ኢዮብ 26 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኢዮብ 1 ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፦ 2 “ይህን በመናገርህ ደካማውን የረዳኸው ይመስልህ ይሆን? ክንዱ የዛለውንስ ያበረታኸው ይመስልህ ይሆን? 3 ጥበብ ለጐደለው ምን ምክር ሰጠኸው! ምንስ ዕውቀት ገለጥክለት! 4 ለመሆኑ ይህን ቃል እንድትናገር የረዳህ ማነው? ያነሣሣህስ የማን መንፈስ ነው?” (ቢልዳድ) 5 “ከውቅያኖስ በታች ያሉት የሙታን ነፍሳት በከባድ መንቀጥቀጥ ላይ ናቸው። 6 የሙታን ዓለም በእግዚአብሔር ፊት ግልጥልጥ ያለ ነው፤ ምንም ነገር ሊሸፍነው አይችልም። 7 እግዚአብሔር የሰሜንን ሰማይ በሕዋው ላይ ዘረጋ፤ ምድርም በባዶ ቦታ እንድትንጠለጠል አደረገ። 8 እግዚአብሔር፥ ደመናዎች ውሃን እንዲጠቀልሉ ያደርጋል፤ ከውሃውም የተነሣ ደመናዎቹ አይቀደዱም። 9 የሙሉ ጨረቃውን ፊት ይጋርዳል፤ በደመና ይሸፍነዋል። 10 ብርሃንና ጨለማን ለመለየት በውቅያኖስ ፊት አድማስን ድንበር አድርጎ ዘረጋ። 11 እርሱ በሚገሥጻቸው ጊዜ፥ የሰማይ አዕማድ በድንጋጤ ይናወጣሉ። 12 በኀይሉ ባሕርን ጸጥ ያደርጋል፤ በጥበቡም ረዓብ የተባለውን ታላቅ አውሬ ያጠፋል። 13 በእስትንፋሱ ሰማይን ያጠራል፤ በእጁም ተወርዋሪውን እባብ ይወጋል። 14 እነዚህ ሁሉ እግዚአብሔር ከሚሠራቸው ነገሮች ጥቂቶቹ ናቸው፤ የምንሰማውም ሹክሹክታውን ብቻ ነው፤ የኀይሉን ነጐድጓድማ ማን ሊያስተውል ይችላል?” |