Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 18 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ቤልዳድ

1 ሹሐዊው ቢልዳድም እንዲህ ሲል መለሰ፦

2 “ኢዮብ ሆይ! ለምን እንደዚህ ንግግር ታበዛለህ? እስቲ አድምጥ፤ እኛም እንናገር።

3 ስለምን አንተ እኛን እንደ እንስሶች ትቈጥረናለህ? ለምንስ እንደ ደንቆሮዎች የማናስተውል አድርገህ ትመለከተናለህ?

4 አንተ ብትቈጣ ራስህን ትጐዳለህ እንጂ በአንተ ቊጣ ምድር ባዶ አትሆንም። አለቶችም ከስፍራቸው አይነቃነቁም።

5 “የኃጢአተኛ መብራት ይጠፋል፤ የእሳቱም ነበልባል ዳግመኛ አይታይም።

6 በእርሱ ድንኳን ውስጥ ያለው መብራት ይጠፋል፤ ብርሃኑም ይጨልማል።

7 የብርቱ ዕርምጃው ርዝመት እያጠረ ይሄዳል፤ የራሱም የተንኰል ዕቅድ ይጥለዋል።

8 በገዛ ራሱ እርምጃ አሽክላ ውስጥ ይገባል፤ እግሩም በመረቡ ውስጥ ይተበተባል።

9 አሽክላ ተረከዙን ይይዘዋል፤ ወጥመድም አጣብቆ ያስቀረዋል።

10 በመሬት ላይ የሸምቀቆ ገመድ ተዘርግቶለታል፤ በመንገዱም ወጥመድ ተዘጋጅቶአል።

11 “ፍርሀት በዙሪያው ከቦታል፤ በኋላው እየተከተለም ያሳድደዋል።

12 ኀይሉ በራብ አልቆአል፤ ቀጠናም እርሱን ሊያጠፋው ተዘጋጅቶአል።

13 በሽታ ሰውነቱን ያመነምነዋል፤ ሞትም ጨርሶ ይረከበዋል።

14 ያለ ስጋት ተማምኖ ከሚኖርበት ቤት ይባረራል፤ የሰው ሁሉ ገዢ ወደ ሆነው ወደ ሞት ይወሰዳል።

15 በቤቱ ውስጥ ምንም ነገር አይቀርለትም፤ በመኖሪያውም ውስጥ ዲን ይበተናል።

16 ሥሩ ከመሠረቱ እንደሚደርቅና ቅርንጫፎቹም እንደሚረግፉ ዛፍ ይሆናል።

17 በምድር ላይ የሚያስታውሰው አይኖርም። ዝናውም ከምድር ይጠፋል።

18 ከብርሃን ወደ ጨለማ ይባረራል፤ ከሕያዋን ምድርም ይወገዳል።

19 በወገኖቹ መካከል ለእርሱ ተተኪ የሚሆን ትውልድ አይገኝለትም፤ በመኖሪያውም ዘር አይተርፍለትም።

20 የምዕራብና የምሥራቅ ሰዎች በእርሱ ላይ በደረሰው መከራ እጅግ ፈርተው ተንቀጠቀጡ።

21 ምን ጊዜም የክፉ ሰዎች መጨረሻ ይኸው ነው፤ እግዚአብሔርንም የማይፈሩ ሰዎች ዕድል ፈንታቸው ይህ ነው።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告