Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 38 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የእግዚአብሔር መልስ

1 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ኢዮብን እንዲህ አለው፦ እግዚአብሔር

2 “ይህ፥ ያለ ዕውቀት በሚነገሩ ቃላት ምክሬን የሚያቃልል እርሱ ማነው?

3 እስቲ በፊቴ እንደ ወንድ ታጠቅ፤ እጠይቅሃለሁ፤ አንተም መልስልኝ።

4 ለመሆኑ ዓለምን ስፈጥር አንተ በዚያ ነበርክን? የምታውቅና የምታስተውል ከሆነ እስቲ ንገረኝ።

5 የምድርን መጠን የወሰነ ማን ነው? በእርሱዋ ላይስ የመለኪያ መስመሮችን የዘረጋ ማን እንደ ሆነ ታውቃለህን?

6 የምድርን ምሰሶዎች አጽንቶ የያዘ ኀይል ምንድን ነው? የዓለምንስ የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጠ ማን ነው?

7 የንጋት ከዋክብት በአንድነት ሲዘምሩ፥ መላእክትም ሁሉ እልል ሲሉ አንተ የት ነበርክ?

8 “ከምድር ውስጥ ፈንድቶ በወጣ ጊዜ የመፍለቂያ በሮቹን የዘጋ ማነው?

9 ባሕርን በደመና የጋረድኩ በድቅድቅ ጨለማም የሸፈንኩ እኔ ነኝ።

10 ለባሕር ወሰንን የሠራሁ፥ በርና ገደብም እንዲኖረው ያደረግኹ እኔ ነኝ።

11 እስከዚህ ድረስ ትመጣለህ! ከዚህም አታልፍም! የአንተም ብርቱ ማዕበል እዚህ ይቁም! ያልኩ እኔ ነኝ።

12 ኢዮብ ሆይ! በሕይወት ዘመንህ ሁሉ ከቶ ንጋትን አዘህ ታውቃለህን? ለንጋት ወገግታስ ቦታ መድበህለታልን?

13 ንጋት በምድር ላይ ብርሃን እንዲያሳይ፥ ክፉ ሰዎችንም ከተደበቁበት ቦታ እንዲያጋልጥ ትእዛዝ ሰጥተህ ታውቃለህን?

14 የንጋት ብርሃን ኰረብቶችንና ሸለቆዎችን እንደ ተጣጠፈ ልብስ ቈመው እንዲታዩ ያደርጋቸዋል፤ በሸክላ ላይ እንዳለ መኅተምም አጒልቶ ያሳየዋል።

15 ክፉዎች ብርሃን ተከልክለዋል፤ ለዐመፅ ያነሡአቸው ክንዶቻቸውም ተሰብረዋል።

16 “ወደ ባሕሩ ጥልቀት ወርደሃልን? በውቅያኖስ ወለል ላይ ተመላልሰህ ታውቃለህን?

17 የሞትን በሮች እንድታይ ተደርገሃልን? የድቅድቅ ጨለማንስ መዝጊያ አይተሃልን?

18 ዓለም ምን ያኽል ትልቅ እንደ ሆነች ማወቅ ትችላለህን? እስቲ ይህን ሁሉ ታውቅ እንደ ሆነ ንገረኝ።

19 “ወደ ብርሃን የሚወስደውን መንገድ ጨለማስ የት እንደሚኖር ታውቃለህን?

20 ብርሃንንና ጨለማን ወደየቦታቸው ልትወስዳቸው ትችላለህን? ወደ መኖሪያቸው የሚወስደውን መንገድ ታውቃለህን?

21 ዓለም በተፈጠረ ጊዜ ተወልደህ ስለ ነበረ በእርግጥ ታውቃለህ! ዕድሜህም በጣም የገፋ ነው!

22 “ወደ በረዶ ማስቀመጫ ቤት ገብተሃልን? ወይስ የተቀመጠውን የበረዶ ክምችት አይተሃልን

23 ይህም በረዶ እኔ በጦርነትና በውጊያ ላይ እንድጠቀምበት ለችግር ጊዜ ያስቀመጥኩት ነው።

24 ብርሃን የሚከፋፈልበት ቦታ ወዴት ነው? ወይስ ደረቅ ነፋስ በምድር ላይ የሚሠራጭበት ቦታ ወዴት ነው?

25 “ለዝናብ መውረጃን ያዘጋጀለት፥ ነጐድጓድ ለተቀላቀለበት ውሽንፍርም መንገድ ያበጀለት ማነው?

26 እንዲሁም ማንም በሌለበት ምድር፥ ሰው በማይኖርበት ምድረ በዳ፥

27 ዝናብ እንዲዘንብ የሚያደርግ ማነው? ጠፍና ባድማ የሆነውን መሬት ረስርሶ ምድሩንም ሣር እንዲያበቅል ያደረገው ማነው?

28 ዝናብንና ጤዛን የሚያስገኝ ማነው?

29 በረዶንና አመዳይን የሚያስገኝ ማነው?

30 ውርጩ ውሃን እንደ ድንጋይ ያጠጥራል፤ የባሕሩም ወለል እንደ በረዶ እንዲረጋ ያደርገዋል።

31 “ ‘ፕልያዲስ’ የተባሉትን ከዋክብት በአንድነት ማሰር ትችላለህን? ኦርዮን የተባሉትንስ ከዋክብት የተያያዙበትን ገመድ መበጠስ ትችላለህን?

32 ከዋክብትን ሁሉ በየወቅታቸው ማሰማራት ትችላለህን? የድብ ቅርጽ ያላቸውን ከዋክብትስ ከልጆቻቸው ጋር መምራት ትችላለህን?

33 ሰማያት በምን ዐይነት ሥርዓት እንደሚተዳደሩ ታውቃለህን? ይህንንስ ደንብ በምድር ላይ እንዲሠራ ለማድረግ ትችላለህን?

34 “ብዙ ዝናብ እንዲያዘንብልህ፥ ደመናን ልታዘው ትችላለህን?

35 መብረቅ በአንተ ትእዛዝ ይበርቃልን?

36 ለልብ ጥበብን ለአእምሮስ ማስተዋልን የሰጠ ማነው?

37-38 በጥበቡ ደመናን ለመቊጠር የሚችል ማነው? የተሰበሰበው ዐፈር ርሶ ጭቃ እንዲሆን ከማከማቻው ከሰማይ ውሃ ወደታች ለማፍሰስ የሚችል ማነው?

39 በጫካው ውስጥ ታጋድመውና አድብተው ሳሉ ለአንበሳይቱ አደን ታድናለህን?

40 የተራቡ ልጆችዋንስ መመገብ ትችላለህን?

41 ልጆችዋ ምግብ አጥተው ሲቅበዘበዙ ወደ እኔም ሲጮኹ ለቁራ ምግብ የሚሰጣት ማነው?”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告