ኢዮብ 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኢዮብ 1 ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፦ 2 “እስቲ ንግግሬን በጥሞና አድምጡኝ፤ በዚህም እኔን እንዳጽናናችሁኝ ይቈጠርላችሁ። 3 አንድ ጊዜ ለመናገር ዕድል ስጡኝ፤ ከዚያ በኋላ እንደ ፈለጋችሁ መሳለቅ ትችላላችሁ። 4 “እኔ የማዝነው በሰብአዊ ፍጡር ላይ ነውን? ታዲያ፥ ትዕግሥቴ ቢያልቅ ምን ያስገርማል? 5 እስቲ ወደ እኔ ተመልከቱ፤ መናገር እስኪያቅታችሁ ድረስ ሁኔታዬ ያሠቅቃችኋል። 6 እኔ እንኳ ሳስበው ያስደነግጠኛል፤ ሰውነቴንም በፍርሃት ያንቀጠቅጠዋል። 7 “ክፉ ሰዎች ዕድሜአቸው ረዝሞ፥ ሃብታቸው በዝቶ በምድር ላይ ስለምን ይኖራሉ? 8 ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው አድገውና ተደላድለው ሲኖሩ ለምን ያያሉ? 9 ያለ አንዳች ሥጋት በሰላም ይኖራሉ፤ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ደርሶባቸው አያውቅም፤ 10 ከብቶቻቸው ያለአንዳች ችግር ይረባሉ፤ ላሞቻቸውም ምንም ሳይጨነግፉ ይወልዳሉ። 11 ልጆቻቸውን እንደ በግ መንጋ ያሰማራሉ፤ ሕፃናታቸውም ይቦርቃሉ። 12 አታሞ እየመቱ፥ በገና እየደረደሩ፥ እምቢልታ እየነፉ፥ በደስታ ይዘፍናሉ። 13 ዕድሜአቸውን በተድላ ደስታ ያሳልፋሉ፤ ያለ ሥቃይም ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ። 14 “ይህም ሆኖ ሳለ እግዚአብሔርን ‘ከእኛ ራቅ፤ የአንተን መንገድ ማወቅ አንፈልግም’ ይሉታል። 15 ‘እናመልከው ዘንድ ሁሉን ቻይ አምላክ ማነው? ወደ እርሱስ መጸለይ ምን ይጠቅመናል?’ ይላሉ። 16 ይህንንም የሚሉት በእጃቸው ያለው ሀብት ሁሉ በራሳቸው ጥረት የተገኘ ስለሚመስላቸው ነው፤ እኔ ግን የክፉ ሰዎችን ሐሳብ አልቀበልም። 17 “ለመሆኑ የክፉ ሰዎች መብራት ጠፍቶ ያውቃልን? መቅሠፍትስ በእነርሱ ላይ ወርዶ ያውቃልን? እግዚአብሔር በቊጣው ቀጥቶአቸው ያውቃልን? 18 እንደ ገለባ በነፋስ የተወሰዱበት፥ እንደ ትቢያም በዐውሎ ነፋስ የተጠረጉበት ጊዜ አለን? 19 “እናንተ ‘እግዚአብሔር በአባቶች በደል ልጆችን ይቀጣል’ ትላላችሁ፤ እስቲ እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን ራሳቸውን ይቅጣቸው፤ ይህ ከሆነ በደለኛነታቸውን ሊገነዘቡት ይችላሉ። 20 ኃጢአተኞች ራሳቸው በሠሩት በደል ቅጣታቸውን ይቀበሉ፤ ሁሉን የሚችል አምላክ ቊጣውን ያውርድባቸው፤ 21 ሰው ከሞተ በኋላ፥ ስለ ልጆቹ ምን ደንታ ይኖረዋል? 22 እግዚአብሔር በታላላቅ ሰዎች ላይ እንኳ ይፈርዳል፤ ታዲያ፥ ሰው ለእርሱ የፍርድን ዕውቀት ሊያስተምር ይችላልን? 23 “አንዳንድ ሰዎች እስከ ሕይወታቸው መጨረሻ ምንም ችግር ሳይደርስባቸው ብርቱዎችና ጤናማዎች ሆነው፥ 24 ሰውነታቸው ወፍሮ እንዳማረባቸው፥ አጥንታቸውም በመቅን እንደ ተሞላ (እንደ ለመለመ) ይሞታሉ። 25 ሌሎች ግን መሪር ሐዘን ሳይለያቸው፥ በችግር እንደ ተቈራመዱ መልካም ነገር ሳያገኙ ይሞታሉ። 26 ሁሉም ወደ መቃብር በአንድ ላይ ወርደው ዐፈር ይሆናሉ፤ ትልም ይወርሳቸዋል። 27 “እነሆ፥ እኔን ለመበደል በማሰብ በአእምሮአችሁ ያቀዳችሁትን ተንኰል ዐውቃለሁ። 28 እናንተ ‘የዚያ የትልቅ ሰው ቤት የት ነው?’ የክፉውስ ሰው መኖሪያ የት ነው? ትላላችሁ። 29 መንገደኞችን አልጠየቃችሁምን? የተናገሩትንስ ምስክርነት አትቀበሉምን? 30 እነዚያ ‘ክፉ ሰዎች መቅሠፍት በሚመጣበት ጊዜ ጒዳት አይደርስባቸውም፤ የእግዚአብሔር ቊጣም ሲገለጥ ያመልጣሉ’ ሲሉ ተናግረዋል። 31 ክፉውን ሰው ስለ መጥፎ ጠባዩ የሚወቅሰው ማን ነው? በክፉ ሥራውስ የሚቀጣው ማን ነው? 32 ከሞተ በኋላም አስከሬኑን ተሸክመው ወደ መቃብርም ይወስዱታል፤ መቃብሩ ይጠበቃል፤ 33 በሸለቆ ያለው ዐፈር ይመቻችለታል፤ ሰዎች ሁሉ ይከተሉታል፤ እጅግ ብዙ ሕዝብም በፊቱ ይሄዳል። 34 “ታዲያ፥ እናንተ ከንቱ በሆነ አነጋገር ልታጽናኑኝ ለምን ትሞክራላችሁ? የምትመልሱልኝ መልስ ሁሉ ሐሰት ነው።” |