ዮሐንስ 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኢየሱስ ለዳስ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ መጠየቁ 1 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ይዘዋወር ነበር፤ አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበረ ግን በይሁዳ ሊዘዋወር አልፈለገም፤ 2 በዚያን ጊዜ የአይሁድ የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር። 3 ስለዚህ ወንድሞቹ ወደ ኢየሱስ ቀርበው እንዲህ አሉት፦ “ደቀ መዛሙርትህ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሥተህ ወደ ይሁዳ ምድር ሂድ፤ 4 በግልጥ ለመታወቅ የሚፈልግ ሰው ሥራውን በስውር አያደርግም፤ አንተም እነዚህን ነገሮች ሁሉ ስታደርግ ራስህን ለዓለም ልትገልጥ ያስፈልጋል።” 5 ይህንንም ያሉበት ምክንያት ወንድሞቹ እንኳ በእርሱ ስላላመኑ ነው። 6 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የእኔ ጊዜ ገና አልደረሰም፤ የእናንተ ጊዜ ግን ዘወትር የተመቸ ነው። 7 ዓለም እናንተን ሊጠላ አይችልም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን ስለምመሰክርበት እኔን ይጠላኛል። 8 እናንተ ወደ በዓሉ ሂዱ፤ እኔ ግን ጊዜዬ ገና ስላልደረሰ ወደዚህ በዓል አልሄድም።” 9 ይህንንም ብሎ እርሱ በገሊላ ቀረ። ኢየሱስ በዳስ በዓል ላይ መገኘቱ 10 ነገር ግን ወንድሞቹ ወደ በዓሉ ከሄዱ በኋላ እርሱ በይፋ ሳይሆን በስውር ወደ በዓሉ ሄደ። 11 በበዓሉም ላይ “እርሱ የት ነው?” እያሉ አይሁድ ይፈልጉት ነበር። 12 ሕዝቡም ስለ እርሱ በሹክሹክታ ይነጋገሩ ነበር፤ አንዳንዶቹ “እርሱ ደግ ሰው ነው” ሲሉ፥ ሌሎች ደግሞ “አይደለም፤ እርሱ ሕዝቡን ያስታል” ይሉ ነበር። 13 ይሁን እንጂ የአይሁድን ባለ ሥልጣኖች በመፍራት ማንም ስለ እርሱ በግልጥ አልተናገረም። 14 በበዓሉም አጋማሽ ላይ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዶ ያስተምር ጀመር። 15 አይሁድም፥ “ይህ ሰው ሳይማር ይህን ሁሉ እንዴት ሊያውቅ ቻለ?” እያሉ ይደነቁ ነበር። 16 ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የእኔ ትምህርት ከላከኝ ከአብ የተገኘ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም። 17 የላከኝን ፈቃድ ማድረግ የሚፈልግ ቢኖር ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር የተገኘ ወይም እኔ ከራሴ የተናገርኩት መሆኑን ያውቃል። 18 ከገዛ ራሱ የሚናገር የገዛ ራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላኪውን ክብር የሚፈልግ ግን እውነተኛ ነው፤ ሐሰትም የለበትም። 19 ሙሴ ሕግን ሰጥቶአችሁ የለምን? ነገር ግን ከእናንተ ሕግን የሚፈጽም ማንም የለም። እናንተ ለምን ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ?” 20 ሕዝቡም “አንተ ጋኔን አለብህ፤ ማን ሊገድልህ ይፈልጋል?” አሉት። 21 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ አንድ ሥራ ሠራሁ፤ እናንተም ሁላችሁ በዚህ ሥራ ትደነቃላችሁ። 22 ሙሴ የግዝረትን ሥርዓት ሰጣችሁ፤ ይህም ሥርዓት የተገኘው፤ ከአባቶች ነው እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ እናንተም እኮ በሰንበት ሰውን ትገርዛላችሁ። 23 እንግዲህ በሙሴ አማካይነት የተሰጠው ሕግ እንዳይሻር በሰንበት ቀን ሰው የሚገረዝ ከሆነ ታዲያ፥ እኔ በሰንበት ቀን የሰውን ሁለንተና በመፈወሴ ስለምን ትቈጣላችሁ? 24 ትክክለኛ ፍርድ ፍረዱ እንጂ የሰውን ፊት አይታችሁ በማዳላት አትፍረዱ።” ስለ መሲሕ የተነሣ ክርክር 25 ከኢየሩሳሌም ሰዎች አንዳንዶቹ እንዲህ አሉ፦ “ሊገድሉት የሚፈልጉት ሰው ይህ አይደለምን? 26 እነሆ፥ እርሱ በግልጥ ይናገራል፤ እነርሱም ምንም አላሉትም፤ ይህ ሰው መሲሕ መሆኑን ባለሥልጣኖች በእውነት ዐውቀው ይሆን? 27 ሆኖም ይህ ሰው ከወዴት እንደ ሆነ እኛ እናውቃለን፤ መሲሕ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደ ሆነ የሚያውቅ ማንም የለም።” 