Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 30 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 “አሁን ግን በዕድሜ ከእኔ ያነሱ ሰዎች ያፌዙብኛል፤ የእነርሱ አባቶች የበጎቼን መንጋ ከሚጠብቁ ውሾቼ ጋር እንኳ እንዲሰማሩ የምንቃቸው ሰዎች ነበሩ።

2 ኀይላቸው የደከመ ስለ ነበረ፥ ለእኔ ምንም አይጠቅሙኝም ነበር።

3 ከችግርና ከራብ ብዛት የተነሣ፥ ወደ በረሓ እየሄዱ ሥራ ሥሮችን ያኝኩ ነበር።

4 ጨው ጨው የሚሉ የበረሓ ቅጠላ ቅጠሎችን ይለቅሙ ነበር፤ ጣዕም የሌላቸውንም የክትክታ ሥሮች ይበሉ ነበር።

5 ሰዎች ሌቦችን እየጮኹ እንደሚያባርሩ፥ እነርሱንም ከኅብረተሰቡ መካከል ያባርሩአቸው ነበር፤

6 መኖሪያቸውንም በየዋሻውና በየገደሉ ሥር በተቈፈሩ ጒድጓዶች ውስጥ ለማድረግ ተገደዱ።

7 በየጫካው እየዞሩ እንደ ዱር አውሬ ይጮኹ ነበር፤ በየቊጥቋጦውም ሥር ተሰባስበው ይኖሩ ነበር።

8 በጅራፍ እየተገረፉ ከአገር በመባረራቸው፥ ስማቸው የጠፋ አእምሮ ቢሶች ሆነው ይኖሩ ነበር።

9 “አሁን ልጆቻቸው በዘፈን ያፌዙብኛል፤ በመካከላቸውም የመሳለቂያ ርእስ ሆኛለሁ።

10 ተጸይፈውኝ ከእኔ ይርቃሉ፤ ያለ አንዳች ኀፍረት በፊቴ ምራቃቸውን ይተፋሉ።

11 እግዚአብሔር ኀይሌን አድክሞ ስላዋረደኝ፥ እነርሱ ልጓሙ እንደ ወለቀለት ፈረስ እንዳሻቸው ፈነጩብኝ።

12 በስተቀኜ በኩል ስድ ዐደጎች ተነሡብኝ፤ እግሬንም ለማሰናከል ወጥመድ አጠመዱ፤ በእኔም ላይ ከበባ አደረጉ።

13 መተላለፊያ መንገዴን ዘግተው ሊያጠፉኝ ይፈልጋሉ፤ ይህን ከማድረግ የሚገታቸው የለም።

14 ጐርፍ ጥሶ እንደሚገባ መከላከያዬን ጥሰው ገቡ፤ ሁሉንም እየሰባበሩ በእኔ ላይ መጡ።

15 ታላቅ ድንጋጤ ይዞኛል፤ ክብሬ እንደ ነፋስ ሽውታ አልፎአል፤ የመዳኔም ተስፋ እንደ ጉም በኖ ጠፍቶአል።

16 “ነፍሴ እጅግ ተጨነቀች ለሞትም ተቃርቤአለሁ።

17 ሌሊቱን ሙሉ አጥንቶቼ በሕመም ይሠቃያሉ፤ ሕመሙም ዕረፍት አይሰጠኝም።

18 ከሕመሜ ጽናት የተነሣ ልብሴ ተቈራፍዶ ተበላሽቶአል፤ እንደ ሸሚዝ ክሳድ አንቆ ይዞኛል።

19 እግዚአብሔር ዐፈር ላይ ወርውሮ ስለ ጣለኝ፥ ትቢያና ዐመድ መስያለሁ።

20 “እግዚአብሔር ሆይ! አንተን ለመንኩ፤ ነገር ግን አልመለስክልኝም፤ ቆሜም ወደ አንተ ጸለይኩ፤ አንተ ግን ፊትህን አልመለስክልኝም።

21 እጅግ ጨከንክብኝ፤ በታላቅ ኀይልህም አሳደድከኝ።

22 አንሥተህ በነፋስ ላይ አስቀመጥከኝ፥ እንዲያዞረኝም አደረግህ፤ ዐውሎ ነፋሱም ያንገዋልለኛል።

23 የሰው ሁሉ ዕድል ፈንታ ለሆነው ለሞት አሳልፈህ እንደምትሰጠኝ ዐውቃለሁ።

24 አንድ የተቸገረ ሰው ለእርዳታ እጁን ዘርግቶ ሲጮኽ በእርግጥ ማንም ሰው አያጠቃውም።

25 ለተቸገሩ ሰዎች አላለቀስኩምን? ለድኾችስ አልተጨነቅኹምን?

26 መልካም ነገር አገኛለሁ ብዬ ስመኝ፥ ክፉ ነገር ደረሰብኝ፤ ብርሃን ይወጣልኛል ብዬ ስጠባበቅ፥ ቀኑ ጨለመብኝ።

27 ልቤ ተጨነቀች፤ ምንም ሰላም አላገኘሁም፤ የመከራ ቀኖችም ደረሱብኝ።

28 ሰውነቴ በፀሐይ ቃጠሎ ሳይሆን በሐዘን ጠቈረ፤ በአደባባይም መካከል ቆሜ ርዳታ እጠይቃለሁ።

29 ከሰው ተለይቼ ለቀበሮ ወንድም ለሰጎንም ባልንጀራ ሆንኩ።

30 ቆዳዬ ጠቊሮ ተገለፈፈ፤ ሰውነቴም በትኩሳት ተቃጠለ።

31 ደስታዬን እገልጥባቸው የነበሩት በገና እና እምቢልታ አሁን የሐዘን እንጒርጒሮዬ ማሰሚያ ሆነዋል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告