ኢዮብ 15 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሁለተኛው ክርክር ኤሊፋዝ ( 15፥1—21፥34 ) 1 ቴማናዊው ኤሊፋዝ እንዲህ ሲል መለሰ፦ 2 “በውኑ ብልኅ ሰው እንደ ነፋስ የማይጨበጥ ነገር ይናገራልን? በሆዱስ ጐጂ የሆነ ሐሳብ ሊኖረው ይገባልን? 3 ለመሆኑ ብልኅ ሰው ምንም በማይጠቅሙ ቃላትና ዋጋ በሌለው ንግግር ይከራከራልን? 4 አንተ እግዚአብሔርን መፍራት ትተሃል፤ ለእግዚአብሔር የሚገባውንም አምልኮ ታደናቅፋለህ። 5 በደለኛነትህ በአነጋገርህ ይታወቃል፤ ነገር ግን በብልጠት አነጋገር ልትሸፍነው ትሞክራለህ። 6 የሚፈርድብህ የገዛ አንደበትህ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፤ አነጋገርህም ያጋልጥሃል። 7 “ከሰው በፊት የተወለድክ አንተ ነህን? ተራራዎችስ ከመፈጠራቸው በፊት ተወልደህ ነበርን? 8 በውኑ የእግዚአብሔርን ምሥጢር ሰምተሃልን? ሰብአዊ ጥበብን ሁሉ የምታውቅ አንተ ብቻ የሆንክ ይመስልሃልን? 9 እኛ ከምናውቀው የተለየ የምታውቀው ነገር ምንድን ነው? ከእኛ ተሰውሮ ለአንተ የተገለጠልህ ምን ጥበብ አለ? 10 በዕድሜ ከአባትህ የሚበልጡ ጠጒራቸው የሸበተ ሽማግሌዎች በሐሳብ ከእኛ ጋር ናቸው። 11 “በእኛ አማካይነት የሚነግርህ ከእግዚአብሔር የተሰጠህ መጽናናት አይበቃህምን? 12 ልብህ ለምን ወደ ሌላ ይወስድሃል? ስለምንስ በቊጣ ዐይኖችህን ታፈጣለህ? 13 ይህንንም በማድረግህ በእግዚአብሔር ላይ መንፈስህን አነሣሥተሃል። እንዲህ ያለውን ሁሉ የወቀሳ ቃል እስከ መናገር ደርሰሃል። 14 “ሰው ንጹሕ ሊሆን ይችላልን? ሥጋ ለባሽስ ጻድቅ ሊሆን ይችላልን? 15 እግዚአብሔር በመላእክቱ ላይ እምነት የለውም፤ ሰማያት እንኳ በእርሱ ፊት ንጹሓን አይደሉም፤ 16 የተበላሸና የረከሰ ኃጢአትንም እንደ ውሃ የሚጠጣ ሰውማ ምንኛ የባሰ ነው? 17-18 “አባቶቻቸው ሳይደብቁ ያስተላልፉላቸውን፥ ጥበበኞች የገለጡትን፥ እኔም የመረመርኩትን አስረዳሃለሁና ስማኝ፤ ልንገርህ። 19 ምድሪቱ ለእነርሱ ብቻ ተሰጥታ ነበር፤ መጻተኞችም በመካከላቸው አልተቀላቀሉባቸውም። 20 “ሰዎችን ሲጨቊን የኖረ ክፉ ሰው ዕድሜ ልኩን ሲሠቃይ ይኖራል። 21 የሽብርን ድምፅ በጆሮው ይሰማል፤ ሁሉ ነገር ሰላም መስሎ በሚታይበት ጊዜ አጥፊው ይመጣበታል። 22 ዕድል ፈንታው በሰይፍ መሞት ስለ ሆነ፥ ከጨለማ የማምለጥ ተስፋ የለውም፤ 23 ለአሞራ እንደሚጣል ምግብ ይጣላል፤ የሚጠፋበት ጨለማው ቀን እንደ ቀረበበት ያውቃል። 24 የጨለማው ጊዜ አስፈራራው፤ አንድ ንጉሥ ለጦርነት እንደ ተዘጋጀ ዐይነት ሐዘንና ጭንቀት ይበረቱበታል። 25 “ይህም የሚሆነው እጁን በእግዚአብሔር ላይ አነሣ፤ ሁሉን የሚችለውንም አምላክ ተዳፈረ። 26 የተዳፈረውም በትከሻው ላይ ጠንካራና ሰፊ ጋሻውን አንግቦ በትዕቢት ወደ እርሱ፥ እየገሠገሠ ነው። 27 ፊቱ በስብ ተሸፍኖአል ወገቡም በውፍረት ተድቦልብሎአል። 28 “ይህ ሰው በወደሙ ከተሞች፥ ሰው በማይኖርባቸውና ለመፍረስ በተቃረቡ ቤቶች ውስጥ ይኖራል። 29 ባለጸጋ አይሆንም፥ ሀብቱም ለብዙ ጊዜ አይቈይም፤ በምድር ላይም አይስፋፋም። 30 ከጨለማ ማምለጥ አይችልም፤ የእሳት ነበልባል ቅርንጫፎቹን እንዳደረቃቸውና አበባዎቹም በነፋስ እንደ ረገፉበት ዛፍ ይሆናል። 31 በከንቱ ነገር እየተማመነ ራሱን አያታል፤ በዚህም ዋጋ ቢስ ሆኖ ይቀራል። 32 ጊዜው ሳይደርስ ግንዱ እንደሚደርቅና ቅርንጫፎቹም እንደማይለመልሙ ዛፍ ይሆናል። 33 ገና ሳይበስል ዘለላውን እንደሚያረግፍ የወይን ተክልና አበባው እንደሚረግፍ የወይራ ዛፍ ይሆናል። 34 “የእግዚአብሔርን ሕልውና የሚክዱ ሰዎች ዘር አይወጣላቸውም፤ በጉቦ የተሠሩ ቤቶችም በእሳት ይጋያሉ። 35 እንደዚህ ያሉ ሰዎች ተንኰልን ያቅዳሉ፤ ችግርንም ይወልዳሉ፤ ልባቸውም በአታላይነት የተሞላ ነው።” |