ኢዮብ 37 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 “በውሽንፍሩም ኀይል ልቤ ተንቀጠቀጠ፤ በፍርሃትም ተርበደበደ። 2 ከአፉ የሚወጣውን ድምፅ ስሙ እንደ ነጐድጓድ የሚያጒረመርመውን ቃሉን አድምጡ። 3 መብረቁን ከሰማይ በታች ሁሉ ያሠራጫል፤ እስከ ምድር ዳርቻም ድረስ ይልካል። 4 ከዚህም በኋላ ኀይለኛ ድምፁን ያስገመግማል፤ የሚያስፈራ ድምፁንም እንደ ነጐድጓድ ያሰማል፥ የመብረቁም ብልጭታ ደጋግሞ ይታያል። በግርማዊ ድምፁም ነጐድጓድን ያሰማል፤ ድምፁን በሚያሰማበት ጊዜ መብረቁን አያግድም። 5 እግዚአብሔር አስደናቂ በሆነ ድምፁ ነጐድጓድን ያሰማል፤ እኛ ልንረዳው የማንችል ታላላቅ ነገሮችንም ያደርጋል። 6 በረዶ በምድር ላይ እንዲወርድ ያደርጋል፤ ብርቱ ዝናብም እንዲዘንብ ያዛል። 7 እርሱ የፈጠራቸው ሰዎች የእርሱን ሥራ እንዲያውቁ፥ ሰዎች ሁሉ ሥራቸውን እንዲያቆሙ ያደርጋል። 8 በዚያን ጊዜ የዱር አውሬዎች ሸሽተው ወደየመሸሸጊያቸው ይገባሉ፤ በየዋሻቸውም ውስጥ ይሰወራሉ። 9 ብርቱ ነፋስ ከደቡብ ይነሣል። ብርዳማ ነፋስም ከሰሜን ይመጣል። 10 የእግዚአብሔር እስትንፋስ ውሃን ያቀዘቅዛል፤ ወደ በረዶም ይለውጠዋል። 11 ደመና ውሃ እንዲሸከም ያደርጋል፤ በውስጡም መብረቅን ያበርቃል። 12 ደመናዎች በጌታ መሪነት በምድር ዙሪያ ይዞራሉ፤ የሚያግዛቸውንም ትእዛዞች ይፈጽማሉ። 13 እግዚአብሔር ዝናብን የሚያዘንበው፥ ምድርን ለማረስረስ፥ ሰዎችን ለመቅጣት፥ ወይም ፍቅሩን ለመግለጥ ነው። 14 “ኢዮብ ሆይ! እስቲ ዝግ ብለህ አድምጥ፤ እግዚአብሔር የሚያደርጋቸውንም ድንቅ ሥራዎች ልብ ብለህ አስተውል። 15 እግዚአብሔር ደመናን እንዴት እንደሚቈጣጠር፥ መብረቅንም እንዴት እንደሚያበርቅ ታውቃለህን? 16 ደመናን በሕዋው ላይ የሚያንሳፍፈውንና ሁሉን የሚያውቀውን የአምላክን ድንቅ ሥራ ታውቃለህን? 17 ሰማዩ ነሐስ በመሰለ ጊዜ አንተ በኀይለኛው የበረሓ ነፋስ በሙቀት ትቀልጣለህ። 18 እግዚአብሔር ሰማይን እንደ ቀለጠ መስተዋት ቢዘረጋ፥ አንተ በአጠገቡ ሆነህ ትረዳዋለህን? 19 አእምሮአችን ጨለማ በመሆኑ ጉዳያችንን ለማቅረብ ስለማንችል፥ ለእግዚአብሔር ምን እንደምለው ንገረን፤ 20 እግዚአብሔርን ልናገር ብዬ በመጠየቅ ለምን ያጠፋኝ ዘንድ አነሣሣዋለሁ? 21 “ነፋሱ ደመናውን ከሰማይ ላይ በገፈፈው ጊዜ ማንም ፀሐይን ትኲር ብሎ መመልከት አይችልም። 22 ከሰሜን በኩል ወርቅ የመሰለ ብርሃን ይመጣል፤ እግዚአብሔርም በሚያስደንቅ ግርማ ይገለጣል። 23 እግዚአብሔር ሊታይ አይቻልም፤ ሥልጣኑም ታላቅ ነው፤ እርሱም ትክክለኛ ፈራጅ ነው። 24 በሐሳባቸው ጠቢባን ነን የሚሉትን ስለሚንቃቸው ሰዎች ሁሉ ይፈሩታል።” |