ኢዮብ 34 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ኤሊሁም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦ 2 “እናንተ ጠቢባን የምናገረውን ስሙኝ፤ እናንተም ዐዋቂዎች አድምጡኝ። 3 የምግብ ጣዕም በምላስ እንደሚታወቅ፥ ንግግርም በጆሮ ይለያል። 4 ትክክለኛ የሆነውን ነገር መርምረን እንወቅ፤ መልካሙንም ነገር አብረን እንማር። 5 ኢዮብ ‘እኔ ንጹሕ ነኝ፤ እግዚአብሔር ግን ፍትሕ ነፈገኝ። 6 እኔ እውነተኛ ስሆን፥ እንደ ውሸተኛ ተቈጠርኩ፤ ምንም በደል ሳይኖርብኝ በማይፈወስ ቊስል እሠቃያለሁ’ ብሎአል። 7 “እንደ ኢዮብ በእግዚአብሔር ላይ የሚያፌዝ ሰው ከቶ ይገኛልን? 8 ጓደኞቹ ክፉ አድራጊዎች ናቸው፤ የሚውለውም ከክፉ አድራጊዎች ጋር ነው። 9 ‘እግዚአብሔርን ማስደሰት፥ ለሰው ምንም አይጠቅመውም’ ይላል። 10 “አስተዋዮች የሆናችሁ ሰዎች አድምጡኝ! ክፋትን ማድረግ ከእግዚአብሔር፥ ስሕተትንም ማድረግ ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ! 11 እግዚአብሔር ለሰው እንደ ሥራው ይከፍለዋል፤ በአካሄዱም መጠን የሚገባውን ያደርግለታል። 12 ሁሉን የሚችል አምላክ ከቶ ክፉ ነገር አያደርግም፤ በማንኛውም ሰው ላይ ፍርድን አያዛባም። 13 ምድርን ለእግዚአብሔር ዐደራ የሰጠው የለም፤ በዓለም ላይ ኀላፊ አድርጎ የሾመው የለም። 14 እግዚአብሔር መንፈሱንና እስትንፋሱን ወደ ራሱ ለመመለስ ቢያስብ፥ 15 የሰው ዘር ሁሉ በአንድነት በጠፋ ነበር፤ ወደ ዐፈርም በተመለሰ ነበር። 16 አስተዋይ ብትሆን ይህን ስማ፤ ንግግሬንም አድምጥ። 17 ፍትሕን የሚጠላ መግዛት ይችላልን? ጻድቁንና ኀያሉን እግዚአብሔር በደለኛ ታደርገዋለህን? 18 ንጉሡን የማትጠቅም ነህ፤ መኳንንቱንም ክፉዎች ናችሁ፤ የሚላቸው ማነው? 19 ሁሉም የእጁ ሥራዎች ስለ ሆኑ፤ እርሱ ለመኳንንቱ አያደላም ባለጸጋውን ከድኻው አይለይም። 20 ሰዎች በእኩለ ሌሊት በቅጽበት ሊሞቱ ይችላሉ። ተንቀጥቅጠውም ያልፋሉ። ኀያላንም የማንም ሰው እጅ ሳይነካቸው ይወገዳሉ። 21 እግዚአብሔር የሰዎችን ሁሉ እርምጃ ይመለከታል። የእያንዳንዳቸውን እርምጃ ይቈጣጠራል። 22 ክፉ አድራጊዎች የሚደበቁበት፤ ድቅድቅ ጨለማ ከቶ የለም። 23 በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ ለመቅረብ ቀጠሮ አይሰጣቸውም። 24 ገዢዎችን ከሥልጣናቸው አውርዶ፥ በቦታቸው ሌሎችን ለመተካት፥ ምርመራ አያስፈልገውም። 25 ስለዚህም ሥራቸውን ዐውቆ፥ በአንድ ሌሊት ከሥልጣናቸው አስወግዶ ያጠፋቸዋል። 26 በሠሩት ዐመፃ ምክንያት ኃጢአተኞችን በሰው ፊት ይቀጣቸዋል። 27 ይህንንም የሚያደርግባቸው፥ እርሱን መከተል ስለ ተዉና ትእዛዞቹንም ስለ ናቁ ነው። 28 ድኾችን በመጨቈን ወደ እግዚአብሔር እንዲጮኹ አድርገዋቸዋል፤ እግዚአብሔርም የድኾችን ጩኸት ሰምቶአል። 29-30 “እግዚአብሔርን የሚክድና ሕዝቡን የሚያጠምድ ንጉሥ ሲነግሥ፥ እግዚአብሔር ዝም ቢል፥ ወይም ፊቱን ቢሰውር ማን ሊወቅሰው ይችላል? 31 “ምናልባት አንድ ሰው ለእግዚአብሔር ‘እስከ አሁን በድዬአለሁ ዳግመኛ አልበድልም፥ 32 የሠራሁት ኃጢአት የትኛው እንደ ሆነ አስተምረኝ፤ በድዬም ከሆነ፥ ዳግመኛ አልሠራም’ ያለው ሰው አለን? 33 ታዲያ፥ አንተ ንስሓ መግባት እንቢ እያልክ፥ አንተ በምታቀርበው ሐሳብ መሠረት እግዚአብሔር ምኞትህን እንዲፈጽምልህ ትፈልጋለህን? 34 “የሚሰሙኝ ሰዎች እንዲህ ይሉኛል፤ የሚያስተውሉ ሰዎች እንዲህ ይላሉ፦ 35 ‘ኢዮብ የሚናገረው ያለ ዕውቀት ነው፤ ንግግሩም ፍሬ ቢስ ነው’ 36 የክፉዎች ሰዎችን የመሰለ መልስ ስለሚሰጥ ምነው ኢዮብ እስከ መጨረሻው ድረስ በተፈተነ! 37 በመካከላችን ሕገ ወጥ በመሆን፥ በእግዚአብሔር ላይ ንቀትን በማብዛት ኢዮብ በኃጢአቱ ላይ ዐመፅን ጨምሮአል።” |