Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የመጀመሪያው ውይይት ኤሊፋዝ
( 4፥1—14፥22 )

1 የቴማን አገር ሰው የሆነው ኤሊፋዝ እንዲህ ሲል መለሰ፦

2 “ኢዮብ ሆይ! አንድ ሰው ደፍሮ ቢናገርህ በትዕግሥት ታዳምጣለህን? ነገር ግን ከመናገር ማን ይቈጠባል?

3 ብዙ ሰዎችን አስተምረሃል፤ የደከሙትንም እጆች አበርትተሃል።

4 ቃሎችህ የሚሰናከሉትን ይደግፉ ነበር፤ የሚብረከረኩትንም ጒልበቶች ታበረታ ነበር።

5 አሁን ግን ችግር ስለ መጣብህ ተስፋ ቢስ ሆነሃል፤ ችግሩም ስለ በረታብህ ተስፋ ቈርጠሃል።

6 አምላክህን መፍራትህ መተማመኛህ፥ ትክክለኛ መንገዶችህም፥ ተስፋህ አይደለምን?

7 ንጹሕ ሰው ሆኖ መከራ የደረሰበት፥ ቀጥተኛ ሰው ሆኖ ሳለ የተደመሰሰ እንዳለ እስቲ አስብ።

8 እኔ እንዳስተዋልኩት ክፋትን የሚያርሱና መከራን የሚዘሩ ያንኑ ይሰበስባሉ።

9 በእግዚአብሔር እስትንፋስ ይጠፋሉ፤ በቊጣውም ማዕበል ይደመሰሳሉ።

10 ክፉዎች እንደ አንበሳ ያገሣሉ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው ይጮኻሉ፤ እግዚአብሔር ግን ጥርሳቸውን ይሰባብራል።

11 አንበሳ አድኖ የሚበላውን ሲያጣ እንደሚሞት እነርሱም ይሞታሉ፤ የአንበሳይቱም ደቦሎች እንደሚበተኑ የእነርሱም ልጆች ይበተናሉ፤

12 “ከዕለታት አንድ ቀን ምሥጢራዊ መልእክት ወደ እኔ መጣ፤ ይህንንም መልእክት በሹክሹክታ ሰማሁት።

13 ሰዎች ከባድ እንቅልፍ በሚይዛቸውና በሚያስጨንቅ የሌሊት ቅዠት ጊዜ፥

14 ፍርሀትና መርበድበድ ይዞኝ፥ አጥንቶቼ ሁሉ እንዲንቀጠቀጡ አደረገ።

15 የነፋስ ሽውታ በፊቴ ላይ አለፈ፤ ከድንጋጤ የተነሣ ጠጒሬ ተንጨፍርሮ ቆመ።

16 በዚያም አንድ ነገር ቆሞ አየሁ፤ ትኲር ብዬ ብመለከትም ምን እንደ ሆነ ለማወቅ አልቻልኩም። ከዚያ በኋላ ጸጥ ካለው ስፍራ እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማሁ፦

17 ‘በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሆኖ ሊገኝ የሚችል ሰው አለን? ወይስ በፈጣሪው ፊት ንጹሕ የሚሆን ሰው ይገኛልን?

18 እግዚአብሔር በአገልጋዮቹ የማይተማመንባቸው ከሆነ፥ በመላእክቱ እንኳ ስሕተት የሚያገኝባቸው ከሆነ፥

19 ታዲያ፥ ምስጥ ሳይበላቸው የሚፈርሱ መሠረታቸው ዐፈር በሆነና ከሸክላ በተሠራ ቤት ውስጥ በሚኖሩትማ ላይ እንዴት ይተማመንባቸዋል?

20 በጠዋትና በማታ መካከል ይሰባበራሉ፤ ሳይታወቅ ለዘለዓለም ይጠፋሉ።

21 ካስማው እንደ ተነቀለ ድንኳን ያለ ጥበብ ይሞታሉ።’ ”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告