Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 41 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 “ሌዋታን የሚባለውን የባሕር አውሬ በመንጠቆ ከባሕር ውስጥ ልትይዘው ትችላለህን? ወይም ምላሱን በገመድ ታስረዋለህን?

2 በአፍንጫው መሰነጊያ አስገብተህ መንጋጋውንም በመንጠቆ ወግተህ ልትይዘው ትችላለህን?

3 ምሕረት እንድታደርግለት ይለምንሃልን? በመልካም አነጋገር ይለምንሃልን?

4 ለዘለዓለም በባርነት እንዲያገለግልህ ከአንተ ጋር ስምምነት ያደርጋልን?

5 እንደ ወፍ እርሱን ልታለማምድ ትችላለህን? ወይስ ሴቶች ልጆችህን እንዲያጫውት አስረህ ታኖረዋለህን?

6 ዓሣ ነጋዴዎች እርሱን ለመግዛት ይጫረታሉን? ቈራርጠውስ ይከፋፈሉታልን?

7 ቆዳውን በፈለግህበት ቦታ በጦር መብሳት፥ ጭንቅላቱንም በሾተል ወግተህ መሰንጠቅ ትችላለህን?

8 ከቻልክ እስቲ እጅህን በላዩ ላይ አሳርፍበት። ከእርሱ ጋር የምታደርገውን ትግል በፍጹም አትረሳውም፤ ዳግመኛም ከእርሱ ጋር ለመታገል አትሞክርም።

9 “ከሌዋታን ጋር ታግሎ በቊጥጥር ሥር ለማዋል የሚደረግ ሙከራ ከንቱ ነው። እርሱን የሚያየው ሁሉ በፍርሃት ይብረከረካል።

10 በእርሱ ላይ አደጋ መጣል ይህን ያኽል አደገኛ ከሆነ፥ ታዲያ፥ እኔን ለመቃወም የሚደፍር ማነው?

11 ከሰማይ በታች ያለው ነገር ሁሉ የእኔ ነው፤ ታዲያ፥ እንድመልስለት ለእኔ ያበደረ ማነው?

12 “ስለ ሌዋታን እግሮች፥ ስለ ብርቱ ኀይሉ ስለሚያምረው አካሉ ሳልገልጥ አላልፍም።

13 ድርብርብ የሆነ ቆዳውን ለመግፈፍና መንጋጋውንስ ለመፈልቀቅ ማን ይችላል?

14 እጅግ የሚያስፈሩ ጥርሶች ያሉበት አፉን ከፍቶ መንጋጋውን ሊያላቅቀው የሚችል ማን ነው?

15 የጀርባው ቆዳዎች በመደዳ እንደ ተደረደሩ ጋሻዎች ናቸው፤ እጅግ የተጣበቁም ስለ ሆኑ እንደ ብረት ጠንካሮች ናቸው።

16 አንዱ ከሌላው ጋር እጅግ የተጣበቀ በመሆኑ፥ በመካከላቸው ነፋስ እንኳ ማለፍ አይችልም።

17 ሁሉም እርስ በርሳቸው የተያያዙ ስለ ሆኑ፥ ከቶ ምንም ነገር ሊለያያቸው አይችልም።

18 እርሱ በሚያነጥስበት ጊዜ፥ የብርሃን ብልጭታ ይታያል፤ ዐይኖቹም እንደ ንጋት ፀሐይ ያበራሉ፤

19 ከአፉ የእሳት ነበልባል ይወጣል፤ የእሳት ፍንጣሪም ሲበተን ይታያል።

20 ድስት በተጣደበት ምድጃ ጭራሮ እንደሚጤስ፥ ከአፍንጫው ጢስ ሲወጣ ይታያል።

21 የትንፋሹ ግለት ከሰል ያቀጣጥላል፤ የእሳት ነበልባልም ከአፉ ይወጣል።

22 የአንገቱ ደንደስ ኀይልን የተሞላ ነው፤ የፊቱም ግርማ እጅግ አስፈሪ ነው።

23 ሥጋው ድርብርብ ሆኖ እርስ በርሱ የተጣበቀ ስለ ሆነ ሰውነቱ እንደ ብረት የጠነከረ ነው።

24 ልቡ እንደ ድንጋይ ጠንካራ ነው፤ ጥንካሬውም እንደ ወፍጮ ድንጋይ ነው።

25 ይህ አውሬ በሚነሣበት ጊዜ ኀያላን እንኳ በፍርሃት ይርበደበዳሉ።

26 በምንም ዐይነት ሰይፍና፥ ጦር፥ ፍላጻና መውጊያ ቢያገኙት አያሸንፉትም።

27 እርሱ ብረትን እንደ ሰንበሌጥ ይሰባብራል፤ ነሐስንም እንደ በሰበሰ እንጨት ያደቃል።

28 ፍላጻ ቢወረወርበት እንኳ ፈርቶ አይሸሽም፤ የወንጭፍ ድንጋይም በእርሱ ፊት እንደ ገለባ ነው።

29 እርሱ ዱላን የሚቈጥረው እንደ ሣር ነው፤ ሰዎችም ጦር ሲወረውሩበት በማፌዝ ይስቃል።

30 በጭቃ ውስጥ ሲጥመለመል ሹልና ስለ ታም የሆነው ቆዳው፥ እንደ ማረሻ ምድርን ይሰነጣጥቃል።

31 ባሕርን እንደ ፈላ ውሃ ያፍለቀልቀዋል፤ በማሰሮ ውስጥ እንደሚፈላ ዘይትም ያንተከትከዋል።

32 እርሱ የሚያልፍበት መንገድ ያበራል፤ የባሕሩንም ውሃ ወደ ዐረፋ ይለውጠዋል።

33 እርሱ ፍርሀት የማያውቅ ፍጡር ስለ ሆነ፥ በዓለም ላይ እርሱን የሚመስል ፍጡር ከቶ የለም።

34 እጅግ ታላላቅ የሆኑትን ፍጡሮች እንኳ ይንቃል፤ እርሱ በአራዊት ሁሉ ላይ ንጉሥ ነው።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告