Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 36 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 ኤሊሁ አሁንም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦

2 “ ስለ እግዚአብሔር የምናገረው ገና ሌላ ነገር ስላለ፥ እንዳብራራልህ ጥቂት ታገሠኝ።

3 ከእግዚአብሔር ባገኘሁት ዕውቀት ፈጣሪዬ እግዚአብሔር እውነተኛ መሆኑን አስረዳለሁ።

4 ንግግሬ ሐሰት ላለመሆኑ እርግጠኛ ሁን፤ ከአንተ ጋር የምነጋገረው እኔ የተሟላ ዕውቀት እንዳለኝ ዕወቅ።

5 “በእርግጥ እግዚአብሔር ኀያል ነው፤ ማንንም አይንቅም፤ እርሱም ሁሉንም ነገር ያስተውላል።

6 እርሱ ክፉ ሰዎች በሕይወት እንዲኖሩ አያደርግም፤ ለተጨቈኑ ሰዎች ግን በቅንነት ይፈርድላቸዋል።

7 እግዚአብሔር ደጋግ ሰዎችን ይጠብቃል፤ እንደ ነገሥታትም በዙፋን ላይ ያስቀምጣቸዋል፤ ለዘለዓለምም ከፍ ከፍ ያደርጋቸዋል።

8 ነገር ግን ሰዎች በሰንሰለት ቢታሰሩ፥ ወይም በችግር ወጥመድ ቢያዙ፥

9 እነርሱ በትዕቢታቸው፥ የሠሩትን ኃጢአት ይገልጥባቸዋል።

10 ተግሣጽን እንዲሰሙ ጆሮአቸውን ይከፍትላቸዋል፤ ከክፉ ሥራቸውም ተመልሰው ንስሓ እንዲገቡ ያዛቸዋል።

11 ለእግዚአብሔር ቢታዘዙና ቢያገለግሉ፥ ቀሪ ዘመናቸውን በብልጽግናና በደስታ ያሳልፋሉ።

12 እርሱን ካልሰሙት በሰይፍ ይጠፋሉ፤ በድንቊርና እንዳሉም ይሞታሉ።

13 “በልባቸው እግዚአብሔርን የሚክዱ ዘወትር እንደ ተቈጡ ይኖራሉ፥ ሲቀጣቸው እንኳ ይቅርታ ለማግኘት አይጸልዩም።

14 በሚፈጽሙትም ግብረ ሰዶም ይቀሠፋሉ። በወጣትነታቸውም በሞት ይቀጫሉ።

15 እግዚአብሔር በሥቃይ ላይ ያሉትን፥ ከሥቃይ ያድናቸዋል። በደረሰባቸውም መከራ ትምህርት ይሰጣቸዋል።

16 “በአሁኑም ወቅት እግዚአብሔር የሚፈቅደው፥ አንተን ከችግር አውጥቶ ምርጥ በሆነ ምግብ ወደተሞላ ማእድ ሊመራህ ነው።

17 አሁን ግን የበደለኛ ፍርድ ስለ ተፈረደብህ፥ ተገቢ ቅጣትህን በመቀበል ላይ ነህ።

18 ማንም ሰው በሀብት ብዛት እንዳያስትህ፥ በጉቦም እንዳይደልልህ ተጠንቀቅ።

19 ሀብትህና ሥልጣንህ ምንም ያህል ከፍተኞች ቢሆኑ፥ ከጭንቀት አያድኑህም።

20 ሕዝቦች ከስፍራቸው የሚጠፉበት የጨለማ ጊዜ እንዲመጣ አትመኝ።

21 በችግር የምትፈተነው በዚህ ምክንያት ስለ ሆነ ተመልሰህ ክፉ ከመሥራት ተጠንቀቅ።

22 የእግዚአብሔር ኀይል ምን ያኽል ታላቅ መሆኑን አስተውል፤ እግዚአብሔር ከሁሉ የበለጠ አስተማሪ ነው።

23 ‘ይህን አድርግ’ ብሎ የሚያዘው፥ ወይም ‘ክፉ ሥራ ሠርተሃል’ ብሎ የሚወቅሰው ማነው?

24 ሰዎች ሁልጊዜ በሚሠራው ሥራ በመዝሙር እንደሚያመሰግኑት። አንተም የእርሱን ሥራ በመዝሙር አመስግን።

25 የእግዚአብሔርን ሥራ የሰው ዘር ሁሉ አይቶታል፤ ሰዎች በሩቅ ይመለከቱታል።

26 የእግዚአብሔርን ታላቅነት መርምረን ልንደርስበት አንችልም፤ የዘመኑንም ልክ መመርመር አይቻልም።

27 “እግዚአብሔር ውሃን ከባሕር ወደ ላይ ይስባል፤ ከሰማይም ያዘንበዋል።

28 ከደመናው ዝናብ እየጐረፈ ይወርዳል፤ በሰዎችም ላይ በብዛት ይዘንባል።

29 ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ደመናውን እንዴት እንደሚዘረጋና በነጐድጓድም ውስጥ ሆኖ እንዴት እንደሚናገር፥ ማን ሊረዳ ይችላል?

30 እግዚአብሔር የባሕሩን ጥልቀት እየሸፈነ መብረቁን በዙሪያው እንዴት እንደሚበትን ተመልከት።

31 በዚህ ዐይነት እግዚአብሔር ሕዝብን ያስተዳድራል፤ ምግብንም በብዛት ያዘጋጅላቸዋል።

32 መብረቅን በእጁ ይይዛል፤ ወደተወሰነለትም አቅጣጫ እንዲሄድ ያዘዋል።

33 ነጐድጓድ፥ ኀይለኛ ዝናብ መምጣቱን ያመለክታል፤ እንስሶችም ውሽንፍር መምጣቱን ያውቃሉ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告