28 ስለዚህ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሲያስተምር ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “እኔን ታውቁኛላችሁ፤ ከወዴትም እንደ መጣሁ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እኔ በራሴ ሥልጣን አልመጣሁም፤ የላከኝ እርሱ እውነተኛ ነው፤ እናንተ ግን አታውቁትም። 29 እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ስለ መጣሁና እርሱ ስለ ላከኝ ዐውቀዋለሁ።” 30 በዚያን ጊዜ ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም። 31 ሆኖም ከሕዝቡ ብዙዎቹ በእርሱ አመኑ፤ እንዲህም አሉ፦ “መሲሕ በሚመጣበትስ ጊዜ ይህ ሰው ካደረጋቸው ተአምራት የበለጠ ያደርጋልን?” ኢየሱስን እንዲይዙ ወታደሮች መላካቸው 32 ሰዎቹ ስለ ኢየሱስ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ ፈሪሳውያን ሰሙ፤ ስለዚህ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ኢየሱስን ለማስያዝ የቤተ መቅደስ ዘብ ጠባቂዎችን ላኩ። 33 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ከእናንተ ጋር ጥቂት ጊዜ እቈያለሁ፤ ከዚያ በኋላ ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፤ 34 እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤ እኔ ወዳለሁበት፥ እናንተ መምጣት አትችሉም።” 35 ስለዚህ የአይሁድ ባለ ሥልጣኖች እንዲህ ተባባሉ፦ “እኛ እንዳናገኘው ይህ ሰው ወዴት ሊሄድ ነው? ምናልባት በግሪኮች መካከል ወደ ተበተኑት አይሁድ ዘንድ ሄዶ አሕዛብን ያስተምር ይሆን? 36 ‘ትፈልጉኛላችሁ፤ ነገር ግን አታገኙኝም፤ እኔ ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም’ ሲል ምን ማለቱ ነው?” የሕይወት ውሃ ምንጭ 37 የበዓሉ መጨረሻ በሆነው በታላቁ ቀን ኢየሱስ ቆመና ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “ውሃ የጠማው ቢኖር ወደ እኔ መጥቶ ይጠጣ፤ 38 በእኔ የሚያምን ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚለው፥ የሕይወት ውሃ ምንጭ ከውስጡ ይፈልቃል።” 39 ይህንንም የተናገረው በእርሱ የሚያምኑ ስለሚቀበሉት ስለ መንፈስ ቅዱስ ነበር፤ ኢየሱስ ገና ወደ ክብር ስላልወጣ መንፈስ ቅዱስ ገና አልተሰጠም ነበር። በሕዝቡ መካከል መለያየት መከሠቱ 40 ስለዚህ ከሕዝቡ አንዳንዶቹ ይህን ቃል በሰሙ ጊዜ፦ “ይመጣል የተባለው ነቢይ በእርግጥ ይህ ነው” አሉ። 41 ሌሎች “ይህ መሲሕ ነው” አሉ። ሌሎቹ ግን “መሲሕ የሚመጣው ከገሊላ ነውን? 42 መሲሕ ከዳዊት ዘር እንደሚወለድና ከዳዊት ከተማ ከቤተልሔም እንደሚመጣ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፎ የለምን?” አሉ። 43 ስለዚህ በእርሱ ምክንያት በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ። 44 አንዳንዶቹ ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ማንም አልያዘውም። የአይሁድ መሪዎች አለማመን 45 ከዚህ በኋላ ዘብ ጠባቂዎቹ ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን ተመልሰው ሄዱ፤ እነርሱም “ስለምን አላመጣችሁትም?” አሉአቸው። 46 ወታደሮቹም “ይህ ሰው እንደሚናገረው ዐይነት ማንም ተናግሮ አያውቅም” ሲሉ መለሱ። 47 ፈሪሳውያን ግን እንዲህ አሉ፦ “እናንተም ደግሞ ተሳሳታችሁን? 48 ለመሆኑ ከባለ ሥልጣኖች ወይም ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመኑ አሉን? 49 ይህ የሙሴን ሕግ የማያውቅ ሕዝብ በእርግጥ የተረገመ ነው።” 50 ከዚህ በፊት ወደ ኢየሱስ ሄዶ የነበረውና ከፈሪሳውያን አንዱ የሆነው ኒቆዲሞስ፥ 51 “በሕጋችን መሠረት አንድ ሰው የክስ መልስ አስቀድሞ ሳይሰማለትና ምን እንዳደረገ ሳይታወቅ ይፈረድበታልን?” አላቸው። 52 እነርሱም “አንተም ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንደማይነሣ መርምረህ ተረዳ” አሉት። 53 እያንዳንዱም ወደየቤቱ ሄደ። |