Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ኢዮብ የተወለደበትን ቀን መርገሙ ኢዮብ

1 ከዚህ በኋላ ኢዮብ መናገር ጀመረ፤ የተወለደበትን ቀን እንዲህ ሲል ረገመ፦

2-3 “የተፀነስኩበት ሌሊት፥ የተወለድኩበትም ቀን የተረገመ ይሁን!

4 ያ ቀን ወደ ጨለማ ይለወጥ፤ የሰማይ አምላክ አያስበው፤ ብርሃን ከቶ አይታይበት።

5 በጭጋግና በድቅድቅ ጨለማ የተሸፈነ ይሁን፤ ደመና ረቦበት ጨለማ ብርሃኑን ይዋጠው፤

6 ያን ሌሊት ድቅድቅ ጨለማ ይሸፍነው፤ ከዓመቱ ቀኖች ጋር አይቈጠር፤ ከወሮቹም ውስጥ ገብቶ አይታሰብ።

7 ያ ሌሊት ባዶ ይሁን፤ የደስታም ድምፅ አይሰማበት።

8 ሌዋታንን መቀስቀስ የሚችሉና ቀኖችን የሚረግሙ አስማተኞች ያን ቀን ይርገሙት።

9 የዚያ ሌሊት አጥቢያ ኮከቦች ይጨልሙ፤ የብርሃን ተስፋ አይገኝበት፤ የንጋትም ጮራ አይፈንጥቅበት።

10 ችግርን ከዐይኖቼ ለመሸሸግ የማሕፀን በሮችን በእኔ ላይ ስላልዘጋ ያ ቀን የተረገመ ይሁን።

11 “ምነው በእናቴ ማሕፀን ሳለሁ ውሃ ሆኜ በቀረሁ! ከማሕፀን ስወጣስ ለምን አልጠፋሁም?

12 ጒልበቶች እኔን ለመቀበል፥ ጡቶችም እኔን ያጠቡ ዘንድ ለምን ተገኙ?

13 አሁን በሰላም በተጋደምኩ፥ አንቀላፍቼም ዕረፍት ባገኘሁ ነበር።

14 አሁን ፈርሰው የሚታዩትን ለራሳቸው ከገነቡት የምድር ነገሥታትና አማካሪዎች ጋር አንቀላፍቼ ዕረፍት ባገኘሁ ነበር።

15 ቤቶቻቸውን በወርቅና በብር ከሞሉ መሳፍንት ጋር አብሬ በተኛሁ ነበር፤

16 ወይስ ለምን በመሬት ውስጥ እንደ ተቀበረ ጭንጋፍ የቀንን ብርሃን ፈጽሞ እንዳላየ ሕፃን አልሆንኩም?

17 በዚያ ክፉዎች አስቸጋሪነታቸው ይቀራል፤ በአድካሚ ሥራም የኖሩ ያርፋሉ።

18 እስረኞች እንኳ ሰላም ያገኛሉ፤ የአሠሪዎቻቸውን የቊጣ ድምፅ ከመስማት ይድናሉ።

19 ታናናሽና ታላላቅ ሰዎች በአንድነት ይገኛሉ፤ ባሪያዎችም በዚያ ከጌቶቻቸው ነጻ ይወጣሉ።

20 “በጭንቀት ላይ ላሉ ብርሃን፥ ኑሮአቸው በመራራ ሐዘን ለተመላ ሕይወት የሚሰጣቸው ለምንድነው?

21 ሞትን ለሚናፍቁና፥ ከተደበቀ ሀብት ይልቅ ፈልገው የማያገኙት ሕይወት የሚሰጣቸው ለምንድን ነው?

22 ወደ መቃብር ሲደርሱ ደስታ ለሚሰማቸው ሕይወት የሚሰጣቸው ለምንድን ነው?

23 መንገዱ ለተሰወረበትና እግዚአብሔር ለዘጋበት ሰው ብርሃን የሚሰጠው ለምንድን ነው?

24 በምግብ ፈንታ እቃትታለሁ፤ ጩኸቴም እንደ ፈሳሽ ውሃ ነው።

25 የፈራሁት ነገር መጥቶብኛል፤ የደነገጥሁበትም ነገር ደርሶብኛል።

26 በውስጤ ሁከት ብቻ ስላለ፥ ሰላም፥ ጸጥታና ዕረፍት የለኝም።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告