ኢዮብ 19 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኢዮብ 1 ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፦ 2 “እስከ መቼ ድረስ ታሠቃዩኛላችሁ? እስከ መቼስ በነገር ቅስሜን ትሰብሩታላችሁ? 3 እነሆ ዐሥር ጊዜ ትሰድቡኛላችሁ፤ ስታዋርዱኝም አታፍሩም። 4 በእርግጥ ተሳስቼ ከሆነ፥ ስሕተቱ የሚጐዳው ራሴን ብቻ ነው። 5 በእውነት እናንተ ራሳችሁን ከፍ ከፍ አድርጋችሁ፥ የእኔን መዋረድ የመከራከሪያ ነጥብ ታደርጉታላችሁ 6 ነገር ግን ይህን ሁሉ መከራ ያደረሰብኝና መረብ ውስጥም የጣለኝ እግዚአብሔር መሆኑን እንድታውቁ እወዳለሁ። 7 ተበደልኩ ብዬ ብጮኽ የሚሰማኝ አላገኘሁም፤ ድምፄን ከፍ አድርጌ አቤቱታ ባሰማም ፍትሕ አላገኘሁም። 8 እግዚአብሔር መንገዴን ሁሉ ስለ ዘጋው መተላለፊያ የለኝም፤ መሄጃዬንም በጨለማ ጋርዶታል። 9 ክብሬን ከራሴ ላይ ገፎ አዋረደኝ። 10 ሰውነቴን በየአቅጣጫው በመቀጥቀጥ ጨርሶ አፈራረሰው፤ የነበረኝንም ተስፋ ሥሩ ተነቃቅሎ እንደሚወድቅ ዛፍ አደረገው። 11 እግዚአብሔር ተቈጥቶ መዓቱን አፈሰሰብኝ፤ እንደ ጠላትም ቈጠረኝ። 12 እኔን ለማጥፋት ሠራዊቱን ላከ፤ በድንኳኔም ዙሪያ ምሽግ ሠርተው ከበቡኝ። 13 “እግዚአብሔር ወንድሞቼ ከእኔ እንዲርቁ አደረገ፤ የሚያውቁኝም ሰዎች ሁሉ ባይተዋር አደረጉኝ። 14 ዘመዶቼ ራቁኝ፤ ወዳጆቼም ረሱኝ። 15 በእንግድነት በቤቴ ተቀብዬ ያስተናገድኳቸው ሁሉ ረሱኝ፤ ገረዶቼ ሁሉ እንደ መጻተኛ ቈጠሩኝ፤ እንደ ባዕድም ተመለከቱኝ። 16 አገልጋዬን ስጠራው መልስ አይሰጠኝም እባክህ እርዳኝ ብዬ ስለምነውም እንኳ እሺ አይለኝም። 17 ሚስቴ ጠረኔን ጠላችው፤ የገዛ ወንድሞቼም ተጸየፉኝ። 18 ሕፃናት እንኳ ይንቁኛል፤ እኔንም በሚያዩበት ጊዜ ያፌዙብኛል። 19 የቅርብ ወዳጆቼ ተጸየፉኝ፤ በጣም የምወዳቸው ሰዎች በጠላትነት ተነሡብኝ። 20 ሥጋዬ አልቆ ቆዳዬ በአጥንቴ ላይ ተጣበቀ፤ ድድ ብቻ ቀርቶልኝ ተረፍኩ። 21 “ወዳጆቼ ሆይ! የእግዚአብሔር እጅ ስለ መታኝ እባካችሁ እናንተ እዘኑልኝ! ራሩልኝም! 22 እግዚአብሔር እንዳሳደደኝ እናንተ ደግሞ ለምን ታሳድዱኛላችሁ? እስካሁንስ ያሠቃያችሁኝ አይበቃችሁምን? 23 “እስከ አሁን የተናገርኩትን ቃል የሚያስታውስና በመጽሐፍ የሚመዘግበው ሰው ቢገኝ እንዴት ደስ ባለኝ ነበር! 24 ምነው በብረት መሣሪያና በእርሳስ ተጽፈው ወይም በድንጋይ ላይ ተቀርጸው ለዘለዓለም እንዲኖሩ ቢደረግ እንዴት ደስ ባለኝ ነበር! 25 ነገር ግን አዳኜ ሕያው እንደ ሆነና፥ በመጨረሻ ጊዜም እኔን ለመታደግ በምድር ላይ እንደሚቆም ዐውቃለሁ። 26 ቆዳዬ ተበልቶ ቢያልቅም፥ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንደማየው ዐውቃለሁ። 27 እርሱም እኔው ራሴ የማየው ነው፤ ዐይኖቼ ያዩታል፤ ሌላም አይደለም፤ ልቤም ያችን ዕለት በጣም ይናፍቃል። 28 “ወዳጆቼ ሆይ! እኔን ወቅሳችሁ ለማሠቃየት፥ የችግሩን ምክንያት እርሱ ራሱ ነው በማለት ትናገራላችሁ። 29 የእግዚአብሔር ቊጣ የሰይፍን ቅጣት ስለሚያስከትል ሰይፍ እንዳይበላችሁ ተጠንቀቁ። የእግዚአብሔር ፍርድ መኖሩንም ዕወቁ።” |