Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ጾፋር

1 ናዕማታዊው ጾፋርም እንዲህ ሲል መለሰ፦

2 “ኢዮብ ሆይ! የሕሊናዬ ብስጭት መልስ እንድሰጥህ አስገደደኝ፤ ስለዚህም ነው ለመናገር የቸኰልኩት።

3 የምሰማው እኔን የሚያዋርድ ተግሣጽ ነው፤ የማስተዋል ችሎታዬ መልስ እንድሰጥ ይመራኛል።

4 “ሰው በምድር ላይ ከተገኘበት ጊዜ ጀምሮ ከጥንት እንደዚህ እንደ ሆነ ታውቃለህ።

5 የክፉ ሰው ድንፋታ ለአጭር ጊዜ ነው፤ እግዚአብሔርንም የሚክዱ ሰዎች ደስታቸው በቅጽበት የሚጠፋ ነው።

6 ክፉ ሰው ምንም እንኳ በትዕቢቱ እስከ ሰማይ ከፍ ቢልም ዐናቱም ደመናን ቢነካ

7 እርሱ እንደ ራሱ ኩስ በፍጹም ይጠረጋል፤ ያዩት የነበሩ ሰዎችም ወዴት ነው? ይላሉ።

8 እንደ ሕልም ብን ብሎ ስለሚጠፋ አይገኝም፤ እንደ ሌሊት ራእይም ይጠፋል።

9 ከሚኖርበት ቦታ ደብዛው ስለሚጠፋ፥ አንድ ጊዜ የተመለከተው ሰው ዳግመኛ አያየውም።

10 ልጆቹ እየተለማመጡ አባታቸው ከድኾች በግፍ የቀማውን ገንዘብ ይከፍላሉ።

11 ኀይል የተሞላው የወጣትነት ሰውነቱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዐፈር ይሆናል።

12 “ምንም እንኳ ክፋት በአፉ ውስጥ እንደ ምግብ ቢጣፍጠው፥ በምላሱ ቢያጣጥመው፥

13 እንዳያልቅበትም በአፉ ይዞ እያላመጠ ቢያቈየውም፥

14 በሆዱ ውስጥ ግን ወደ መራራነት ይለወጣል፤ እንደ እባብ መርዝም ይሆንበታል።

15 ክፉ ሰው የበላውን ሀብት በግዱ ይመልሳል፤ በሆዱ ውስጥ ያለውንም ሁሉ እግዚአብሔር ያስተፋዋል።

16 ክፉ ሰው የሚበላው ሁሉ መርዝ ይሆንበታል፤ መርዝም ሆኖ ይገድለዋል።

17 የወይራ ዘይት እንደ ጐርፍ ሲወርድ፥ ማርና ወተት እንደ ጅረት ውሃ ሲፈስ ሳያይ ይሞታል።

18 የድካሙን ፍሬ መልሶ ያስረክባል እንጂ አይበላም፤ ነግዶ ባተረፈውም ሀብት አይደሰትበትም።

19 ይህም የሚሆነው ድኻን ስለ ጨቈነና ያልሠራውንም ቤት በግፍ ስለ ወሰደ ነው።

20 ስግብግብነቱ ዕረፍት ነሥቶታል፤ ያካበተው ሀብትም ሊያድነው አይችልም።

21 ሀብቱ ሁሉ ተሟጦ ስለሚያልቅ የሚቀምሰው ነገር አያገኝም።

22 ምንም እንኳ ሀብታም ቢሆን ብስጭት ይደርስበታል፤ ብዙ ችግርም ያጋጥመዋል።

23 በልቼ እጠግባለሁ ሲል እግዚአብሔር ኀይለኛ ቊጣውን ያወርድበታል። መዓቱንም በእርሱ ላይ ያዘንብበታል።

24 ከብረት ሰይፍ ቢያመልጥ በነሐስ ፍላጻ ይወጋል፤

25 ፍላጻውም ዘልቆ በስተጀርባው ይወጣል፤ የሚያብለጨልጨው ጫፉ ጒበቱን በጣጥሶ ያልፋል፤ በታላቅ ፍርሀትም ልቡ ይሸበራል።

26 ያካበተው ንብረት ሁሉ ጥቅጥቅ ባለ ጨለማ ውስጥ ይወድማል፤ በሰው እጅ ያልተቀጣጠለ እሳትም ያቃጥለዋል፤ በቤቱ ውስጥ የሚተርፈውን ንብረት ሁሉ ያጋየዋል።

27 የሠራውን ኃጢአት ሰማይ ሁሉ ይገልጥበታል፤ ምድርም በጠላትነት ትነሣበታለች።

28 በእግዚአብሔርም የቊጣ ቀን የቤቱ ንብረት ሁሉ በጐርፍ ተጠራርጎ ይወሰዳል።

29 እግዚአብሔር ለዐመፀኞች የወሰነላቸው ዕድል ፈንታ፥ የክፉ ሰዎች ዋጋ ይኸው ነው።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告