Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 28 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ጥበብን በማሞገስ የቀረበ ቅኔ

1 “በእውነቱ ማዕድን ተቈፍሮ ብር የሚወጣበትና ወርቅ የሚጣራበት ቦታ አለ።

2 ብረት ከመሬት ይገኛል፤ መዳብም ከማዕድን ድንጋይ ቀልጦ ይወጣል።

3 ሰዎች ጨለማን በማስወገድ እስከ መሬቱ ጥልቀት ዘልቀው በመግባት ራቅ ብሎ ወደሚገኘው ውስጥ በመግባት በድቅድቅ ጨለማው ውስጥ የማዕድን ድንጋይ ይፈልጋሉ።

4 ሰው ከሚኖርበት ቦታ ርቀው፥ የሰው እግር ረግጦት ወደማያውቅ ስፍራ ይደርሳሉ። እዚያም ጥልቅ ጒድጓድ ይቈፍራሉ፤ በገመድም ላይ እየተንጠለጠሉ፥ ከሰው ተለይተው ብቻቸውን ይሠራሉ።

5 ምድር ለምግብ የሚሆን እህል ታበቅላለች። ውስጥዋ በእሳት ቀልጦ ይገለባበጣል።

6 ሰንፔር የተባለው ዕንቊ በድንጋዮችዋ ውስጥ ይገኛል፤ በዐፈርዋም ውስጥ ወርቅ ይገኛል።

7 ወደ ማዕድኑ የሚወስደውን መንገድ ጭልፊት አያውቀውም፤ የአሞራም ዐይን አላየውም።

8 ክፉ አውሬዎች ያን ቦታ አልረገጡትም፤ አንበሳም በዚያ በኩል አላለፈም።

9 “ሰው መሬትን ሲቆፍር እጆቹን በሰላ ድንጋይ ላይ ያኖራል። ተራራዎችንም ከመሠረታቸው ይገለብጣል።

10 አለትን ሰንጥቆ መሿለኪያ መንገድ ያበጃል፤ ውድ የሆኑ የማዕድን ድንጋዮችንም ያገኛል።

11 የወንዞቹን ምንጮች ይገድባል፤ በምድር ውስጥ የተደበቀውንም ሀብት ያገኛል።

12 ታዲያ፥ ጥበብ ከየት ትገኛለች? ማስተዋልስ ቦታዋ የት ነው?

13 “ጥበብ ሕይወት ያላቸው ፍጥረቶች በሚኖሩባት ምድር አትገኝም፤ እውነተኛ ዋጋዋንም የሚያውቅ ሰው የለም።

14 ‘ውቅያኖስ በእኔ ውስጥ የለችም’ ይላል፤ ‘ባሕሩም ከእኔ ጋር አይደለችም’ ይላል።

15 ጥበብ በንጹሕ ወርቅ አትገዛም፤ ዋጋዋም በብር አይተመንም።

16 ጥበብ ኦፊር ከሚባል ወርቅና፥ መረግድና ሰንፔር ከሚባሉ ዕንቆች የከበረች ናት።

17 ወርቅና የጠራ መስተዋት አይስተካከሉአትም፤ ከንጹሕ ወርቅ በተሠራ ጌጥም አትለወጥም።

18 የከበሩ ዛጐልና አልማዝ ከጥበብ ጋር አይወዳደሩም። የጥበብ ዋጋ ከሉልም በላይ ነው።

19 ‘ቶጳዝዮን’ የተባለ የኢትዮጵያ ዕንቊ አይተካከላትም፤ እጅግ በጠራ ወርቅም አትገመትም።

20 ታዲያ፥ ጥበብ ከየት ትመጣለች? ማስተዋልስ ከወዴት ትገኛለች?

21 “ከሕያው ፍጡር ሁሉ የተሰወረች ናት፤ በሰማይ የሚበሩ ወፎች እንኳ ፈልገው አያገኙአትም።

22 ጥፋትና ሞት ‘ስለ እርስዋ የምናውቀው፥ በወሬ ብቻ ነው’ ይላሉ።

23 “ወደ ጥበብ የሚወስደውን መንገድና መኖሪያ ቦታዋንም የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው።

24 እርሱም የምድርን ዳርቻ ሁሉ ይመለከታል፤ ከሰማይ በታች ያለውን ሁሉ ያያል።

25 የነፋስን ኀይል በመሠረተ ጊዜ፥ የውቅያኖስን ውሃ በሰፈረ ጊዜ፥

26 ዝናብና ለነጐድጓዳዊ መብረቅ ሥርዓትን በደነገገ ጊዜ፥

27 እግዚአብሔር ጥበብን ተመለከታት ገምግሞም አከበራት፤ መርምሮም አጸናት።

28 “በዚያን ጊዜ ሰውን ‘እነሆ፥ ጥበብ ማለት እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ማስተዋልም ማለት ከክፋት መራቅ ነው’ ብሎታል።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告