Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 42 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ኢዮብ

1 ከዚህ በኋላ ኢዮብ ለእግዚአብሔር እንዲህ ሲል መለሰ፦

2 “አምላክ ሆይ! አንተ ሁሉን ነገር ማድረግ እንደምትችል ዐውቃለሁ፤ የአንተንም ዕቅድ ማሰናከል የሚችል የለም።

3 እኔ የማውቀው በጣም ትንሽ ሆኖ ሳለ ብዙ የምናገረው ለምን እንደ ሆነ ጠይቀሃል። በእርግጥ እኔ ስለማላውቃቸውና እጅግ ድንቅ ስለ ሆነ ነገር ተናግሬአለሁ።

4 ‘አድምጥና ለጥያቄዬ መልስ ስጥ’ ብለኸኛል፤

5 እኔ እስከ አሁን ስለ አንተ የማውቀው፥ ሰዎች የነገሩኝን በመስማት ብቻ ነበር፤ አሁን ግን በዐይኖቼ አየሁህ።

6 ከዚህም የተነሣ የተናገርኩት ነገር ስላሳፈረኝ በዐመድና በትቢያ ላይ ተቀምጬ ንስሓ እገባለሁ።”


መደምደሚያ

7 እግዚአብሔር ከኢዮብ ጋር እነዚህን ነገሮች ከተነጋገረ በኋላ ቴማናዊውን ኤሊፋዝን እንዲህ አለው፦ “እናንተ ስለ እኔ እንደ አገልጋዬ እንደ ኢዮብ ትክክለኛውን ነገር ስላልተናገራችሁ እኔ በአንተና በሁለቱ ጓደኞችህ ላይ ተቈጥቼአለሁ።

8 ስለዚህ አሁን ሰባት ኰርማዎችንና ሰባት አውራ በጎችን ይዛችሁ ወደ አገልጋዬ ወደ ኢዮብ ሂዱ፤ እዚያም ስለ ራሳችሁ ኃጢአት የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ፤ አገልጋዬ ኢዮብ ይጸልይላችኋል፤ እኔም ጸሎቱን ሰምቼ በበደላችሁ መጠን አልቀጣችሁም፤ እናንተ እንደ ኢዮብ ስለ እኔ ትክክል የሆነውን ነገር አልተናገራችሁም።”

9 ከዚህ በኋላ ቴማናዊው ኤሊፋዝ፥ ሹሐዊውም ቢልዳድና ናዕማታዊውም ጾፋር ሄደው እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ እግዚአብሔርም የኢዮብን ጸሎት ሰማ።

10 ኢዮብ ለሦስቱ ወዳጆቹ ከጸለየ በኋላ እግዚአብሔር እንደገና እንዲበለጽግ አደረገው፤ ዱሮ ከነበረውም ይበልጥ እጥፍ አድርጎ ሰጠው።

11 በዚህ ጊዜ የኢዮብ ወንድሞች፥ እኅቶችና ቀድሞ የሚያውቁት ሰዎች ሁሉ ሊጐበኙት መጡ፤ በቤቱም ከእርሱ ጋር ተመገቡ፥ ሐዘናቸውን በመግለጥ እግዚአብሔር ስላደረሰበት ብርቱ መከራ አጽናኑት፤ እያንዳንዳቸውም የብርና የወርቅ ቀለበት ስጦታ አደረጉለት።

12 እግዚአብሔር የኢዮብን የመጨረሻ ሕይወት ከመጀመሪያው አስበልጦ ባረከው፤ ስለዚህ ኢዮብ ዐሥራ አራት ሺህ በጎች፤ ስድስት ሺህ ግመሎች፤ አንድ ሺህ ጥማድ በሬዎች፤ አንድ ሺህ እንስት አህዮች ነበሩት።

13 እንዲሁም ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆችን እንደገና ወለደ።

14 ከሴቶች ልጆቹ የመጀመሪያዋን ይሚማ፥ ሁለተኛዋን ቀጺዐ ሦስተኛዋን ቄሬንሀፉክ ብሎ ሰየማቸው።

15 በዓለም ላይ የኢዮብን ሴቶች ልጆች በቊንጅና የሚወዳደሩአቸው ሴቶች አልነበሩም፤ አባታቸውም ከወንድሞቻቸው ጋር ርስት አካፈላቸው።

16 ከዚህም በኋላ ኢዮብ መቶ አርባ ዓመት ኖረ፤ የልጅ ልጆቹንም እስከ አራት ትውልድ ድረስ ለማየት በቃ።

17 ብዙ ዘመን ከኖረ በኋላ አርጅቶ ሞተ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告