Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 22 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 ቴማናዊውም ኤሊፋዝ እንዲህ ሲል መለሰ፦

2 “ሰው እግዚአብሔርን ሊጠቅም ይችላልን? ሌላው ቀርቶ ጠቢብ እንኳ ቢሆን ጥቅሙ ለራሱ እንጂ ለእግዚአብሔር አይሆንም።

3 የአንተ መልካም ሥራ ሁሉን ለሚችል አምላክ ምን ይጠቅመዋል? የኑሮህስ ፍጹምነት ለእርሱ ምን ይረባዋል?

4 ታዲያ፥ በአንተ ላይ የፈረደብህና እንዲህ አድርጎ የገሠጸህ የእግዚአብሔር ወዳጅ ስለ ሆንክ ነውን?

5 ይህ ሁሉ የደረሰብህ ክፋትህ ስለ በዛና ኃጢአትህም ወሰን የሌለው ስለ ሆነ አይደለምን?

6 ወንድሞችህን ያለ አንዳች ምክንያት በዋስትና አስይዘሃቸዋል፤ ሌሎችንም ልብሳቸውን ገፈህ ራቊታቸውን አስቀርተሃቸዋል።

7 ተርበውና ተጠምተው ለደከሙ እህልና ውሃ ከልክለሃል።

8 ምድር የኀይለኛ ሰዎች ንብረት፥ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ይዞታ ሆናለች።

9 ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች ባዶ እጃቸውን ሰደሃል፤ የሙት ልጆችንም መተዳደሪያ አጥፍተሃል።

10 በዚህም ምክንያት እነሆ፥ ዙሪያህን በወጥመድ ተከበሃል፤ ድንገተኛ አደጋም ያሸብርሃል፤

11 ማየት እስከሚሳንህ ድረስ ጨለማ ወርሶሃል፤ የጐርፍ ውሃም አጥለቅልቆሃል።

12 “እግዚአብሔር ከፍ ባለው ሰማይ የሚኖር አይደለምን? ከዋክብት ምንም እንኳ ከፍ ባለ ስፍራ ቢሆኑ፥ እርሱ ከበላያቸው ሆኖ ይመለከታቸዋል።

13 አንተ ግን ‘እግዚአብሔር ምን ያውቃል? ከድቅድቅ ጨለማ ባሻገር ሆኖ እንዴት ሊፈርድብን ይችላል?

14 ጠፈር ላይ ሲመላለስ ድቅድቅ ደመና ስለሚጋርደው ሊያይ አይችልም’ ትላለህ።

15 “ኃጢአተኞች ይመላለሱበት የነበረው የዱሮውን መንገድ ትከተላለህን?

16 እነርሱ እኮ ጊዜአቸው ሳይደርስ ተቀሥፈዋል፤ በጐርፍም ተጠራርገው ሥር መሠረታቸው ጠፍቶአል።

17 እነርሱም ሁሉን የሚችለውን አምላክ፦ ‘ከእኛ ራቅ፤ ምን ልታደርግልን ትችላለህ?’ አሉት።

18 ሆኖም ቤታቸውን በብልጽግና የሞላው እግዚአብሔር ነው። ስለዚህ እኔ የክፉ ሰዎችን ሐሳብ አልቀበልም።

19 ክፉ ሰዎች ሲቀጡ በማየት ደጋግ ሰዎች ይደሰታሉ፤ ቀጥተኞች እንዲህ እያሉ በእነርሱ ላይ ያፌዛሉ፥

20 ‘በእርግጥ ጠላቶቻችን ጠፍተዋል፤ ንብረታቸውም ሁሉ በእሳት ጋይቶአል።’

21 “ስለዚህ ኢዮብ ሆይ፥ ራስህን ለእግዚአብሔር አስገዛ፤ ከእርሱም ጋር ሰላም ይኑርህ፤ ይህን ብታደርግ መልካም ነገርን ታገኛለህ።

22 እግዚአብሔር የሚሰጥህን ትምህርት ተቀበል፤ ቃሉንም በልብህ አኑር።

23 ራስህን ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመልስ እንደ ቀድሞህ ትሆናለህ። ከቤትህ የክፋትን ሥራ አስወግድ

24 ወርቅን ወደ ትቢያ ጣለው፤ የኦፊርንም ወርቅ እንደ ጅረት ድንጋይ ወርውረው፤

25 በዚያን ጊዜ ሁሉን ቻይ አምላክ ለአንተ ወርቅና ንጹሕ ብር ይሆንልሃል።

26 በዚያን ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፤ በእርሱም ተማምነህ ትኖራለህ።

27 ወደ እርሱም በምትጸልይበት ጊዜ የለመንከውን ሁሉ ስለሚፈጽምልህ፥ ስለትህን ትከፍላለህ።

28 ዕቅድህ ሁሉ ይሳካልሃል፤ መንገድህ ሁሉ ብርሃን ይሆንልሃል።

29 እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ያዋርዳል፤ ትሑታንን ግን ያድናቸዋል።

30 አንተም ቅን ልብ ያለህ ብትሆን እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፤ እጆችህም ከበደል ሥራ የነጹ ቢሆኑ እግዚአብሔር ይታደግሃል።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告