ኢዮብ 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኢዮብ 1 ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦ 2 “አዎ! እኔ ይህ እውነት መሆኑን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ሰው በእግዚአብሔር ፊት፥ እንዴት ጻድቅ መሆን ይችላል? 3 ከእርሱስ ጋር ማን ሊከራከር ይችላል? እርሱ አንድ ሺህ ጥያቄዎች ቢጠይቅ ከእነርሱ አንዱን እንኳ መመለስ የሚችል የለም። 4 እግዚአብሔር ጠቢብና ኀያል ነው፤ ማነው እርሱን ተቋቊሞ ያልተሸነፈ? 5 ሳይታሰብ በድንገት ተራራዎችን ያናውጣል፤ በቊጣውም ይገለባብጣቸዋል። 6 እግዚአብሔር ምድርን ከቦታዋ ያንቀጠቅጣል፤ ምሰሶችዋንም ያነቃንቃል። 7 ፀሐይ እንዳትወጣ ሊያደርግ ይችላል፤ ከዋክብትም እንዳያበሩ ያደርጋል። 8 ማንም ሳያግዘው ሰማይን የዘረጋ እርሱ ነው፤ እርሱ በባሕር ሞገድ ላይ ይራመዳል። 9 ድብ፥ ኦሪዮንና፥ ፕልያዲስ የተባሉትን ከዋክብት፥ እንዲሁም በደቡብ በኩል ያሉትን የከዋክብት ክምችቶች በሰማይ ላይ ያኖራቸው እግዚአብሔር ነው። 10 እርሱ የሚያደርጋቸውን ድንቅ ነገሮች መርምረን ልናስተውል አንችልም፤ እርሱም የሚፈጽማቸውን ተአምራት ልንቈጥራቸው አንችልም። 11 “እግዚአብሔር በአጠገቤ ቢያልፍ አላየውም፤ ወደ እኔም ቢቀርብ ለይቼ አላውቀውም፤ 12 የፈለገውን ቢወስድ ማንም አይከለክለውም፤ ‘ለምን እንዲህ ታደርጋለህ?’ ብሎ ሊጠይቀው የሚደፍርም የለም። 13 እግዚአብሔር ከቊጣው አይመለስም፤ ረዓብ የተባለው የባሕር አውሬ ረዳቶች እንኳ በእግሩ ሥር ይንበረከካሉ። 14 ታዲያ፥ እኔ ለእርሱ መልስ መስጠት እንዴት እችላለሁ? ከእርሱ ጋር ለመከራከርስ ምን ቃላት አገኛለሁ? 15 ንጹሕ ሆኜ ብገኝ እንኳ፥ ፈራጁ አምላክ እንዲምረኝ እለምነዋለሁ እንጂ መልስ ልሰጠው አልደፍርም። 16 የእርሱን ስም ብጠራና መልስ ቢሰጠኝም እንኳ አቤቱታዬን ያዳምጣል ብዬ አላምንም። 17 በዐውሎ ነፋስ ያደቀኛል ያለ ምክንያትም ቊስሌን ያበዛል። 18 ትንፋሽ እስካገኝ እንኳ ፋታ አይሰጠኝም፤ ሕይወቴን በሥቃይ ሞልቶታል። 19 ባለኝ ኀይል ልታገለው እንዳልል፥ በኀይል እርሱን የሚቋቋም የለም፤ ተሟግቼ እረታዋለሁ እንዳልል፥ እርሱን ወደ ፍርድ ሸንጎ ሊያቀርበው የሚችል የለም። 20 እኔ ንጹሕና እውነተኛ ነኝ፤ ነገር ግን አነጋገሬ በደለኛ ያደርገኛል፤ የምናገራቸው ንግግሮች ሁሉ ይፈርዱብኛል። 21 ምንም እንኳ ፍጹም ብሆን ስለ ራሴ አላስብም ሕይወቴንም እጸየፈዋልሁ። 22 እግዚአብሔር ፍጹሙንና በደለኛውን ስለሚያጠፋ ምንም ልዩነት የለም ያልሁት ስለዚህ ነው። 23 በአደጋ ሰው ሲቀሠፍ እርሱ በንጹሕ ሰው ችግር ይሳለቃል። 24 ምድር በክፉ ሰዎች እጅ ተላልፋ ስትሰጥ እርሱ የዳኞችን ዐይን ይሸፍናል፤ ይህን ያደረገ እግዚአብሔር ካልሆነ ታዲያ፥ ማነው? 25 “የዕድሜዬ ቀኖች ከሯጭ ይልቅ የፈጠኑ ናቸው ምንም ደስታ ሳላይ ያልፋሉ። 26 እነርሱም ከደንገል እንደ ተሠራ ታንኳ ይሮጣሉ፤ እንደ ነጣቂ ንስርም ይፈጥናሉ። 27 ሮሮዬን ልርሳ፥ ፊቴንም ማጥቈር ትቼ ፈገግታ ላሳይ ብል፥ 28 እግዚአብሔር ንጹሕ አድርጎ እንደማይቈጥረኝ ስለማውቅ፥ መከራና ሥቃይ ይመጣብኛል ብዬ እፈራለሁ። 29 እንግዲህ በደለኛ ሆኜ ከተቈጠርኩ፥ በከንቱ መድከሜ ለምንድን ነው? 30 ሰውነቴን በሳሙና ባጥብ፥ እጄንም በእንዶድ ባጸዳ 31 ይህም ሁሉ ሆኖ አንተ ወደ አዘቅት ትጥለኛለህ፤ የገዛ ልብሴ እንኳ ይጸየፈኛል። 32 እርሱ እንደ እኔ ሰው ስላልሆነ፥ ወደ ፍርድ ሸንጎ ሄደን፥ እንፋረድ ልለው አልችልም። 33-34 ከጀርባዬ እግዚአብሔር በትሩን እንዲያነሣና ግርማውም እንዳያስፈራኝ እጁን በሁለታችን ላይ የሚያኖር ዳኛ በመካከላችን ምነው በተገኘ! 35 እኔ ሰዎች እንደሚያስቡኝ ስላልሆንኩ እርሱን ሳልፈራው በተናገርኩት ነበር። |