Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 29 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የኢዮብ የመጨረሻ ስሞታ

1 ኢዮብም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦

2 “የአሁኑ ኑሮዬ ቀድሞ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ እንደ ነበረው ጊዜ ቢሆንልኝ እንዴት ደስ ባለኝ ነበር!

3 ያን ጊዜ በጨለማ ውስጥ ስሄድ፥ እግዚአብሔር መብራቱን እያበራልኝ በብርሃን እራመድ ነበር።

4 ምነው የእግዚአብሔር ረድኤት ቤቴን ይጠብቅ እንደ ነበረበት እንደ ወጣትነቴ ጊዜ በሆንኩ!

5 ሁሉን የሚችል አምላክ ገና ስላልተለየኝ፥ ልጆቼ ሁሉ በዙሪያዬ ነበሩ።

6 እግሮቼ እንኳ በወተት እስኪታጠቡ ድረስ ብዙ ወተት አገኝ ነበር። የወይራ ዛፎቼም በጭንጫ መሬት ላይ እንኳ ተተክለው እንደ ጐርፍ የሚወርድ ብዙ ዘይት ይሰጡኝ ነበር።

7 ወደ ከተማም አደባባይ እየሄድኩ በሸንጎ እቀመጥ በነበረ ጊዜ፥

8 ወጣቶች እኔን ሲያዩ በአክብሮት ከፊቴ ገለል ይሉ ነበር፤ ሽማግሌዎችም ስለ እኔ ክብር ከተቀመጡበት ይነሡ ነበር።

9 ሲነጋገሩ የነበሩ የሕዝብ መሪዎችም እኔን ሲያዩ እጆቻቸውን በአፋቸው ላይ አድርገው ጸጥ ይሉ ነበር።

10 የአገር መኳንንትም እኔ ባለሁበት ጸጥ ይሉ ነበር፤ ምላሳቸው ተሳስሮ መናገር ያቅታቸው ነበር።

11 “የሰማኝ ሁሉ አሞገሰኝ፤ ያየኝ ሁሉ አመሰገነኝ።

12 ይህም የሆነው የድኾችን ጩኸት ሰምቼ እታደጋቸውና፥ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውንም ልጆች እረዳቸው ስለ ነበረ ነው።

13 ለሞት የተቃረቡትን ሰዎች ስለምረዳ መረቁኝ፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶች ስለምረዳቸው በደስታ ይዘምሩ ነበር።

14 ጽድቅን እንደ ልብስ ለበስኳት፤ ትክክለኛ ፍርድንም እንደ ካባ ደረብኳት፤ እንደ ቆብም ደፋኋት።

15 ለዕውሮች ዐይን፥ ለአንካሶችም እግር ነበርኩ።

16 ለድኾች አባት፥ ለማላውቃቸውም ሰዎች ጠበቃ ነበርኩ።

17 የግፈኛውን መንጋጋ ሰበርኩ፤ ነጥቆ የወሰደውንም ከአፉ አስጣልኩ።

18 “ ‘ዕድሜዬ እንደ አሸዋ በዝቶ፥ በቤቴ እንዳለሁ በክብር እሞታለሁ’ ብዬ ነበር።

19 ሥሮቹ ዘወትር ውሃ እንደሚያገኙና ቅርንጫፎቹም በጠል እንደሚርሱ ዛፍ ነበርኩ።

20 ሁልጊዜ እንደ ተከበርኩ እኖር ነበር ኀይሌም ዘወትር ይታደስ ነበር።

21 ሰዎች እኔን በማዳመጥ ጸጥ ይሉ ነበር፤ ምክሬንም ለመስማት በዝምታ ያዳምጡ ነበር።

22 ንግግሬ ያረካቸው ስለ ነበር፥ ከእኔ ንግግር በኋላ የሚናገር ሰው አልነበረም።

23 ገበሬ የበልግ ዝናብ ለማግኘት እንደሚመኝ፤ እነርሱም የኔን ንግግር ለመስማት አፋቸውን ከፍተው ይጠባበቁ ነበር።

24 ፈገግ ስልላቸው ተዝናኑ፤ ፊቴ ሲበራ የተቋጠረ ፊታቸው ተፍታታ።

25 እኔ እንደ ፈለግኹት አስተዳድራቸው ነበር፤ ሠራዊቱንም እንደሚመራ ንጉሥ እመራቸው ነበር፤ በሚያዝኑበትም ጊዜ አጽናናቸው ነበር።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告