ኢዮብ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሰይጣን ኢዮብን እንደገና መፈተኑ 1 ከዕለታት አንድ ቀን የሰማይ መላእክት በእግዚአብሔር ፊት በቀረቡ ጊዜ ሰይጣንም አብሮአቸው ቀረበ። 2 እግዚአብሔርም “ከወዴት መጣህ?” ብሎ ሰይጣንን ጠየቀው። ሰይጣንም “በምድር ዙሪያ ወዲያና ወዲህ እመላለስ ነበር” አለው። 3 እግዚአብሔርም ሰይጣንን “አገልጋዬን ኢዮብን ልብ ብለህ አየኸውን? እርሱን የመሰለ ታማኝና ደግ ሰው በምድር ላይ አይገኝም፤ እርሱ ከክፋት ሁሉ ርቆ እኔን የሚፈራ ቀጥተኛ ሰው ነው፤ እርሱን ማጥፋት እንድትችል እፈቅድልህ ዘንድ ያነሣሣኸኝ በከንቱ ነው፤ እነሆ፥ ኢዮብ አሁንም በቅንነቱ እንደ ጸና ነው” አለው። 4 ሰይጣንም “በቊርበት ፈንታ ቊርበት” እንዲሉ፥ “ሰው እኮ ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል። 5 ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ በመላ ሰውነቱ ላይ ጒዳት ብታደርስበት በእርግጥ ፊት ለፊት ይሰድብሃል!” አለው። 6 እግዚአብሔርም ሰይጣንን “መልካም ነው፤ አትግደለው እንጂ በእርሱ ላይ የፈለግኸውን ማድረግ ትችላለህ” አለው። 7 ከዚህ በኋላ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ኢዮብን ከራስ ጠጒሩ እስከ እግር ጥፍሩ ድረስ በከባድ ቊስል እንዲሠቃይ አደረገው። 8 ከዚህም የተነሣ ኢዮብ በዐመድ ክምር ላይ ተቀምጦ ቊስሉን በገል ያክ ጀመር። 9 ሚስቱም “አሁንም በእግዚአብሔር ላይ ያለህ ቅንነት እንደ ጸና ነውን? ይልቅስ እግዚአብሔርን ካደውና ሙት!” አለችው። 10 ኢዮብም “እንዴት የሞኝ ሴት ንግግር ትናገሪያለሽ? እግዚአብሔር መልካም ነገር ሲሰጠን በደስታ እንቀበላለን፤ ታዲያ፥ መከራ ሲያመጣብን በእርሱ ላይ ማጒረምረም ይገባናልን?” አላት። ኢዮብ ምንም እንኳ ይህ ሁሉ መከራና ሥቃይ ቢደርስበት በእግዚአብሔር ላይ ክፉ ነገር በመናገር ኃጢአት አልሠራም። ሦስት የኢዮብ ወዳጆች ሊጐበኙት መምጣታቸው 11 የቴማን አገር ሰው የሆነው ኤሊፋዝ፥ የሹሐ አገር ሰው የሆነው ቢልዳድና የናዕማ አገር ሰው የሆነው ጾፋር፥ እነዚህ ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆች ነበሩ። እነርሱም በኢዮብ ላይ የደረሰውን ሥቃይ በሰሙ ጊዜ ሐዘናቸውን ሊገልጹለትና ሊያጽናኑት ከየአገራቸው ተጠራርተው በአንድነት ወደ ኢዮብ መጡ። 12 ገና በሩቅ ሳሉ ኢዮብን አዩት፤ ሆኖም እርሱ መሆኑን በቀላሉ ለይተው ሊያውቁት አልቻሉም። በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ትቢያ ወደ ሰማይ እየበተኑና በራሳቸውም ላይ እየነሰነሱ በመጮኽ ማልቀስ ጀመሩ። 13 የሥቃዩንም ብዛት ስላዩ ምንም ቃል ሳይናገሩ ከእርሱ ጋር ሰባት ቀንና ሰባት ሌሊት በመሬት ላይ ተቀምጠው ሰነበቱ። |