Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 24 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 “ሁሉን የሚችል አምላክ ፍርድ የሚሰጥበትን ጊዜ ለምን አይወስንም? የእርሱ ታማኞችስ የፍርዱን ቃል እስከ መቼ ይጠባበቃሉ?

2 “ክፉ ሰዎች ድንበር ያፈርሳሉ። በጎችንም እየሰረቁ ያሰማራሉ።

3 የድኻ አደጉን አህያ ይቀማሉ፤ ባልዋ የሞተባትን ሴት ንብረት የሆነውንም በሬ፥ በመያዣ ስም ይወስዳሉ።

4 ድኾችን በመጸየፍ ከየመንገዱ ያባርራሉ፤ ከፊታቸውም ሸሽተው እንዲደበቁ ያደርጋሉ።

5 “ድኾች በበረሓ እንዳሉ የሜዳ አህዮች ለልጆቻቸው ምግብ ለመፈለግ ወጥተው ይንከራተታሉ፤

6 ተቀጥረውም የሌላ ሰው መከር ሰብሳቢ ይሆናሉ፤ የክፉ ሰው ንብረት በሆነ የወይን አትክልት ቦታ ይቃርማሉ።

7 ሌሊቱን ሙሉ ራቁታቸውን ተኝተው ያድራሉ፤ ብርድ የሚከላከሉበትም ልብስ የላቸውም።

8 በተራራ ላይ በሚዘንበው ዝናብ ሰውነታቸው ይረሰርሳል፤ መጠለያም አጥተው ቋጥኝ ተጠግተው ያድራሉ።

9 “አባቱ የሞተበት ልጅ አገልጋይ እንዲሆናቸው የእናቱን ጡት አስጥለው ይነጥቃሉ፤ የችግረኛውንም ልጅ የዕዳ መያዣ አድርገው ይወስዳሉ።

10 ድኾች ምንም ልብስ ሳይኖራቸው ራቁታቸውን ወደ ሥራ ይሰማራሉ። በመከር ወራት ነዶ ተሸክመው እያጋዙ እነርሱ ይራባሉ።

11 በክፉ ሰዎች የአትክልት ቦታ ከወይራ ፍሬ ዘይት ያወጣሉ፤ ከወይን ዘለላም የወይን ጠጅን ይጠምቃሉ፤ እነርሱ ግን ይጠማሉ።

12 በየከተማው ለመሞት የሚያጣጥሩ ሰዎች ይቃትታሉ፤ የቈሰሉትም ሰዎች ርዳታ በመጠየቅ ይጮኻሉ። እግዚአብሔር ግን በእነርሱ ላይ የተሠራውን ግፍ አልተመለከተም።

13 “ብርሃንን የሚጠሉ ሰዎች አሉ፤ ብርሃንም ምን እንደ ሆነ ስለማያውቁ የብርሃንን መንገድ አይከተሉም።

14 ነፍሰ ገዳይ ገና ሳይነጋ በማለዳ ተነሥቶ፥ ድኾችንና ችግረኞችን ይገድላል፤ በሌሊትም ለስርቆት ይሰማራል።

15 አመንዝራ ሰው የቀኑን መምሸት ይጠባበቃል፤ ማንም ሰው እንዳያየው ፊቱን ይሸፍናል።

16 ሌቦች በሌሊት ቤት ሰርስረው ለስርቆት ይገባሉ፤ ቀን ግን ተሸሽገው ይውላሉ። ብርሃንንም ይጠላሉ።

17 የጨለማ ሽብር ስለሚያስደስታቸው ለሁሉም ድቅድቅ ጨለማ ማለዳቸው ነው።”

18 “ሆኖም እነርሱ በውሃ ላይ እንደሚታይ ዐረፋ ለጥቂት ጊዜ ብቻ ይታያሉ፤ ርስታቸው የተረገመ ይሆናል፤ ወደ ወይን ተክል ቦታቸውም ማንም አይሄድም።

19 በረዶ በሙቀት ቀልጦ ውሃውም በድርቅ እንደሚጠፋ፥ ኃጢአተኞችም ሞተው በሙታን ዓለም ይጠፋሉ።

20 እናቶቻቸው ሁሉ ይረሱአቸዋል፤ ሥጋቸውንም ትል ይበላዋል፤ ክፉ ሰዎች አይታወሱም፤ ነገር ግን እንደ ዛፍ ይሰባበራሉ።

21 ይህ ሁሉ የደረሰባቸው እነርሱ ልጆች የሌላቸው መኻኖች ሴቶችን በመበዝበዛቸውና ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች ምንም ርኅራኄ ባለማሳየታቸው ነው።

22 ነገር ግን እግዚአብሔር በኀይሉ በሥልጣን ላይ ያሉትን ሰዎች ያስወግዳቸዋል። ኑሮአቸው የተሳካ ቢመስልም እንኳ የመኖር ዋስትና የላቸውም።

23 እግዚአብሔር በሰላም እንዲኖሩ ቢፈቅድላቸውም እንኳ የሚሄዱበትን መንገድ ሁሉ አተኲሮ ይመለከታል።

24 ክፉ ሰዎች ለጥቂት ጊዜ ይበለጽጋሉ፤ ነገር ግን ወዲያውኑ እንደ አረም ጠውልገው ይጠፋሉ፤ እንደ እህልም ይታጨዳሉ።

25 እንደዚህ አይደለም ከተባለ እኔ ሀሰተኛ መሆኔንና የተናገርኩትም ቃል ትክክል አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ማነው?”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告