገር አሸንፈው ያዙ፤ ነገር ግን በረባዳማው ሜዳ አገር የነበሩት ኗሪዎች የብረት ሠረገሎች ስለ ነበሩአቸው ሊያስወጡአቸው አልቻሉም።

20 ሙሴ ባዘዘው መሠረት ኬብሮን ለካሌብ ተሰጠ፤ ርሱም ሦስቱን የዐናቅ ጐሣዎች ከዚያ አስወጣ።

21 የብንያም ነገድ ግን በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን አላስወጡም ነበር፤ ከዚያን ጊዜም ጀምሮ ኢያቡሳውያን ከብንያም ሕዝብ ጋር እስከ ዛሬ ድረስ አብረው መኖርን ቀጠሉ።


የኤፍሬምና የምናሴ ነገዶች ቤትኤልን መያዛቸው

22 የዮሴፍ ዘሮች ደግሞ በቤቴል ላይ ዘመቱ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነበር፤

23 የዮሴፍ ልጆች ቤቴልን የሚሰልሉ ሰዎች ላኩ፤ የከተማይቱ ስም አስቀድሞ ሎዛ ይባል ነበር።

24 ሰላዮቹም ከከተማይቱ የሚወጣ አንድ ሰው አግኝተው “ወደ ከተማይቱ እንዴት መግባት እንደሚቻል ብትነግረን መልካም እናደርግልሃለን” አሉት።

25 እርሱም የከተማይቱን መግቢያ አሳያቸው፤ እነርሱም የከተማይቱን ሕዝብ በሰይፍ ፈጁአቸው፤ ያን ሰውና ወገኖቹን ሁሉ ግን በነጻ ለቀቁአቸው።

26 ያም ሰው ዘግይቶ ወደ ሒታውያን ምድር ሄዶ ከተማ ሠራና “ሎዛ” ብሎ ሰየማት፤ እስከ ዛሬም የምትጠራበት ስም ይኸው ነው።


እስራኤላውያን ያላባረሩት ሕዝብ

27 የምናሴ ነገድ ቤትሻን፥ በታዕናክ በዶርን የዪብልዓምንና በመጊዶና በአካባቢያቸው የሚኖሩትን ሰዎች አላስወጡም ነበር፤ ከነዓናውያንም በዚያው መኖርን ቀጠሉ፤

28 እስራኤላውያን ብርታት ባገኙ ጊዜ ከነዓናውያን ለእነርሱ የጒልበት ሥራ እንዲሠሩላቸው ያስገድዱአቸው ነበር፤ ሆኖም ሁሉንም አላስወጡም ነበር።

29 የኤፍሬም ነገድም በጌዜር ይኖሩ የነበሩትን ከነዓናውያንን አላባረሩም ነበር፤ ስለዚህ ከነዓናውያን እዚያው ከእነርሱ ጋር ኗሪዎች ሆኑ።

30 የዛብሎን ነገድ በቂትሮንና በናህላል ይኖሩ የነበሩትን ኗሪዎች አላስወጡም ነበር፤ ስለዚህ ከነዓናውያን እዚያው ከእነርሱ ጋር ኗሪዎች ሆኑ፤ ሆኖም ለዛብሎናውያን የጒልበት ሥራ ለመሥራት ይገደዱ ነበር።

31 የአሴር ነገድ በዓኮ፥ በሲዶና፥ በአሕላብ፥ በአክዚብ፥ በሔልባ፥ በአፌቅና በረሖብ ይኖሩ የነበሩትን ኗሪዎች አላባረሩም ነበር።

32 ከነዓናውያንንም ሳያስወጡ በመቅረታቸው የአሴር ሕዝብ በዚያው ከእነርሱ ጋር አብረው ይኖሩ ነበር።

33 የንፍታሌም ነገድ በቤትሼሜሽና በቤትዓናት ይኖሩ የነበሩትን ሰዎች አላስወጡም፤ ስለዚህም የንፍታሌም ሕዝብ ከከነዓናውያን ጋር እዚያው አብረው መኖርን ቀጠሉ፤ ሆኖም የጒልበት ሥራ እንዲሠሩላቸው ከነዓናውያንን ያስገድዱአቸው ነበር።

34 አሞራውያን የዳንን ነገድ ሕዝብ ወደ ኮረብታማው አገር አባረሩአቸው፤ ወደ ሜዳማውም ምድር እንዲወርዱ አልፈቀዱላቸውም፤

35 አሞራውያን በሔሬስ ተራራና በአያሎን፥ በሻዓልቢም መኖርን ቀጠሉ፤ ነገር ግን የዮሴፍ ልጆች (የኤፍሬምና የምናሴ ነገዶች) የእነርሱ ተገዢዎች አድርገው የጒልበት ሥራ እንዲሠሩላቸው ያስገድዱአቸው ነበር።

36 የአሞራውያን ድንበር ከዐቅራቢም አቀበት ከሴላዕ ጀምሮ ወደ ላይ ይወጣ ነበር።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告