Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 39 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 “የበረሓ ፍየሎች የሚወልዱበትን ጊዜ ታውቃለህን? ዋልያ አምጣ ስትወልድ አይተህ ታውቃለህን?

2 በእርግዝና ምን ያኽል ጊዜ እንደምትቈይ፥ መቼስ እንደምትወልድ ታውቃለህን?

3 ተንበርክካ በማማጥ ግልገሎችዋን የምትወልደው መቼ እንደ ሆነ ታውቃለህን?

4 ግልገሎችዋ በዱር አድገው ይጠነክራሉ፤ ወጥተውም ከሄዱ በኋላ፥ ዳግመኛ ወደ እናታቸው አይመለሱም።

5 “ለሜዳ አህዮች ነጻነት የሰጣቸው ማን ነው? ከእስራት የፈታቸውስ ማን ነው?

6 በረሓን ለእነርሱ መሰማሪያ አድርጌ ሰጥቼአለሁ፤ ጨው ባለበት ሜዳም እንዲኖሩ አድርጌአቸዋለሁ።

7 ሁካታ ከበዛባቸው ከተሞች ርቀው ይኖራሉ፤ ከኋላ እየነዳ የሚጮኽባቸውን አይቀበሉም።

8 በተራሮች ላይ ይሰማራሉ፤ በዚያም ምግብ የሚሆናቸው ለምለም ሣር ይፈልጋሉ።

9 “ጎሽ የተባለው የዱር እንስሳ አንተን ለማገልገል ፈቃደኛ ይሆናልን? በበረትህስ ውስጥ ሊያድር ይችላልን?

10 ጐሽን ጠምደህ ሞፈር እየጐተተ እንዲያርስ ልታደርገው ትችላለህን?

11 ስለ ብርቱ ጥንካሬው በእርሱ ትተማመናለህን? ከባድ ሥራህንስ ለእሱ ትተውለታለህን?

12 ወደ አንተ እንደሚመለስና ሰብልህን ወደ አውድማ እንደሚያመጣልህ ትተማመንበታለህን?

13 “ሰጎን ክንፎችዋን በፍጥነት ትዘረጋለች፤ ነገር ግን እንደ ሸመላ አትበርም።

14 ሰጎን እንቊላልዋን በምድር ላይ ትጥላለች፤ በዐፈር ላይ ተቀምጦም እንዲሞቅ ታደርጋለች።

15 ‘በዚያ የሚያልፍ በእግሩ ይሰብረዋል፤ የዱር አውሬም ረግጦ ያደቀዋል’ ብላ አታስብም።

16 ጫጩቶችዋ የእርስዋ እንዳልሆኑ አድርጋ ትጨክንባቸዋለች፤ ድካምዋ ሁሉ በከንቱ ቢቀር ደንታ የላትም።

17 እንደዚህ ጥበብ የነሣኋትና ሞኝ እንድትሆን ያደረግኋት እኔ ነኝ።

18 ተነሥታ በምትሮጥበት ጊዜ ግን፥ ፈረስና ፈረሰኛው ሊወዳደሩአት ቢሞክሩ ትስቅባቸዋለች።

19 “ኢዮብ ሆይ! ለፈረሶች ኀይልን የሰጠህ፥ በረጃጅምም ጋማ ያስጌጥካቸው አንተ ነህን?

20 እንደ አንበጣ እየዘለሉ በማንኮራፋት ሰውን እንዲያስደነግጡ የምታደርጋቸው አንተ ነህን?

21 ፈረሶቹ ወደ ጦር ሜዳ ተጋልበው ሲሄዱ በጒልበታቸው በመመካት ሶምሶማ ይረግጣሉ።

22 ፍርሀት የሚባል ነገር ከቶ አያውቁም፤ ምንም ነገር አያስደነግጣቸውም፤ ሰይፍ ቢመዘዝባቸው እንኳ ወደ ኋላ አይመለሱም።

23 የሚጋልቡአቸው ጦረኞች የያዙአቸው የጦር መሣሪያዎች በፀሐይ እየተብለጨለጩ እርስ በርሳቸው ሲፋጩ ይሰማል።

24 እምቢልታው ሲነፋ ሲቃ ይዞአቸው በጭካኔና በቊጣ ወደ ጦር ሜዳ ይሸመጥጣሉ።

25 እምቢልታ በተነፋ ቊጥር በደስታ ያናፋሉ፤ በሩቅ ሆነው ጦርነቱን በሽታ ያውቃሉ፤ የጦር አዛዦች የሚሰጡትን ትእዛዝና የሠራዊቱን ድንፋታ ይሰማሉ።

26 በውኑ ጭልፊት የሚያንዣብበው፥ ክንፎቹንም ወደ ደቡብ የሚዘረጋው በአንተ ጥበብ ነውን?

27 ንስርን ወደ ላይ ወጥቶ በከፍተኛም ቦታ ላይ ጎጆውን የሚሠራው አንተ አዘኸው ነውን?

28 ንስር በቋጥኞች መካከል ይኖራል፤ እዚያም ጎጆውን ይሠራል። ቋጥኞቹም መከላከያ ይሆኑለታል።

29 እዚያም ሆኖ የሚነጥቀውን ነገር ያማትራል፤ ዐይኖቹም በሩቅ ያለውን ያያሉ።

30 በዚህ ዐይነት ንስሮች በበድን ዙሪያ ይሰበሰባሉ፤ ጫጩቶቻቸውም ደሙን ይጠጣሉ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告